ሪፖርት | ነብሮቹ በተከታታይ ድል ነጥባቸውን 30 አድርሰዋል

ሀዲያ ሆሳዕና ተቀይሮ የገባው መለሰ ሚሻሞ በመጀመሪያ ንክኪው ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል ወላይታ ድቻን 1-0 አሸንፏል።

\"\"

ተጋጣሚዎቹ ከመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው አንፃር ባደረጓቸው ለውጦች ሀዲያ ሆሳዕና አምስት ቢጫ ያለበት ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀንን በፍሬዘር ካሳ ሲተካ ወላይታ ድቻ ደግሞ ዘላለም አባቴን አሳርፎ ዮናታን ኤልያስን አስጀምሯል።

ጨዋታውን ወደ ግራ መስመር ያደላ የማጥቃት ጫና በመፍጠር የጀመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች የተሻጋሪ ኳሶቻቸው ጥራት ዕድሎችን ለመፍጠር በቂ አልነበሩም። ይልቁኑም ጠንቀቅ ብለው የጀመሩት ድቻዎች 8ኛው ደቂቃ ላይ ፔፔ ሰይዶ በሰራው ስህተት በቢኒያም ፍቅሬ አማካይነት ለማስቆጠር ተቃርበው ግብ ጠባቂው ኳሱን በማዳን ስህተቱን ሊያርም ችሏል።

\"\"

በጠንካራ ፉክክር አካላዊ ፍትጊያዎች የበዙበት ቀሪው የአጋማሹ ክፍል ግን ወላይታ ድቻዎች የተጋጣሚያቸውን ጥቃት አቅም በማሳጣቱ ረገድ የተሻሉ ሆነው ቢታዩም በሦስት አጋጣሚዎች ያገኟቸው ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶች ወደ ግብ ዕድልነት ሳይቀይሩ ቀርተዋል። በነብሮቹ በኩልም እንዲሁ አልፎ አልፎ ሾልከው የድቻ ግብ አፋፍ የደረሱ ኳሶች ቢታዩም ቢኒያም ገነቱን ያስጨነቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ተጋምሷል።

በቆሙ ኳሶች የታጀበው ፍትጊያ በሁለተኛውም አጋማሽ የቀጠለ ሲሆን ወላይታ ድቻ በንፅፅር የተሻለ ጫና ፈጥሯል። ሆኖም 65ኛው ደቂቃ ላይ ካሌብ በየነ የመታው ቅጣት ምት የግቡን ቋሚ ገጭቶ ሲመለስ ተቀይሮ የገባው መለሰ ሚሻሞ በመጀመሪያ ንክኪው አስቆጥሮ ነብሮቹን ቀዳሚ አድርጓል።

\"\"

ከግቡ መቆጠር በኋላ ወላይታ ድቻዎች ቅያሪዎችን በማድረግ ቀጥተኛነታቸው ጨምረው የአቻነት ግብ ፍለጋ ተንቀሳቅሰዋል። በአንፃሩ ነብሮቹ ወደ ሜዳቸው ሳብ ብለው አደጋ በመቀነስ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል። ጨዋታውም በነብሮቹ 1-0 አሸናፊነት ተፈፅሟል።

ጨዋታው ካበቃ በኋላ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በሰጡት አስተያየት ጨዋታው ፈታኝ እንደነበር አንስተው መለሰ ተቀይሮ በገባባቸው ጨዋታዎች ሦስት ግቦች ማስቆጠሩን አስታውሰው የክለቡ ወጣት ተጫዋቾች ወደፊት ለቡድኑም ሆነ ለሀገር እንደሚጠቅሙ ተናግረዋል። ጨዋታው ተመጣጣኝ እንደነበር ያነሱት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በበኩላቸው ጥሩ በነበሩበት ቀዳሚው አጋማሽ ጎል ማግባት እንደነበረባቸው ተናግረው የመስመር ጥቃታቸው አጥጋቢ እንዳልነበር እና ድካምም እንደታየባቸው አስረድተዋል።

\"\"