ሪፖርት | መቻል ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ ወደ ድል ተመልሷል

የዳዊት ማሞ የመጨረሻ ደቂቃ የቅጣት ምት ጎል መቻልን ሙሉ ሦስት ነጥብ አስጨብጣለች።

መድኖች ከወላይታ ድቻው ጨዋታ ባደረጓቸው ለውጦች ቴዎድሮስ በቀለ ፣ ያሬድ ካሳዬ ፣ ሐቢብ ከማል እና አሚር ሙደሲር ወደ አሰላለፍ ሲመጡ መቻሎች ከመጨረሻው ጨዋታቸው አንፃር በረከት ደስታን አሳርፈው ከነዓን ማርክነህን አስጀምረዋል።

\"\"

የኢትዮጵያ መድን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በነበረበት የመጀመርያው አጋማሽ ምንም እንኳ በርካታ የግብ ሙከራዎች ባያስመለክትም በፉክክር ረገድ የተሻለ ነበር። ሙከራዎች በማድረግ ረገድ የተሻሉ የነበሩት መድኖች በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች በብሩክ እና ሀቢብ አማካኝነት ሁለት እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም ሀቢብ የመቻል ግብ ጠባቂ ውብሸት የተሳሳተውን ኳስ ተጠቅሞ የሞከረው ኳስ እጅግ ለግብ የቀረበ ነበር።

በአጋማሹ የጥንቃቄ ጨዋታ በመምረጥ የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት በመመከት ተጠምደው የነበሩት መቻሎች በመስመር በሚሻሙ ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ፍያማ አልነበረም። በጠንካራ ሙከራ ደረጃም ሳሙኤል ሳሊሶ ከቅጣት ምት ካደረገው ሙከራ ውጭ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሁሉ ጥቂት ሙከራዎች የታዩበት ሁለተኛው አጋማሽ መቻሎች ተሻሽለው የቀረቡበት በአንፃሩ መድኖች ከመጀመርያው አጋማሽ እንቅስቃስያቸው ወርደው የታዩበት ነበር። በመቻል በኩል በምንይሉ ወንድሙ እና ከነዓን ማርክነህ በኩል ሙከራ አድርገዋል። በስልሳ ሰባተኛው ደቂቃም በበረከት ደስታ አማካኝነት መሪ ለመሆን የተቃረቡበት ዕድልም ማግኘት ችለው ነበር። አማካዩ እስራኤል በግሩም ሁኔታ ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ነበር ሙከራውን ያደረገው።

ጥቂት የግብ ዕድሎች ብቻ የፈጠሩት መድኖችም በአጋማሹ በሳይመን ፒተር እና ባሲሩ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል ፤ በተለይም ሳይመን ያደረገው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ የነበሩት መቻሎች በዘጠናኛው ደቂቃ በዳዊት አማካኝነት ምርጥ የቅጣት ምት ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። ከረዥም ርቀት በተቆጠረው ግብ የግብ ጠባቂው የቦታ አያያዝ ችግር በጉልህ ታይቷል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ሦስት ነጥብ ያስፈልጋቸው የነበረ ቢሆንም የሚገባቸውን አለማድረጋቸውን ገልፀው በተጫዋቾቻቸው ላይ ድካም እንዳለ ያነሱ ሲሆን በቀሪ 10 ጨዋታዎች የሚችሉትን እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ጨዋታው እንደጠበቁት አስቸጋሪ እንዳልነበር ጠቅሰው ከዚህ የተሻለ መጫወት ይችሉ እንደነበር ሆኖም በመጀመሪያው አጋማሽ ለተጋጣሚያቸው በሰጡት ግምት የጥንቃቄ አጨዋወት ማምረጣቸውን አብራርተው በጫና ውስጥ ሆነው ጨዋታዎችን እያደረጉ እንዳሉ ጠቁመዋል።

\"\"