ሪፖርት | ሠራተኞቹ በአዳማ ቆይታቸው የመጀመርያ ድላቸውን አግኝተዋል

ከወራጅ ቀጠና ለመሸሽ የተደረገው ጨዋታ በወልቂጤ ከተማ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ያልተረጋጋ የውድድር ዓመት እያሳለፈ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ያለጎል ካጠናቀቀበት ስብስቡ ምንም አይነት የተጫዋች ለውጥ ሳያደርግ ሲቀርብ በተከታታይ ጨዋታዎች ሽንፈት በማስተናገዱ ሳይታሰብ በወራጅ ቀጠነቀው አፋፍ ላይ የደረሰው ወልቂጤ ከተማ በሀዋሳ ከተማ ከተረታበት ጨዋታ ግብጠባቂ ፋሪስ አላዊ፣ አዲስዓለም ተስፋዬ፣ ብዙአየሁ ሰይፉ እና የኋላሸት ሰለሞን በግብጠባቂ ጀማል ጣሰው፣ ዋሁብ አዳምስ፣ ማቲያስ ወልደአረጋይ እና አቤል ነጋሽ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

\"\"

ከአደገኛው የወራጅነት ቦታ ለመሸሽ ከፍተኛ ፉክክር ይታይበታል ተብሎ የጠጠበቀው ጨዋታ ገና በመጀመርያ ደቂቃዎች ነበር ለጎል የቀረበ ሙከራ መመልከት የቻልነው። በ6ኛው ደቂቃ ጌታነህ ከበደ ከረጅም ርቀት የመታውን ኳስ ፊሊፒ ኦቮኖ ወደ ውጭ አውጥቶበታል። ሁለቱም ቡድኖች ካለባቸው ወቅታዊ የውጤት ቀውስ አንፃር እንቅስቃሴያቸው ይቆራረጥ የነበረ በመሆኖ ሌሎች ግልፅ የጎል እድሎችን ለማየት ረዘም ላሉ ደቂቃዎች መጠበቅ አስፈልጎ ነበር።


በዚህ ሂደት ግን የጨዋታውን እንቅስቃሴ ህይወት የዘራበት ጎል ካልተጠበቀ አቅጣጫ ሠራተኞቹ በ21ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከመሐል ሜዳ ቀኝ መስመር ጥቂት ራቅ ብሎ የተገኘውን የቅጣት ምት ተመስገን በጅሮንድ በቀጥታ ወደ ጎል በመምታት ድንቅ ጎል አስቆጥሮል። ከዚህች ድንገተኛ ጎል አንድ ደቂቃ በኋላ ሲዳማ ቡናዎች አጥቂያቸው ፊሊፕ አጃህ ከሳጥን ውጭ የመታውን ኳስ የግቡ ቋሚ የመለሰበት ጥሩ አፀፋዊ ምላሽ ነበር።

ወደ አቻነት ለመመለስ ሲዳማዎች በተሻለ ብልጫ ወስደው መጫወት ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል የተበታትነው የማጥቃት መንገዳቸው በቀላሉ በወልቂጤ ተከላካዮች ይቋረጥ ነበር። ወልቂጤዎች በጥብቅ መከላከል በመስመሮች በኩል ሾልኮ በመግባት ለማጥቃት ቢያስቡም ስኬታማ ሳይሆኑ ጨዋታው ለእረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።


ከሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ የማጥቃት መንገዳቸውን በተገቢው መንገድ አርመው የመጡት ሲዳማ ቡናዎች በ48ኛው ደቂቃ ወደ ጨዋታው የገቡበትን ጎል በቴዎድሮስ ታፈሰ አማካኝነት አግኝተዋል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ የሲዳማ ቡና የአማካኝ ክፍል ተጫዋቾች ወደ ፊት በመሄድ በማጥቃቱ በኩል እገዛ ማድረጋቸው ተጨማሪ ጎሎች ለማግኘት ጥረት ለማድረግ ቢያስቡም በሂደት እየተቀዛቀዙ መጥተዋል። ይህን ተከትሎ ወልቂጤዎች አልፎ አልፎ ከሚያደርጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ ለሲዳማ ቡና ተከላካዮች የሚያስጨንቅ ነበር።


የጨዋታው መጠናቀቂያ አስራ አምስት ደቂቃ ሲቀረው በሁለቱም በኩል ግልፅ የማግባት ዕድሎችን መመልከት ስንችል ለዚህም ማሳያ በወልቂጤ በኩል 76ኛው ደቂቃ አቤል ነጋሽ ወደ ጎል መቶት ፊሊፕ ኦቮኖ ያመከነበት በሲዳማ በኩል 78ኛው ደቂቃ ፊሊፕ አጃህ ያልተጠቀመበት ግልፅ የጎል አጋጣሚ ተጠቃሽ ነበሩ። በእነዚህ ሙከራዎች ጨዋታው ተነቃቅቶ ሲቀጥል ወልቂጤዎችን መሪ ያደረገች ሁለተኛ ጎል 81ኛው ደቂቃ ተመዝግባለች። ጌታነህ ከበደ ከቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ተቀይሮ የገባው ፋሲል አበባየሁ ኳሷን በእጁ ታግዞ ወደ ጎልነት ቀይሮታል። በመጨረሻው ደቂቃ የአቻነት ጎል ፍለጋ ሲዳማዎች ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ፍሬ ሳያፈራ 2-1 ለመሸነፍ ተገደዋል። ከተከታታይ አምስት ጨዋታ በኋላ የመጀመርያውን ሦስት ነጥብ ያገኙት ወልቂጤዎች ነጥባቸውን 24 በማድረስ ደረጃቸውን በአንድ ከፍ አድርገው 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ በአንፃሩ ሲዳማዎች ባሉበት 21 ነጥብ በ14ኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ ተገደዋል።


ድል ያደረጉት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራ ቡድናቸው ጫና ውስጥ እንደነበረ እና ታክቲካሊ ያሰቡትን ነገር በጨዋታው ተጫዋቾቻቸው መተግበራቸው ደስተኛ እንዳደረጋቸው አንስተው ቡድናቸው በየጨዋታው እድገት የነበረው መሆኑን በጥሩ መንገድ አንስተውታል። ሽንፈት ያስተናገዱት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በበኩላቸው መጀመሪያ ያስተናገዱት ጎል ጫና ውስጥ እንደከተታቸው እና ያገኙትን የጎል ዕድሎች አለመጠቀም እንደክፍተት በማንሳት ከዚህ በኋላ ቡድናቸው የከፋ ውጤት እንደማይገጥመው ገልፀው ሁሉም በርትቶ ከሰራ ከዚህ ደረጃ ከፍ እንደሚሉ በእርግጠኝነት ተናግረዋል።

\"\"