ትኩረት ለቦታ እና ጊዜ

በኤልሻዳይ ቤከማ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ፐርፎርማንስ አናሊስት ኤልሻዳይ ቤከማ በእግርኳስ \’ቦታ እና ጊዜ\’ ዙሪያ ተከታዩን የግል አስተያየት አድርሶናል።

ቅርብ ጊዜ የሀገራችን የእግርኳስ መጫወቻ ሜዳ ጥራትን የሚዳስስ ፁሁፍ ላይ \”ቦታ\” እና \”ጊዜ\”ን በሚመለከት ቀጣይ የምለው እንዳለ ቃል በገባውት መሰረት የተዘጋጀ ፅሁፍ ነው፡፡ እንዴት እንደማስተካክለው አላውቅም አንጂ ሁለት ዓይነት ግብረ መልስ አግኝቻለሁ፡፡ አንደኛው \” ትንሽ በዛ \” የሚል፣ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ለማንበብ አምስት ደቂቃ የማትፈጅ የሚሉ ናቸው ፡፡ ያው ብዛት አንፃራዊ አይደል !

\"\"

እንዲያው ነገሮችን በጥቅሉ ከተመለከትን እግርኳስ ማጥቃት እና መከላከል ነው ፡፡ በማጥቃት ወቅት \”ቦታን\” እና \”ጊዜን\” መፍጠር እና መጠቀም ፣በተቃራኒው በመከላከል \”ቦታ\” እና \”ጊዜ\”ን መከልከል ናቸው ፡፡ ነገር ግን ከዚህ በዘለለ ትንሽ ገባ ብለን መፈተሸ ፣ ከተቻለም በጥልቀት ስለጉዳዩ መመርመር ጠቃሚ ነው ፡፡ በመሆኑም ዛሬ ስለጉዳዩ መጠነኛ ዳሰሳ እና አሰልጣኞች እዚህ ሀሳብ ላይ አፅንኦት ሰጥተው እንዲሰሩ ማስታወስን ያነገበ ፅሁፍ ይዤ መጥቻለሁ፡፡

በምድር ላይ ስንኖር ከስፍራ እና ጊዜ / Space and Time / ውጪ ነገሮችን ለማሳብ ይከብዳል ፡፡ በሁሉም ዘርፍ እነዚህ ጉዳዮች በስፋት እና በጥልቀት የሚመረመሩ ሀሳቦች ናቸው፡፡ ሳይንስ ላይ ፣ የጥበብ ሥራዎች ላይ ፣ በማህበረሰብ ውስጥ ፣ በታሪክ ውስጥ በሁሉም ለሁሉም መሰረታዊ ሆነው እንደየ ዘርፉ በተለያየ መንገድ ትኩረት ተሰጥቷቸው የሚፈተሹ ሀሳቦች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰዓሊ ስዕሎችን ለመሳል የ \”ቦታ\” ግንዛቤ እና \”ጊዜ\”ን ይፈልጋል፡፡ ከሁለት አንዱ ቢጎድልስ ? ስዕል የሚባል የጥበብ ሥራ አይኖርም ፣ ወይም ደግሞ አስፈላጊውን ትኩረት ባይሰጥስ ? ቀሽም ስዕል በፍሬም ውስጥ ማየታችን አይቀርም፡፡ \”ቦታ\” እና \”ጊዜ\” ግን በአግባቡ ሲዋሀዱ የዳቬንቺ ሞናሊዛ ፣ የሎሬት አፈወርቅ ተክሌ እናት ሀገር ዓይነት ውብ ሥራዎች ለማየት እንችላለን፡፡ በተመሳሳይም በእግርኳስም ልክ እንደዚሁ ነው፡፡

\”ቦታ\” እና \”ጊዜን\” በጥልቀት ተረድተን እግር ኳስን ከተጫወትን እጅግ የተሳካ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደምንችል ግልፅ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ እነዚህን ሀሳቦችን ችላ ባልን ቁጥር ለውል አልባ እና በገጠመኝ ለሚመራ እንቅስቃሴ እንዳረጋለን፡፡ እነዚህን ሁለት ሀሳቦች ነጣጥሎ ለማየት ቢያስቸግርም ጉዳዩን ለማብራራት ያህል ለይቶ ማየትን ያስፈልጋል፡፡ ምንም እንኳን ስለ አንደኛው ሀሳብ ሲነሳ ሌላኛው ብቅ ማለቱ ባይቀርም፡፡

