በ19ኛው የጨዋታ ሳምንት በተደረጉ ጨዋታዎች መነሻነት የሳምንቱን ምርጥ 11 እና አሰልጣኝን እንደሚከተለው መርጠናል።
አሰላለፍ – 4-3-3
ግብ ጠባቂ
ፔፔ ሰይዶ – ሀዲያ ሆሳዕና
ነብሮቹ አዞዎቹን ሲረቱ በቀጥተኛ አጨዋወት ይሰነዘሩበት የነበሩ ኳሶችን በማስቀረት ለቡድኑ ሦስት ነጥብ መገኘት ትልቁን ድርሻ የተወጣው ሴኔጋላዊው ግብ ጠባቂ በተለይ ጨዋታው ሊገባደድ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ የተመስገን ደረሰን ኳስ ያወጣበት መንገድ በእጅጉ ድንቅ አስብሎታል።
ተከላካዮች
ብርሀኑ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
ተጫዋቹ ለሀድያ ሆሳዕና ወሳኝ ድል መገኘት ከመከላከል ሚናው በይበልጥ ወደ ፊት በመሳብ በቡድኑ የማጥቃት ሂደት ላይ ተሳታፊ ነበር። በዚህም ለቡድኑ ሙከራዎች ኳሶቹ መነሻ የነበሩ ሲሆን ፍቅረየሱስ የመጀመሪያውን ጎል ሲያስቆጥር አመቻችቶ በማቀበሉ በስብስባችን አካተነዋል።
ከድር ኩሊባሊ – ፋሲል ከነማ
ፋሲል መቻልን ሲረታ ከወትሮው በተለየ አቀራረብ ወደ ሜዳ የገባ ሲሆን ኩሊባሊም የስድስት ቁጥር ሚና ነበረው ፤ እኛ ደግሞ በተፈጥሯዊ ቦታው ላይ ተጠቅመነዋል። በዚህም መሀል ሜዳ ላይ ቡድኑ በአካላዊ ፍልሚያዎች የበላይ እንዲሆን እንዲሁም ተጋጣሚ ወደ አደገኛ ዞን ሳያልፍ ኳስ አቋርጦ ፈጣን ጥቃቶችን እንዲጀምር በማድረግ ረገድ የተጫዋቹ የዕለቱ ብቃት አስፈላጊ ነበር።
ራምኬል ጀምስ – ኢትዮጵያ ቡና
ቁመታሙ ተከላካይ ቡድኑ ከሲዳማ ቡና ጋር ነጥብ ሲጋራ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ያሳየው ብቃት ጥሩ ነበር። በጨዋታው በዐየርም ሆነ በምድር ላይ ፍልሚያዎች ቀዳሚ ሲሆን የታየው ራምኬል በተለይ አደገኛ ኳሶችን በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ ሸርተቴዎች ሲያመክናቸው የነበሩ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች በቦታው እንድንመርጠው አድርጎናል።
ፍራኦል መንግሥቱ – ባህር ዳር ከተማ
ያለፉትን ሦስት ጨዋታዎች በቋሚነት በመሰለፍ ጥሩ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረው የግራ መስመር ተከላካዩ ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ሲረታ የመክፈቻዋን ጎል አመቻችቶ አቀብሏል። በጥሩ መታተር በማጥቃትም ሆነ በመከላከል ሲጫወት የነበረው ፍራኦል በተለይ ደግሞ ከመስመር የሚያሻማቸው ዒላማቸውን የጠበቁ ኳሶች ተመራጭ አድርጎታል።
አማካዮች
ናትናኤል ዘለቀ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
የፈረሰኞቹ አማካይ ናትናኤል ቡድኑ በፈታኙ የአዳማ ጨዋታ የተሻለ እንዲንቀሳቀስ የበኩሉን ሲጥር አስተውለናል። በእርጋታ ውስጥ ሆኖ ኳሶችን የሚያደራጀው ተጫዋቹ በመከላከል ቅርፅም ለተከላካዮቹ የሚሰጠው ሽፋን ጥሩ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ለቡድኑ ዕድገት የነበረው አበርክቶም ቀላል የሚባል አልነበረም።
