የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ23ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጀመር አዲስ አበባ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ድል ተቀዳጅተዋል።

\"\"

ድሬዳዋ ከተማ 0-2 አዲስአበባ ከተማ

04፡00 ላይ በተደረገው የሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር ድሬዳዋ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ሲገናኙ በሚቆራረጡ ቅብብሎች በታጀበው እና ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት እና የግብ ዕድሎችም ያልተፈጠሩበት ነበር። በአጋማሹ መጠናቀቂያ ላይ በአዲስ አበባዎች በኩል የተፈጠረው ብቸኛ የጠራ የግብ ዕድልም ግብ ሆኗል። አሥራት ዓለሙ ያሻገረችላትን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ ሆና ያገኘችው ኪፍያ አብዱልራህማን በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፋዋለች።

ከዕረፍት መልስ ድሬዳዋ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ሙሉ ብልጫ በመውሰድ በርካታ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ 59ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ በገባችው ፎዚያ መሐመድ የመጀመሪያውን ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ 76ኛው ደቂቃ ላይ ወርቅነሽ ሚልሜላ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዛው ገብታ ወደ ውስጥ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘችው ትዝታ ፈጠነ ያደረገችው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫ የተወሰደባቸው አዲስ አበባዎች በአጋማሹ የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድል 90ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ አሥራት ዓለሙ እና ሰርካዲስ ጉታ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም ኪፍያ ኢብራሂም ግሩም ሙከራ ብታደርግበትም የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። የአቻነት ግብ ፍለጋ በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ድሬዎች 93ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ቢቃረቡም ሊዲያ ጌትነት ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ በሰኮንዶች ልዩነት በጨዋታው ኮከብ የነበረችው ኪፍያ ኢብራሂም በግሩም ዕይታ ያቀበለቻትን ኳስ ሌላኛዋ የቡድን አጋሯ አሥራት ዓለሙ አስቆጥራዋለች። ጨዋታውም በአዲስ አበባ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ 2-0 ቦሌ ክ/ከተማ

ከምሳ መልስ 08፡00 ላይ በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው መድረስ የቻሉት ሀዋሳዎች በዙፋን ደፈርሻ እና በፀሐይነሽ ጅላ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ሲያደርጉ 23ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግቧንም ረድዔት አስረሳኸኝ የቦሌ ተከላካዮችን ትኩረት ማጣት ተጠቅማ ኳሱን አቋርጣ በማግኘት በተረጋጋ አጨራረስ ማስቆጠር ችላለች። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተለይም በግራው የማጥቂያ መስመር አልፎ አልፎ  በሚያደርጉት ማራኪ ቅብብል ከተመልካች አድናቆት የተቸራቸው ቦሌዎች የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው አጋማሹን አገባደዋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 65ኛው ደቂቃ ላይ ምሕረት መለሰ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ እሙሽ ዳንኤል ሳታገኘው ቀርታ የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ስትቀር 76ኛው ደቂቃ ላይ ከቱሪስት ለማ የተነሳው እና የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ የተመለሰውን ኳስ ከጥቂት ንክኪዎች በኋላ ያገኘችው ፀሐይነሽ ጅላ ከሳጥን አጠገብ ድንቅ ግብ አደርጋዋለች። ከግቧ መቆጠር በኋላም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ሳይደረግበት ጨዋታው በሀዋሳ ከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ 0-3 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

10፡00 ሲል የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ ጊዮርጊሶች በተለይም በቀኙ የሜዳ ክፍል ስኬታማ ቅብብሎችን በማብዛት እና ዝግ ባለ የማጥቃት ሂደት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ 38ኛው ደቂቃ ላይ ዐይናለም ዓለማየሁ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ከሞከረችው እና የግቡን አግዳሚ ታክኮ ከወጣው ኳስ ውጪ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲቸገሩ በኝቦኝ የን ሁለት እና በሎዛ አበራ አንድ ፈታኝ ያልሆነ የረጅም ርቀት ሙከራ ማድረግ የቻሉት ንግድ ባንኮች 39ኛው ደቂቃ ላይ በሎዛ አበራ ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል የተሻማውን እና ኳስ ሎዛ አበራ በግንባሯ የጨረፈችውን ኳስ ያገኘችው አረጋሽ ካልሳ አስቆጥራው ንግድ ባንክ አጋማሹን 2-0 መርቶ እንዲወጣ አስችላለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ ለተመልካች አሰልቺ ሆኖ ሲቀጥል 56ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው የንግድ ባንኳ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ከሳጥን አጠገብ ወደ ግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን የመለሰችባት ኳስ በአጋማሹ የተሻለው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ ነበር። የጨዋታው የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች በአንጻራዊነት ጥሩ እንቅስቃሴ ሲደረግባቸው 85ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ወደግብ የሞከረችው ኳስ በፍቅርአዲስ ገዛኸኝ ተጨርፎ አቅጣጫ ቢቀይርም ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን ስትይዘው 87ኛው ደቂቃ ላይ የምሥራች ላቀው ተቀይራ በገባችበት ቅፅበት ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥራ የግቡን ልዩነት ወደ ሦስት ስታሳድግ ንግድ ባንኮች በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ በመሳይ ተመስገን እና በሎዛ አበራ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ሆኖም ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"