ቦታ /Space/

ማነኛውንም ነገር ለማድረግ ቦታ እንደሚያስፈልገው ሁሉ ለእግር ኳስም በተመሳሳይ ቦታ ያስፈልጋል ፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የቦታን ዝርዝር ሀሳቦችን መመልከት ግድ ይላል ፡፡ በእግር ኳስ ቋሚ ቦታ / Static Space / እና ተለዋዋጭ ቦታ / Dynamic Space / የሚባሉ ስፍራዎች አሉ ፡፡ እነዚህን ቦታዎች በጥልቀት ማወቅ በዚህ ሞያ ላይ ለሚኖረን ቆይታ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ፡፡

ቋሚ ቦታዎች / Static Space /

ቋሚ ቦታ / Static Space / ስል አንድ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ወደ አዕምሯችሁ ከመጣ ትክክል ናችሁ፡፡ የሜዳን መጠን የሚወስነው አካል የአንድ ሜዳ ርዝመት እና ስፋት ምን መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ ለምሳሌ ለኢንተርናሽናል ጨዋታ ርዝመቱ ከ100 – 110 ሜትር፡፡ ስፋቱ ደግሞ ከ64 – 75 ብሎ አስቀምጧል፡፡ ይህ ማለት የእግርኳስ ሜዳዎች ከቦታ ቦታ የተለያየ መጠን ሊኖራቸው ይችላል እንደ ማለት ነው፡፡ ማተኮር የምፈልገው ጉዳይ የሜዳው ስፋት እና ቁመት በጨመረ እና በቀነሰ ቁጥር የምናደርገው ማስተካከያ ላይ ነው፡፡ ለምሳሌ አንድ ሜዳ ወደ ጎን መስፋቱ ከኋላ መስርቶ ለሚወጣ ቡድን በዋናነት የተሻለ ቦታ እና ጊዜን እንዲያገኝ ይረዳዋል፡፡ በተቃራኒው የሚከላከለው ቡድን በንፅፅር ሰፊ ቦታን የመከላከል ግዴታ ውስጥ ያስገባል፡፡ የሙሉ ሜዳ መጠን በራሱ እነዚህን እና መሰል ጉዳዮችን ከነካካ ሌሎች ክፍልፋዮች ደግሞ የበለጠ በእንቅስቃሴች ላይ ተፅኖ እንደሚኖራቸው መገመት አያዳግትም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ የመጫወቻ ሜዳ ውስጥ \”የቋሚ ቦታ\” አካል የሆኑ ክፍልፋዮች እንዳሉ ይታወቃል ፡፡ ሀገርን ለማስተዳደር ይመች ዘንድ በክልል ፣ በወረዳ እንደሚከፋፈለው ሁሉ በእግርኳስም ተመሳሳይ አሰራር አለ፡፡ ለዚህም ይመስለኛል ብዙ ትላልቅ አሰልጣኞች የጨዋታ ሞዴሉን ያማከለ የተብራራ መግባቢያ ሰነድ የሚመስል ክፍልፋዮች ያላቸው ፡፡ ሜዳን በዞን እና ኮሪደር / Zone and Corridor / መከፋፈል የረጅም ግዜ ተሞክሮ ሲሆን አሰልጣኞች ሀሳባቸውን የሚገልፁበት ፣ የሚያሰርፁበት ሁነኛ መግባቢያ ሆኖው እያገለገሉ ይገኛል ፡፡ ይህ ማለት እነዚህን ቦታዎች እንዲያው ያለ ትርጉም የምንከፋፍላቸው ወይም ደግሞ ከኛ በፊት በሆነ አካል ስለተከፋፈሉ እንደ ወረደ የምንጠቀማቸው አይደሉም ፡፡

\"\"

