ከፍተኛ ሊግ | የ20ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ጨዋታዎች ዛሬ በሦስቱ አዘጋጅ ከተሞች ቀጥለው በምድብ \’ሀ\’ እና \’ለ\’ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ሻሸመኔ ከተማ በመሪነታቸው ሲቀጥሉ በምድብ \’ሐ\’ ከሀምበርቾ ዱራሜ ቀድሞ የተጫወተው ገላን ከተማ ወደ አንደኝነት መጥቷል።

በቴዎድሮስ ታከለ እና ጫላ አቤ

ምድብ ሀ

አሰላ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የከፍተኛ ሊጉ የምድብ ሀ ውድድር ዛሬ አራት ጨዋታዎች ተስታናግደውበታል።

\"\"

ምድቡን አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው የሚመሩት ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቤንች ማጂ ቡና ጨዋታቸውን የሚያደርጉበት ዕለት በመሆኑም ከፍ ያለ ግምትን ያገኘ የጨዋታ ቀን ነበር። በውጤቱም ሁለቱ መሪዎች ድል ሊቀናቸው ችሏል። መሪው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ላለመውረድ እየታገለ የሚገኘው ሰበታ ከተማን በኪሩቤል ወንድሙ እና አቤል ሀብታሙ ጎሎች 2-0 መርታት ችሏል። ውጤቱን ተከትሎ ንግድ ባንክ ነጥቡን 44 ማድረስ የቻለ ሲሆን ከተከታዩ ያለውን የአንድ ነጥብ ልዩነት በማስጠበቅ መሪነቱን አስቀጥሏል።

\"\"

ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ቤንች ማጂ ቡና እንደንግድ ባንክ ሁሉ የ2-0 ድልን ማሳካት ችሏል። በዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ቡታጅራ ከተማን የገጠመው ቡድኑ ኤፍሬም ታምሩ እና ዘላለም በየነ ከመረብ ባገናኟቸው ጎሎች ነበር ወደ 43 ነጥብ ከፍ ያለበትን ውጤት ማስመዝገብ የቻለው። በተቀሩት ሁለት ጨዋታዎች ማለዳ ላይ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ጋሞ ጨንቻ እንዲሁ ባቱ ከተማን 2-0 ረቷል። ጎሎቹን ደሳለኝ አሎ እና የባቱው ይድነቅ የሺጥላ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል። በቀሪው የዕለቱ ጨዋታ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ዱራሜ ከተማ በካፎ ካስትሮ ብቸኛ ጎል አቃቂ ቃሊቲን 1-0 ረቷል።

\"\"

ምድብ ለ

ሀዋሳ ላይ እየተከናወነ በሚገኘው የምድብ ለ ውድድር በበርካታ ደጋፊዎች መካከል ታጅቦ የተደረገው እና ጠንካራ ፉክክርን ያስተናገደው ጨዋታ በመጨረሻም ሻሸመኔ ከተማን አሸናፊ አድርጓል። የዕለቱ ቀዳሚ በነበረው የሻሸመኔ እና ይርጋጨፌ ቡና ጨዋታ በሜዳ ላይ በእጅጉ ማራኪ የሆኑ እንቅስቃሴዎች እና የሁለቱን ቡድኖች የመሸናነፍ ስሜት አሳይቶን የተጠናቀቀ ነበር።

ይርጋጨፌ ቡናዎች ከወትሮ እንቅስቃሴያቸው ተሻሽለው ተጋጣሚዎቹን ሲፈትኑ ውለዋል ይሁን እንጂ በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው ወደ ሜዳ በመመለስ ፈጣን የመልሶ ማጥቃትን የተጠቀሙት ሻሸመኔዎች 79ኛው ደቂቃ ላይ በተከላካዮች ስህተት አሸናፊ ጥሩነህ ግብ አስቆጥሮ ሻሸመኔን ቀዳሚ አድርጓል።

\"\"

በደጋፊዎቻቸው ታግዘው ጫናዎችን በወጥነት ያሳደሩት ሻሸመኔዎች ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ በአብዱልከሪም ቃሲም ሁለተኛ ጎልን አክለው ጨዋታው በሻሸመኔ 2-0 አሸናፊነት ተቋጭቷል። ቡድኑ ምድቡን ያለ ተፎካካሪ በሰፊ የነጥብ ልዩነት መምራቱን አጠናክሮ ቀጥሏል።

ከቀትር በኋላ 8 ሰዓት ሲል ካፋ ቡና እና ንብን ያገናኘው መርሀግብር ካፋን ሦስት ነጥብ አስገኝቶ ተጠናቋል። የንቦችን የጨዋታም ሆነ የሙከራ የበላይነትን ባስመለከተን ጨዋታ ካፋዎች ባደረጉት ፈጣን የሽግግር ጨዋታ በተከላካይ ስህተት የተገኘችን ዕድል እያሱ ፍሬው ከዕረፍት በፊት ብቸኛ የድል ጎልን አስቆጥሮ ካፋን ባለ ድል አድርጓል።

\"\"

10 ሰዓት ሲል አምቦ ከተማ እና የመዲናይቱን ክለብ ጉለሌ ክፍለ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ አምቦ ከተማን ሳይጠበቅ 3ለ1 አሸናፊ ያደረገ ውጤት ተመዝግቦበታል። በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ሚልኪ ዘለቀ እና ነቢል አብዱልሰላም አስቆጥረው ወደ መልበሻ ጨዋታው ሲያመራ ከዕረፍት መልስ ነቢል አብዱልሰላም ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎልን ሲያክል ጁንዴክስ አወቀ ጉለሌን ከሽንፈት ያልታደገች ብቸኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በአምቦ 3ለ1 ድል ተደምድሟል።

\"\"

ምድብ ሐ

ባቱ ላይ እየተከናወነ በሚገኘው የምድብ ሐ ውድድር ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ የነበረው ገላን ከተማ ኮልፌ ክፍለ ከተማን ገጥሞ በጨዋታው ማብቂያ ግድም በተቆጠሩ ጎሎች ድል ማድረግ ችሏል። 72ኛው ደቂቃ ላይ የኮልፌው ዉብሸት ዓለማየሁ በራሱ ላይ ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ የሆኑት ገላኖች 90ኛው ደቂቃ በበየነ ባንጃ ተጨማሪ ጎል አክለው 2-0 አሸንፈዋል። በዚህ ውጤት መሰረት ቡድኑ ነጥቡን 36 በማድረስ ነገ ጨዋታውን የሚያደርገው ሀምበርቾ ዱራሜን በአንድ ነጥብ በልጦ በአንደኝነት ተቀምጧል። በሌሎች ጨዋታዎች ዳሞት ከተማ እና ቡራዩ ከተማ ያለግብ ሲለያዩ ደሴ ከተማ በማናዬ ፋንቱ ብቸኛ ጎል ነገሌ አርሲን 1-0 ረቷል።

\"\"