ግሩም ጎሎች በተስተናገዱበት ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ለገጣፎ ለገዳዲን 3-1 አሸንፏል።
የሊጉን ዋንጫ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ለማንሳት ብርቱ ፉክክር እያደረጉ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ባሳለፍነው ሳምንት ድሬደዋ ከተማን ከረቱበት ስብስባቸው አደም አባስን በፋሲል አስማማው ብቻ በመቀየር ወደ ጨዋታ ሲገቡ ለከርሞ በሊጉ የመቆየታቸውን ጉዳይ ጥያቄ ምልዕክት ውስጥ ያስገቡት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በበኩላቸው ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ነጥብ ተጋርተው በወጡበት ጨዋታ የተጠቀሙባቸውን በረከት ተሰማ፣ መዝገበ ቶላ፣ ፍቅሩ አለማየሁ፣ አስናቀ ተስፋዬ፣ አማኑኤል አረቦ እና ሱሌማን ትራውሬን በሱራፌል ዐወል፣ አቤል አየለ፣ ያሬድ ሀሰን፣ ተስፋዬ ነጋሽ ኢብሳ በፍቃዱ እና ካርሎስ ዳምጠውን በመተካት ገብተዋል።
ኳሱን ተቆጣጥረው በሁሉም የሜዳ ክፍል ብልጫ በመውሰድ ክፍተቶችን በመፈለግ ዕድሎችን ለመፍጠር በትዕግስት ሲጫወቱ የቆዮት ባህር ዳሮች የጠራ የጎል ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ቆይተዋል። ለገጣፎዎች በበኩላቸው ባህር ዳር ከተማዎች የሚያደርጓቸውን ቅብብሎሽን በማቋረጥ በመልሶ ማጥቃት ሽግግር አደጋ ለመፍጠር ቢያስቡም በቁጥር አንሰው ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ይደርሱ የነበረ በመሆኑ ስኬታማ አልነበሩም።
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ ሄዶ በሁለቱም በኩል የሚደረገው እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ እያለ ቢሄድም ባህር ዳሮች በለገጣፎ የሜዳ ክፍሎች በቁጥር በዝተው በተለይ በቀኝ መስመሩ ያደላ ጥቃት መሰንዘራቸውን ቀጥለው በ33ኛው ደቂቃ ነበር የመጀመርያውን እጅግ ለጎል የቀረበ ሙከራዎችን ያገኙት። ፍራኦል መንግስቱ ከግራ መስመር ከሳጥን ውጭ በጠንካራ ምቱ የመታውን ኳስ የለገጣፎ ግብጠባቂ ሚኪያስ እንደምንም የያዘው አጋጣሚ ነበር።
ሆኖም ብዙም ሳይቆዮ ባህር ዳሮች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ በ41ኛው ደቂቃ የመጀመርያ ጎላቸውን አግኝተዋል። ፉአድ ፈረጃ ከመአዘን ምት ያሻገረውን ኳስ ረጅም ወራት በጉዳት ከሜዳ እርቆ የቆየው ፋሲል አስማማው በግንባሩ በመግጨት ጎሉን አስገኝቷል። የፋሲል አስማማው ጎል ከተቆጠረ በኋላ የጨዋታው ሂደት ፈጠን ወዳለ እንቅስቃሴ ተቀይሮ የጦና ሞገዶቹን ተጨማሪ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል በዱሬሳ ሹቢሳ ከሳጥን ውጭ በጥሩ ሁኔታ ቢሞከርም የግቡ አግዳሚ ጎል እንዳይሆን አድርጎባቸዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመርያ አጋማሽ ሁሉ በተመሳሳይ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የገቡት ባህር ዳሮች በ52ኛው ደቂቃ ከአለልኝ አዘነ የተሻገረውን ፉአድ በግንባሩ ጨርፎ ያቀበለውን በሀብታሙ ታደሰ ወደ ጎል ቢመታውም ሚኪያስ ዶጂ ጎል እንዳይሆን አግዶባቸዋል። በአንፃራዊነት ከሀብታሙ ታደሰ ሙከራ በኋላ ለገጣፎዎች ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥረት ቢያደርጉም በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ሁለት ግሩም ጎሎች ለማስተናገድ ተገደዋል።
68ኛው ደቂቃ አለልኝ አዘነ ከዱሬሳ ሹቤሳ የተቀበለውን ኳስ ከረዥም ርቀት ድንቅ ሁለተኛ ጎል ሲያደርገው በ71ኛው ደቂቃ ደግሞ የአብስራ ተስፋዬ ከግራ ጠርዝ ከሳጥን ውጭ የተገኘውን ቅጣት ምት በጥሩ አጨራረስ ወደ ጎልነት በመቀየር የቡድኑን የጎል መጠን ወደ ሦስት ከፍ አድርጎታል። በቀሩት ደቂቃዎች በተዝናኖት ብልጫ ወስደው ተጨማሪ ጎል ፍለጋ መጫወት የቻሉት የጣና ሞገዶቹ በሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት ሌላ ጎል መሆን የሚችል እድል ቢፈጥሩም የጎል መጠኑ ከዚህ በላይ እንዳይሆን ሚኪያስ ዶጂ አድኖታል። የዳኛው ፊሽካ ሲጠበቅ ጋብሬል አህመድ የለገጣፎ ለገዳዲን የማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 3-1 ተጠናቋል። በውጤቱም ባህር ዳሮች ከመሪው በኩል ነጥብ ተቀምጠው ሁለተኛ ደረጃ ሲይዙ ለገጣፎዎች ባሉበት የደረጃ ሠንጠረዡ ግርጌ ለመቀመጥ ተገደዋል።
አሰልጣኝ ደጋረጋል ይግዛው ማሸነፋቸው ለቡድናቸው አስፈላጊ በመሆኑ በጥንቃቄ ተጫውተው ማሸነፍ በመቻላቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው። ከምንም በላይ ተጫዋቾቻቸው በትዕግስት የመከላከሉን አጥር ለማስከፈት ያደረጉትን ጥረትም አድንቀዋል። አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ይዘውት የመጡት እቅድ በጥሩ መንገድ ቢሄድም በቀላሉ ጎል መቆጠሩ ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረው በቀጣይ ከባድ ጊዜ እንደሚጠብቃቸው እና ባለቸው አቅም በሊጉ ለመቆየት ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።