ለምሳሌ የመከላከያ ስፍራ ፣ የአማካይ ስፍራ ፣ የማጥቃያ ስፋራ / Defensive Third, Middle Third, Finishing Third / በስፋት በአሰልጣኞች ሲነገር እንሰማለን። እንደየ ስማቸው በነዛ ዞን ላይ መተግበር የታቀደውን ሥራ ለመስራት መነሻ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ልክ እንደዚሁ በስፋት የሚታወቀው ሜዳን እኩል 18 ቦታ በመክፈል ስለ እያንዳዳቸው ንዑስ ቦታዎች ከኳስ አድራሻ አንፃር የተብራራ በአሰልጣኙም በተጫዋቾችም ዘንድ በግልፅ የሚታወቅ የቋሚ ቦታዎች ክፍልፋይ ወይም የሀሳብ መስመሮች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በተመሳሳይ ጀርመኖች ሜዳን በቁመቱ 5 ቦታ በመክፈል \” Half space\” የሚባል ቦታን ለዓለም ሲያስተዋውቁ ተመልክተናል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ነገሮችን ከተለመደው አስተሳሰብ ውጪ መመልከት የማይቦዝነው አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ ቢሮ ቁጭ ብሎ በሀሳቡ ኳስ ለያዘው ልጅ ቢያንስ ሁለት የማቀበያ አማራጮች ለማግኝት እንዴት ብንቆም ? እንዴት ቦታዎችን ብንጠቀም? ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ በመፈለግ ውስጥ የራሱን ክፍልፋይ ፈጥሮ ተግባራዊ በማድረግ እግር ኳስን ከፍ አድርጎ አይተናል ፡፡ / በእኔ እምነት ከክርስቶስ ልደት በፊት እና ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደሚባለው እግር ኳስ ከጋርዲዮላ በፊት እና በኋላ መባል አለበት ብዬ አምናለሁ (ሊያከራክር ቢችልም ) / ሌሎች እጅግ ብዙ መሰል ሀሳቦች ያለ ማቋረጥ መፈጠራቸውን ስመለከት \’እኛስ ምን እያረግ ነው ?\’ እላለሁ፡፡ በቀጥታ ይሄ ጉዳይ የሚመለከታቸው ግለሰቦች እና ተቋማት ዝም ብለው ሳይ ጉዳዩ ቅርብ ጊዜ ስለመፈታቱ እርግጠኛ እንዳልሆን ያደርገኛል፡፡ መፍጠሩስ ይቅር የተፈጠሩትን በቀለለ መንገድ ተደራሽ ማድረግ እኮ አንድ እርምጃ ነው፡፡

ተለዋዋጭ ቦታ / Dynamic Space /

እግርኳስ ሁለት ቡድኖች ፣ 11 ለ 11፣ በአንድ በሚጋሩት የእግርኳስ ሜዳ ውስጥ፣ ለ90ና ደቂቃ ፣ በእጅ ሳይሆን በእግር ፣ በሁለት በሚቃረን ሀሳብ መሀል የሚደረግ ሰላማዊ ፍልሚያ ነው ፡፡ ለዚህም ነው ኳስ ከሌሎች ስፖርት አንፃር እጅግ የተወሳሰበ ስፖርት ነው የሚባለው ፡፡ በተጠቀሰው መንገድ አንድ ጨዋታ ሲደረግ የተለያዩ ቦታዎች በተለያዩ ግዜያት ይከፈታሉ ፣ ይዘጋሉ ፡፡ እነዚህ ቦታዎች ተለዋዋጭ ቦታ / Dynamic Space / በመባል ይታወቃሉ፡፡ በማጥቃት ጊዜ እንዴት ነው ሚከፈቱት ፤ የተከፈቱትን እንዴት ነው ምንጠቀመው ፣ በመከላከል ጊዜም እንዴት ነው ምንዘጋቸው የሚሉትን ሀሳቦች እንደ አሰልጣኝ በጥልቀት ተረድተን ለተጫዋቾቻችን በሚገባቸው መንገድ አቅልለን ማስረዳት ይኖርብናል ፡፡ ታላቁ ሳይንቲስት እንዲህ ብሎ ነበር።

“If you can\’t explain it simply, you don\’t understand it well enough.” አልበርት እስታይን

