የሽመክት ጉግሳ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ጎል ፋሲል ከነማ መቻልን 1-0 እንዲረታ አድርጋለች።
መቻሎች ከአርባምንጩ ሽንፈት አንፃር አምስት ቅያሪዎችን ያደረጉ ሲሆን ቶማስ ስምረቱ ፣ ዳዊት ማሞ ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ በኃይሉ ኃይለማሪያም እና ምንይሉ ወንድሙን አስጀምረዋል። በባህር ዳር የተሸነፉት ፋሲል ከነማዎች ደግሞ ወንድምአገኝ ማርቆስ እና መናፍ ዐወልን ቅጣት ላይ በሚገኙት ዓለምብርሀን ይግዛው እና አምሳሉ ጥላሁን ቦታ እንዲሁም ሀብታሙ ገዛኸኝን በይሁን እንዳሻው ምትክ ወደ ቀዳሚ አሰላለፍ አምጥተዋል።
ጨዋታውን በተሻለ የኳስ ቁጥጥር የጀመሩት መቻሎች ቀዳሚውን አደገኛ ሙከራም አድርገዋል። 8ኛው ደቂቃ ላይ በኃይሉ ኃይለማሪያም ከሳሙኤል ሳሊሶ ተቀብሎ ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። ሆኖም የመቻልን ቅብብሎች በሚያቋርጡበት ቅፅበት ረዘም ያሉ ኳሶችን ወደ ፊት ይልኩ የነበሩት ፋሲሎች 16ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። ጎሉ በኃይሉ ኃይለማሪያም ሳጥን ውስጥ ኳስ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሽመክት ጉግሳ ሲያስቆጥር የተመዘገበ ነበር።
እምብዛም ጠንካራ ሙከራ ባላሳየን ቀሪው የአጋማሹ ክፍል መቻሎች በቅብብል ሰብረው ለመግባት የሚያረጉት ጥረት ወደ ኋላ በተሳቡት ዐፄዎቹ ጠንከር ያለ ሽፋን ገጥሞታል። ፋሲሎችም እንዲሁ ወደ ፊት በሚልኳቸው ኳሶች አልፎ አልፎ ጥሩ ቅፅበቶችን ቢያገኙም ተገቢውን ውሳኔ ማሳለፍ ሳይችሉ እየቀሩ የውብሸት ጭላሎን ግብ መፈተሽ አልሆነላቸውም።
ከዕረፍት በኋላ የጨዋታው እንቅስቃሴ ይበልጥ የተዳከመ ሆኗል። መቻሎች ከሜዳቸው መውጣት ይበልጥ ከብዷቸው ሲታይ ይልቁኑም ወደ ፊት ገፍተው የተጋጣሚን እንቅስቃሴ ከጅምሩ ለማፈን ጥረታቸውን የቀጠሉት ፋሲሎች 62ኛው ደቂቃ ላይ ሊሳካላቸው ተቃርቦ ነበር። በዚህም በዛብህ መለዮ በመቻል ሳጥን መውጫ ላይ ከግሩም ሀጎስ ያስጣለውን ኳስ ታፈሰ ሰለሞን ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል።
መቻሎች ከነዓን ማርክነህ እና እስራኤል እሸቱን ቀይረው በማስገባት የማጥቃት ሂደታቸውን ለማሻሻል ሞክረዋል። ቡድኑ በጥቂቱ ተነቃቅቶ ቢታይም አሁንም የመጨረሻ የግብ ዕድል ለመፍጠር መቸገሩ አልቀረም። በጥሩ መከላከል ውጤታቸውን አስጠብቀው የቀጠሉት ፋሲሎች በመጨረሻ ደቂቃዎች ነቅለው ይወጡ የነበሩት መቻሎች ጀርባ በመገኘት አደገኛ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል።
በዚህ ረገድ 78ኛ እና 82ኛ ደቂቃዎች ላይ ኦሴይ ማዉሊ ከቅጣት ምት ያደረጋቸው ሙከራዎች ጨዋታውን በመጠኑ ነፍስ የዘሩበት ሲሆን ይኸው አጥቂ 86ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ አጥብቦ በመግባት ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ያደረገው ሙከራም ለጥቂት የወጣ ነበር። ተቀይሮ የገባው ይሁን እንዳሻውም እንዲሁ የርቀት ሙከራ አድርጓል። ከሁሉም በላይ ለግብ በቀረበው አጋጣሚ ማዉሊ በመጨረሻ ደቂቃ ያገኘውን ነፃ ኳስ ውብሸት ጭላሎ አድኖበት ጨዋታ በፋሲል ከነማ 1-0 ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጨዋታው በሚፈልጉት መንገድ እንደሄደ ተናግረው ቡድናቸው እንደከዚህ ቀደሙ ኳስ ተቆጣጥሮ ባይጫወቱም ይህንን ለማድረግ በቂ ምክንያት እንደነበራቸው ጠቁመዋል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ጨዋታው መጥፎ የሚባል እንዳልነበረ ተናግረው የግብ ዕድል በመፍጠሩ ረገድ አጥጋቢ እንቅስቃሴ አለማድረጋቸውን አብራርተዋል።