እግርኳስ ከስፖርትነት ባለፈ ለማህበራዊ አገልግሎቶች ያለውን ፋይዳ ማሳያ ይሆን ዘንድ በበጎ ምግባር ላይ ከተሰማሩ ማህበራት መካከል አንዱን ይዘንላችሁ ቀርበናል።
ኩሓ ከመቐለ መሃል ከተማ 7 ኪ.ሜ ርቃ የምትገኝ ሆና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመቐለ 7 ክፍለ ከተሞች አንድዋ ሆናለች። ኩሓ እንደ ጥበትዋና ትንሽነትዋ ሳይሆን የብዙ የእግርኳስ ተጫዋቾች መፍለቅያ ነች። በመስመር ላይ በሚያሳየው ትጋት ከሚታወቀው የቀድሞው የጉና ኮከብ ተካ ጀብጀብ እስከ ብቸኛው ከክልሉ ተገኝቶ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ኮከብ ግብ አስቆጣሪነትን በዘጠናዎቹ መጨረሻ ካሳካው መድሃንየ ታደሰ፣ ከረዥሙ አማካይ ወልዳይ ገ/ስላሴ(ክረውች) እስከ ከመቐለ 70 እንደርታ ጋር የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን የሆነው የግብ ዘብ ሶፋንያስ ሰይፈ እንዲሁም የቀድሞ የመከላከያ እና የመቐለ 70 እንደርታ አማካይ ኤፍሬም ተስፋይ(ማንዴላ) ድረስ ብዙ የኳስ ተጫዋቾችን አፍርታለች። ከተማዋ በ1980ዎቹ እንደነ ዘይትና ዱቄት፣ አውራሪስና ዞናል የመሳሰሉ በክልሉ ዝናቸው ከፍ ያለ ክለቦችም ነበሯት። ዛሬ ልናወራቹ የወደደነው ግን ስለ እግርኳስ ኮከቦቿ ሳይሆን እግርኳሱ የፈጠራቸው ተጫዋቾች በጦርነቱ ወቅት ስለሰሩት እና እየሰሩት ስላለው የህዝቡን ችግር የማቅለል ስራ ነው።
ሓይራ ኲሓ የስፖርተኞች ማሕበር በ2005 ሲጠነሰስ የአከባቢው ስፖርት እንቅስቃሴ ለማነቃቃት አልሞ ነበር የተመሰረተው። የኋላ ኋላ ግን በርካታ ማሕበረሰባዊ ድጋፎች በማድረግ እግርኳስ ከስፖርትነት ባለፈ ትርጉም እንዳለው አስመስክሯል።በተለይም በጦርነቱ ወቅት ከአንድ ዓመት ገደማ በላይ ለሚሆን ጊዜ የሚላስ የሚቀመስ ላጡ 300 የተቸገሩ ታዳጊዎች ዕለታዊ የምገባ ፕሮግራም ለ100 ህፃናት ደግሞ ወርሀዊ የገንዘብ ድጎማ በማድረግ አለኝታነቱን አሳይቷል።
ተቋሙ ከዛ በፊትም ማለትም በየካቲት 2011 ህጋዊ እውቅና አግኝቶ መንቀሳቀስ ከመጀመሩ በፊት በበዓላት ወቅት የተቸገሩ ቤተሰቦችን በመርዳት ፤ ኮሮና ከተከሰተ በኋላ ደግሞ በስድስት ዙሮች ለአቅመ ደካሞች የተለያዩ ገንዘባዊ እና ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግ ተንቀሳቅሷል። በአንድ ወቅት ለተፈናቃይ ወገኖች ያደረጉት የፍራሽ እና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሁም የአንበጣ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ያበረከቱት አስተዋፅዖም የሚነሳ ነው።
ከላይ በተጠቀሰው ዓመት ከጨዋታ በኋላ በስፖርተኞቹ የተጠነሰሰው ይህ ተቋም በአሁን ወቅት በተጨማሪ ሌሎች የማሕበረሰቡ አካላትም የተቋሙ አባላት በማድረግ እና በማስተባበር የተለያዩ ድጋፎች በማድረድ ላይ ይገኛል። ተቋሙ የህፃናት እና አረጋውያን መርጃ ማዕከል ማቋቋምም የረዥም ጊዜ ዕቅዱ አካል አድርጎ እየተንቀሳቀሰም ይገኛል።
ማሕበሩ ከማሕበረሰባዊ ድጋፎች በተጨማሪም በፌደራል ዳኛ ጥዑማይ ካሕሱ እና በቀድሞ ተጫዋች ኃይልሽ ገ\\ስላሴ የሚሰለጥኑ ሁለት የህፃናት ቡድኖች በማቋቋም በታዳጊ እና ህፃናት እግርኳስ ፕሮጀክት በመንቀሳቀስ ላይ ሲገኝ በአካባቢው አንድ ትልቅ ክለብ የመመስረት ዓላማ አንግቦ እየሰራም ይገኛል።
በሀገራችን በተለያዩ ክፍሎች ዘርፈ ብዙ በሆኑ ችግሮች ምክንያት በርካታ ወገኖቻችን በችግር ውስጥ ይገኛሉ። በደጉ ጊዜ ስታድየም ተገኝቶ የሚወደውን ክለብ እና ሀገሩን የሚደግፈው ለእግርኳስ ፅኑ ፍቅር ያለው ይህ ህብረተሰብ በመሰል ከባድ ወቅቶች ላይ እገዛ እንደሚያስፈልገው ዕሙን ነው። ይህንን ለማድረግም በእግርኳስ ውስጥ ያለፉ ባለድርሻ አካላት በየአካባቢው ተደራጅተው የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ቢያደርጉ እግርኳስ ከስፖርትም በላይ የሆነ ኃይል እንዳለው ማሳያ እንደሚሆኑ ዕምነታችን ነው። በዚህም በተመሳሳይ በጎ ምግባር ላይ የተሰማሩ ማሕበራትን ለማስተናገድ በራችን ክፍት መሆኑን እንገልፃለን።