ለምሳሌ በማጥቃት ጊዜ በእንቅስቃሴ በሁለት የተጋጣሚ ተጫዋቾች መሀል ፣ በመስመሮች መሀል ፣ ከተከላካዮች ጀርባ ፤ እና ሌሎችም ክፍተቶች ይፈጠራሉ ፡፡ እነዚህን ክፍተቶች እንዴት እንደሚፈጠሩ እና እንዴት እንደምንጠቀማቸው የተብራራ ዕቅድ እና ታክቲክ ማዳበር ይኖርብናል፡፡ ከኋላ ስንመሰርት ሊኖረን የሚገባ ቅርፅ እና የተጋጣሚ አቀራረብ ፣ በአንድ ፣ በሁለት ፣ወይም ደግሞ በሦስት ሰው ሲጫኑን ከቦታ እና ጊዜ አጠቃቀም ጋር የተቀናጀ የመፍትሄ እርምጃዎችን በጠራ መንገድ ለተጫዋቾች ልናስተምር ይገባል፡፡ ልክ እንደዚሁ እንቅስቃሴው ሲያድግ እና የተጋጣሚ የግብ ክልል ጋር ስንደርስ ነገሮች እንዴት መከወን አለብን የሚለውን ማጥራት ይኖርብናል፡፡ ብዙን ጊዜ ተለዋዋጭ ቦታ / Dynamic Space / አይናችንን ጨፍነን ስንከፍት ተፈጥረው ወዲያው የሚጠፉ ናቸው፡፡ በመሆኑም \”ክፍተቱን\” በትክክለኛ \”ጊዜ\” መጠቀም እጅግ አስፈላጊ ነው ማለት ነው፡፡ ጎበዝ ከሆንን በጥልቀት አስበን የራሳችንን ሞዴል መፍጠር ካልሆነ ግን ጥሩ አድርገን መኮረጅ፡፡

ጊዜ /Time/

የሰው ልጅ የሚከውነው ነገር ሁሉ በጊዜ ውስጥ የታጠረ ነው ፤ እግርኳስም ልክ እንደዚሁ፡፡ እስካሁን ስለ \”ቦታ\” ባየነው ሀሳብ ውስጥ \”ጊዜ\”ን አብሮ ተሳስሮ እንዳያቹሁ አልጠራጠርም፡፡ ከዛ በተጨማሪ በግል የተጫዋቾችን ውሳኔ በጋራ እንደ ቡድን የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ከጊዜ አንፃር መመዘን ስለ ሂደቱ ሙሉ ግንዛቤ እንዲኖረን ያደርጋል፡፡ አንድ እንቅስቃሴን ነጥለን ብናወጣ እና ስለዛ እንቅስቃሴ ሙሉ መረዳት እንዲኖረን ብንፈልግ ከላይ ስለ ቦታ ያነሳናቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ልንመዝን የምንፈልገውን እንቅስቃሴ ከጊዜ አንፃር ልንቃኝው ይገባል፡፡ በአጭሩ ከእንቅስቃሴው በፊት የነበረን ሁኔታ ፣ በእንቅስቃሴው ጊዜ፣ እንዲሁም ከእንቅስቃሴው በኋላ / Before , During and After / የተፈጠሩትን ነገሮችን በመፈተሽ ለእንቅስቃሴው ከጊዜ አቅጣጫ ትርጉም መስጠት ያስፈልጋል ፡፡ ይሄ ጉዳይ ከላይ እንዳነሳሁት በሁለት መንገድ የሚፈተሽ ሲሆን አንደኛው በግለሰብ ደረጃ የነበሩ ክንውኖችን የሚመዝን ሲሆን ሌላኛው ደግሞ እንደ ቡድን ከጨዋታ ሞዴላችን አንፃር የምንፈትሸው ነው፡፡ የ\”ቦታ\” እና ጊዜ\” አጠቃቀም ጉዳይ በዚህች ፀሁፍ መጠቅለል ቢከብድም በምስል እና በቪዲዮ የተደገፈ እጅግ በቀለለ መንገድ የተዘጋጀ ሥልጠና በቅርቡ ይዤ ብቅ ስለምል በፅሁፉ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች በዚህ መርሀ ግብር ላይ ይጠራሉ፡፡

