የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ23ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

ዛሬ በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት  ልደታ ክ/ከተማ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ድል ሲቀናቸው ይርጋጨፌ ቡናን ከአርባምንጭ ከተማ ጋር ያገናኘው ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።

ልደታ ክ/ከተማ 2-0 ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ

ረፋድ 04፡00 ላይ በተደረገው የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ መሃል ሜዳው ላይ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ቢደረግበትም አንድም  ለግብ የቀረበ ሙከራ ሳይደረግበት ተጠናቋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል እየተሻሻለ ሲሄድ 51ኛው ደቂቃ ላይ የንፋስ ስልኳ ዮርዳኖስ በርሔ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ስትወገድ የተጫዋች ቁጥር ብልጫ ያገኙት ልደታዎች 53ኛው እና 56ኛው ላይ በመዐዛ አብደላ የቅጣት ምቶች ለግብ የቀረበ ሙከራ ሲያደርጉ 57ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አለሚቱ ድሪባ በቀኝ  መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ንጋት ጌታቸው በእግሯ አስቆጥራዋለች። በአጋማሹ ብልጫውን የወሰዱት ልደታዎች 77ኛው ደቂቃ ላይ ግን መሪነታቸው ላይ ውሃ ለመቸለስ ተቃርበው ነበር። በቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ  ተቀይራ የገባችው ዘነበች ለማስወጣት ስትሞክር  ኳሱ አቅጣጫውን ቀይሮ ራሷ መረብ ላይ ሊያርፍ በቀኙ የግቡ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል። ሆኖም 90ኛው ደቂቃ ላይ ህድዓት ካሱ ድንቅ በሆነ ሩጫ ግብ ጠባቂ በማለፍ ተጨማሪ ግብ አስቆጥራ ልደታን የ 2-0 ድል አቀዳጅታለች።

\"\"

መቻል 0-1 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

08፡00 ላይ የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ በመቻል እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ሲደረግ ለተመልካች ማራኪ የሆነ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያው የጠራ ዕድል 14ኛው ደቂቃ ላይ በመቻሎች ሲፈጠር ምርቃት ፈለቀ ከራሷ የሜዳ ክፍል በተሻገረላት ኳስ ከግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ ጋር ብትገናኝም ንቁ የነበረችው ማርታ በፍጥነት ወደ ሳጥኑ ጫፍ በመጠጋት አምክናባታለች። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በአንጻሩ 23ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መሰሉ አበራ በቀኝ መስመር ከረጅም ርቀት ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገችው ሙከራ የግብ ጠባቂዋን አበባየሁ ጣሰው እጅ ጥሶ መረቡ ላይ አርፏል።

\"\"

ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የቻሉት ኤሌክትሪኮች 28ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሽታዬ ሲሣይ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆና ወደ ውስጥ ያሻገረችላትን ኳስ ያገኘችው ምንትዋብ ዮሐንስ ያደረገችውን ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶባታል። የመቻል የማጥቃት እንቅስቃሴዎች መነሻ የሆነችው ምርቃት ፈለቀ 33ኛው ደቂቃ ላይ በርካታ ተጫዋቾችን በግሩም ክህሎት አታልላ በማለፍ ያደረገችውን ሙከራ ግብጠባቂዋ ማርታ ስትመልስባት ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን ኤሌክትሪኮች 39ኛው እና 41ኛው ደቂቃ ላይ እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።  በቅድሚያም መሰሉ አበራ ከረጅም ርቀት አክርራ የመታችው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ በቀጣይም ሽታዬ ሲሣይ ሳጥን ውስጥ ባስገባችው ኳስ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ አበባየሁ ጣሰው ስትመልስባት ያንኑ ኳስ ያገኘችው ትንቢት ሳሙኤል ወደኋላ በመመለስ ለምንትዋብ ዮሐንስ ስታቀብል ምንትዋብ ያደረገችው ሙከራ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ተመልሷል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ መቻሎች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ የተሻለ መንቀሳቀስ ሲችሉ 60ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ምስር ኢብራሂም ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆና ያደረገችው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ሲወጣባት በሴኮንዶች ልዩነት ነጻነት ፀጋዬ ከግራ መስመር ያሻማችውን ኳስ ያገኘችው ሴናፍ ዋቁማ በግንባሯ በመግጨት ግሩም ሙከራ ብታደርግም የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። በተጨማሪም 74ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ቤዛዊት ተስፋዬ ሙከራ አድርጋ ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ መልሳባታለች። ሆኖም ጨዋታው በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ይርጋጨፌ ቡና 0-0 አርባምንጭ ከተማ

10፡00 ላይ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር ይርጋጨፌ ቡናን ከአርባምንጭ ከተማ ሲያገናኝ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ የግብ ዕድሎች አይፈጠሩበት እንጂ ጥሩ እንቅስቃሴ የተደረገበት ነበር። በአርባምንጭ ከተማ በኩል 29ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ታምሩ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ ያገኘችው ትዕግስት አዳነ ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ ብታደርግበትም የግቡን የላይ አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስባት በይርጋጨፌዎች በኩል 35ኛው ደቂቃ ላይ አምበሏ ትርሲት መገርሣ ከሳጥን ውጫ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ትዕግስት አበራ መልሳባታለች።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ አርባምንጮች በቁጥር በዝተው ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ተጭነው ቢጫወቱም የይርጋጨፌን የመከላከል አደረጃጀት ጥሰው ገብተው የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል። ቤተልሔም ታምሩ 73ኛው ፣ 77ኛው እና 89ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት ያደረገቻቸውን ሙከራዎች ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ ስትመልሳቸው  በይርጋጨፌዎች በኩል 74ኛው ደቂቃ ላይ አበራሽ አበበ ከቀኝ መስመር በተሻገረላት ኳስ በግንባሯ በመግጨት ያደረገችው ሙከራ ብቻ ተጠቃሽ ነበር። ሆኖም ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።