ከፍተኛ ሊግ | የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች

ዛሬ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ \’ሀ\’ እና \’ሐ\’ ጨዋታዎች ሲከናወኑ ወልዲያ ልዩነቱን ያጠበበትን ሀምበርቾ ደግሞ መሪነቱ ማስመለስ ያልቻለበትን ውጤት አስመዝግበዋል።

በጫላ አቤ

ምድብ ሀ

አሰላ ላይ በምድብ ሀ ሰንዳፋ በኬን የገጠመው ወልዲያ 3-1 አሸንፏል። በመጀመሪያው አጋማሽ በበድሩ ኑርሁሴኔን ሁለት እና በቢኒያም ላንቃሞ እንድ ጎል መሪ የሆነው ወልዲያ ሰንዳፋዎች በኤርሚያስ ብርሀኑ ጎል ውጤቱን ቢያጠቡበትም በሁለተኛው አጋማሽ በ3-1 ውጤት እንዲያልቅ ማድረግ ችሏል። በዚህም 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወልዲያ ከመሪው ንግድ ባንክ ጋር ያለውን ልዩነት ወደ ሦስት በመመለስ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመመለስ ፍልሚያውን ቀጥሎበታል። በሌሎች የምድቡ ጨዋታዎች አዲስ ከተማ ክ/ከ እና ጅማ አባ ቡና 2-2 ሲለያዩ ሀላባ ከተማ ወሎ ኮምቦልቻን 1-0 ረቷል።

\"\"

ምድብ ሐ

ሀምበሪቾ ዱራሜ 0-0 ሶዶ ከተማ

ሀምበሪቾ ዱራሜ ከጨዋታው መጀመር አንስቶ ኳስን ከተከላካይ መስርቶ በጥሩ ፍሰት ከኳስ ብልጫ ጋር ወደ ግብ ለመድረስ ያደረጉትን ጥረት የተመለከትን ሲሆን ሶዶ ከተማዎች ኳስን በመልቀቅ ኃይል በቀላቀለ አጨዋወት ኳስን ለመንጠቅ እና በዛ ብሎ በመከላከል ያደረጉት እንቅስቃሴን አስመልክተውናል። በተጨማሪም ሶዶ ከተማዎች በመስመር እና በረጅም ኳስ በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩ ቢሆንም በእንዳለ ዮሐንስ የሚመራው የሀምበሪቾ የተከላካይ ክፍል ወደ ፊት ገፍቶ በመጫወት የመልሶ ማጥቃቱን በብቃት ሲያቋርጡ ተስተውሏል። በዚሁ ሁኔታ አጋማሹ ምንም ግብ ሳይቆጠር ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሁኔታ ጨዋታውን ለማሸነፍ ያላቸው ፍላጎት ከሶዶ ከተማ በበለጠ ሁኔታ የነበረ ሲሆን የተጫዋች ቅያሬም በማድረግ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል ። ሶዶ ከተማዎች የጨወዋታውን ፍጥነት በማቀዝቀዝ እና ግብ እንዳይቆጠርባቸው በጥብቅ መከላከል ጨዋታውን የጨረሱ ሲሆን ጨዋታውም ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል። ሀምበርቾ ማሸነፍ ባለመቻሉ በነጥብ ከመሪው ገላን ከተማ ጋር ተስተካክሎ በግብ ክፍያ 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

የካ ክ/ከተማ 0-1 ጅማ አባ ጅፋር

የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ተመጣጣኝ ፉክክር የተመለከትንበት አጋማሽ ሲሆን በየካ ክ/ከተማ በኩል የመሀል ክፍለቸው ክብሮም ግርማይ እንዲሁም በመስመር ተጫዋቹ ኃይሉ ፀጋዬ እና ማቲያስ ሹመቴ መልካም የሚባል እንቅስቃሴ አሳይተዋል። በጅማ አባ ጅፋር በኩል ዋኩማ ደንሳ እና አሚር አብዲ ድንቅ የሚባል እንቅስቃሴ ሲያስመለክቱን በ31ኛው ደቂቃ ላይ ጅማ አባ ጅፋሮች ኳስን መስርተው ወደ ግብ በሚሄዱበት ሰዓት አሚር አብዱ ላይ በተሰራ ጥፋት ሱራፌል ፍቃዱ ወደ ግብ ቀይሮ ጅማ አባ ጅፋርን መሪ ማድረግ ችሏል።

ሁለተኛው አጋማሽ ኳስን ተቆጣጥረው የተጫወቱት የካዎች በብስራት በቀለ አማካኝነት ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን የፊት መስመራቸው ብዙ የግብ ዕድሎችን በማባከን ዋጋ አስከፍለዋል። ጅማ አባ ጅፋሮች ግባቸውን ሳያስደፍሩ በመጀመሪያው አጋማሽ ባስቆጠሩት ግብ አሸንፈው ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።

ሮቤ ከተማ 1-1 ኦሜድላ

እልህ እና አልሸነፍ ባይነት በሁለቱም በኩል የታየበት ቀዳሚ አጋማሽ ገና ከመጀመሩ በ3ኛው ደቂቃ ሮቤ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ጠረት በሚያደርጉበት ሰዓት ተጨራርፎ ያገኘውን ኳስ ሶፊያን ገለቱ በአስገራሚ ሁኔታ ከፍፁም ቅጣት ምት ሳጥን ውጪ አክርሮ የመታውን ኳስ ወደ ግብ ቀይሮ ሮቤ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ኦሜድላዎች ሙሉ በሙሉ ጨዋታውን በመቆጣጠር ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩ ተመልክተናል። በሮቤ ከተማ በኩል ያገቡትን ግብ አስጠብቀው ግብ እንዳይቆጠርባቸው አብዝተው በመከላከል የጨዋታውን ፍጥነት ለማቀዝቀዝ ሲሞክሩ ተስተውሏል። አጋማሹም ሌላ ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር በሮቤ ከተማ መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የኦሜድላዎች የበላይነት የታየበት ጨዋታ ሲሆን የፊት አጥቂያቸው ቻላቸው ቤዛ ከፍተኛ የሆነ ጫና በሮቤ ከተማ ተከላካዮች ላይ ያሳደረ ሲሆን ሮቤ ከተማዎች በመልሶ ማጥቃት አልፎ አልፎ የኦሜድላዎች የግብ ክልል ሲደርሱ ተመልክተናል። በ78ኛው ደቂቃ የኦሜድላው ዋና አሰልጣኝ የሆነው ኢብራሂም ከዳኛ ጋር በፈጠረው እሰጥ አገባ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበተ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በ82ኛው ደቂቃ ኦሜድላዎች ከመስመር ያሻሙትን ኳስ ተመስገን ያቆብ በማስቆጠር ኦሜድላን አቻ ማድረግ ችሎ ጨዋታው በአቻ ውጤት ተፈፅሟል።

\"\"