ስጠቀልለው እግር ኳስ በዋናነት የ\”ቦታን\” እና \”ጊዜ\” አጠቃቀም ነው የሚለው አዋጅ ብቻ በራሱ በቂ አይደለም፡፡ የፁሁፉ መነሻ ላይ እንዳነሳሁት በጥልቀት መመርመር አለብን፡፡ አስፈላጊውን ትኩረት፣ የትምህርት ዝግጅት እና በቂ ልምምድ እያደረግን አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ማሳያ በሜዳ ላይ የሚታየው እንቅስቃሴ ምስክር ነው፡፡ በእኔ እይታ ችግሩ እግርኳስ ላይ ብቻ ያለ አይመስለኝም ወይም ደግሞ በሁሉም ዘርፍ የተሳካን ሆነን እዚህ ስፖርት ላይ ሲደርስ በድንገት በቅሎ አይመስለኝም፡፡ በብዙ ጉዳይ ተዳክመናል አምነን በቁርጠኝነት መነሳት ነው ያለብን፡፡ መልካሙ ዜና በውስጣችን ያለው አቅም ነው። ለዛ ደግሞ አክሱም ፣ ላሊበላ፣ አድዋ ህያው ምስክሮች ናቸው ፡፡ መቼም እነዚህን ድንቅ ቅርሶች ያለ እውቀት ፣ ጥበብ ፣ እና ትብብር ሰርተናቸዋል ብዬ አላምንም፡፡ በመሆኑም እጅግ ባነሰ ትጋት ማሳካት የምንችለውን ጉዳይ እንዴት በዚህ ደረጃ እንገታገታለን ? ከዛ የአክሱም ከፍታ እንዴት በዚህ ደረጃ ልንወርድ እንችላለን ?

\"\"

ሁሉ ነገራችን የሚቀዳው ከስንፍናችን ነውና በጊዜ ነቅተን ካላስወገድነው ውድቀታችን ከደጃችን ቆማ እያንኳኳች እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡ ጨለምተኛ ሆኜ ሳይሆን በጊዜ እንድንመለስ ነው፡፡

በእኔ እይታ ከችግሩ ነፃ የሆነ አካል ለማግኝት ይቸግረኛል፡፡ ከረጅም ዓመት በፊት የሰፈር ልጆች ተሰብስበን እያወራን እስቲ ከሰፈራችን በውሸት ከአንድ እስከ ሦሰት ደረጃ እናውጣ ተባብለን አንደኛ እንትና ነው ፣ ሁለተኛ እንትና ብለን መድበን እንደጨረስን እንደ አጋጣሚ አንደኛ የወጣው ልጅ ወንድም ድንገት ከተፍ አለ ፡፡ ከማህላችን አንድ ልጅ \”ወንድምህ እኮ ከሰፈራችን በውሸት አንደኛ ወጣ ሲለው \” እንደ ልፋቱ ከሆነ ይገባዋል ብሎ ሁላችንንም አሳቀን ፡፡ እግርኳሳችን ያለበት ደረጃ እንደ ልፋታችን ከሆነ የሚገባን ነው፡፡

ሁላችንም ራሳችንን የችግሩ አካል አድርገን በጋራ የድርሻችንን ካልተወጣን በመጠቋቆም እና በመጠላለፍ የምናሳካው ድል አይኖርም፡፡ የሚሞክርን ማሸማቀቅ ፣ ጭራሽ ዝግጅቱ የሌለውን ሰው ከፍ ከፍ ማድረግ ወደ ድቅድቅ ጨለማ ኳሳችን ይወስድ ይሆናል እንጂ የምናተርፈው ነገር አይኖርም፡፡

በእነዚህ ሀሳቦች ላይ በትኩረት መስራት አለብን፡፡ አመራሮች ምቹ ከባቢ በመፍጠር ፣ አሰልጣኞች ራስን በማብቃት ፣ ተጫዋቾች ዝግጁ በመሆን ፣ ሚዲያው ከአድሎ ነፃ በመሆን ኳስ ወዳድ የሆነውን የሀገሬን ህዝብ የሚደሰትበት ቀን ለማቅረብ በጋራ እንስራ፡፡ እንደ ግለሰብ እጅግ እጅግ ውስን የሆነውን አቅማችንን በማስተሳሰር ትልቅ አቅም እንገንባ፡፡

በዚህ ጹሁፍ ለጉዳዩ የነፈግነውን ትኩረት ለማስታወስ እንጂ በበይነ መረብ ላይ ከአንድ ክሊክ ጃርባ ያለን ስለ ቦታ እና ጊዜ ትምርታዊ ዝርዝር ለማቅረብ አይደለም ፡፡