የጦና ንቦቹ ድንቅ በነበረው ጨዋታ ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ ሲጋሩ አማካይ ክፍላቸው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ የመድንን የመሀል ሜዳ መቆጣጠር ችሎ ነበር። በዚህ ሂደት አንድ ግብ አመቻችቶ ያቀበለው አበባየሁ በ\’ሀብታሙ ንጋቱ\’ ሽፋን በመታገዝ በሽግግሮች ወቅት የነበረው ታታሪነት ለቡድኑ ነጥብ መጋራት ጥሩ አስተዋፅዖ አድርጓል።
ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ሀዲያ ሆሳዕና
የሀድያ ሆሳዕና አማካይ ክፍል በአርባምንጭ ላይ ብልጫን ለመውሰዱ የፍቅረየሱስ ሁለገብ መሆን ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው። በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅት ኳስ በማስጣሉም ሆነ አጠገቡ ከተሰለፉ ተጫዋቾች ጋር ጥሩ ጥምረት ከመፍጠሩ በዘለለ ብርሀኑ በቀለ የሰጠውን ኳስ ወደ ጎልነት ለውጦ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።
አጥቂዎች
ዱሬሳ ሹቢሳ – ባህር ዳር ከተማ
በዚህ የውድድር ዓመት ድንቅ እንቅስቃሴ በማሳየት የጣናው ሞገድ ቁልፍ ተጫዋቾች የሆነው ዱሬሳ ድሬዳዋን ሲረቱ በቡድኑ ፈጣን ሽግግር ወሳኝ ሚና ነበረው። በጨዋታው የመስመር አጥቂው አንድ ግብ አስቆጥሮ አንድ ለግብ የሆነ ኳስ በማቀበሉ በሳምንቱ ምርጥ ቡድን ውስጥ ተካቷል።
ብሩክ መሉጌታ – ኢትዮጵያ መድን
ኢትዮጵያ መድን ከወላይታ ድቻ ጋር ብርቱ ፉክክር ባደረገበት ጨዋታ ከመስመር የሚነሳው ብሩክ ወደ ኋላ ተመልሶ ቡድኑ የቁጥር የበላይነት እንዳይፈጠርበት ለማድረግ ከነበረው ተነሳሽነት ባለፈ በዋነኛ ሚናው በጥሩ አጨራረስ ሁለት ግቦችን አስቆጥሮ መድን ነጥብ ተጋርቶ እንዲወጣ የአንበሳውን ድርሻ ተወጥቷል።
ሀብታሙ ታደሰ – ባህር ዳር ከተማ
በፈጣኑ የጣና ሞገዶች የማጥቃት አጨዋወት ጉልህ ድርሻ ካላቸው ተጫዋቾች ውስጥ አንዱ የሆነው ሀብታሙ ታደሰ ቡድኑ ድሬዳዋ ከተማን ስያሸንፍ በመጀመርያው አጋማሽ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። በቁጥሮች እንዲሁም በእንቅስቃሴ ረገድ ጥሩ የነበረው ይህ ተጫዋች አበርክቶው በምርጥ 11 ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።
አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ
በዚህ ውድድር ዓመት በፈጣን ሽግግር የተመሰረተ ስል አጨዋወት ይዘው የቀረቡት አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው በሳምንቱ ቡድናቸው ያሳየው እንቅስቃሴ ምርጥ አሰልጣኝ የምያሰኛቸው ነበር። በአመዘኙ ፈጣን የመስመር አጨዋወት ላይ ተመስርተው በገቡበት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ያሸነፉበት መንገድ ለተከታታይ ሁለተኛ ሳምንት ምርጥ አሰልጣኝ አሰኝቷቸዋል።
ተጠባባቂዎች
መሐመድ ሙንታሪ – ሀዋሳ ከተማ
መናፍ ዐወል – ፋሲል ከነማ
ሄኖክ አርፌጮ – ሀዲያ ሆሳዕና
ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – ፋሲል ከነማ
ፀጋዬ ብርሃኑ – ሀዲያ ሆሳዕና
ኢስማኦል ኦሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ቃልኪዳን ዘላለም – ወላይታ ድቻ