መረጃዎች | 83ኛ የጨዋታ ቀን

በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ20ኛ ሳምንት መቋጫ የሆኑ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አዘጋጅተናል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ፋሲል ከነማ

የዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር በ42 ነጥቦች የሊጉ መሪ የሆነውን ቅዱስ ጊዮርጊስን በ 15 ነጥቦች ዝቅ ብሎ 7ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጠው ፋሲል ከነማ ጋር ሲያገናኝ ፈረሰኞቹ መሪነታቸውን ወደ ሦስት ነጥብ ለማስፋት አፄዎቹ ተከታታይ ድል አስመዝግበው ካሉበት ደረጃ ከፍ ለማለት እጅግ ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በአምስተኛው የጨዋታ ሳምንት የውድድር ዓመቱን ብቸኛ ሽንፈት ሲያስተናግዱ ተጋጣሚያቸው የነበረውን ፋሲል ከነማን የሚገጥሙት ፈረሰኞቹ በሊጉ ወጥ የሆነ አቋም ላይ መገኘታቸው እንደ ጥሩ ጎናቸው ሲታይ ሊያሳስባቸው የሚችለው ብቸኛ ነገር በሊጉ ዝቅተኛውን የግብ መጠን (12) ያስተናገደው ቡድናቸው ካለፉት አምስት ጨዋታዎች በአራቱ ግቡን ማስደፈሩ ነው። ሆኖም ቡድኑ ካለበት የአሸናፊነት መንፈስ ላለመውጣት በውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ከገባው ፋሲል ከነማ የሚጠብቀው ፉክክር ቀላል አይሆንም።

\"\"

በሰባተኛው እና በስምንተኛው ሳምንት ብቻ ተከታታይ ድል ያስመዘገቡት አጼዎቹ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት መቻልን በሽመክት ጉግሣ ብቸኛ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ በመርታት ወደ ድል ቢመለሱም አሁንም ሜዳ ላይ እያሳዩት ያለውን ያልተደራጀ እንቅስቃሴ በጊዜ ማስተካከል ይጠበቅባቸዋል። ፋሲል ከነማዎች የነገው ተጋጣሚያቸውን ሲረቱ ብቸኛዋን ግብ ማስቆጠር ችሎ የነበረው እና በግሉ በድንቅ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኘው ታፈሰ ሰለሞን በነገው ዕለትም ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከዚህ ቀደም ጉዳት ላይ ከነበሩት አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ ሀይደር ሸረፋ እና አቤል ዮናስ በተጨማሪ አማኑኤል ተርፋም ጉዳት የገጠመው በመሆኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ መሆኑ ሲረጋገጥ በፋሲል ከነማዎች በኩል ፍቃዱ አለሙ በጉዳት አለምብርሀን ይግዛው በቅጣት አይኖሩም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በፕሪሚየር ሊጉ ለ12 ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን 28 ግቦች በተቆጠሩበት ግንኙነታቸው አሥራ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው ፋሲል ከነማ ለ6 አሥራ አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ ለ4 ጊዜ ድል ሲቀናቸው ሁለቱ ጨዋታዎች በአቻ ተጠናቀዋል። ቅዱስ ጊዮርጊስ 2000 ዓ.ም ላይ የ 2-0 ፋሲል ከነማ ደግሞ 2011 ዓ.ም ላይ የ 3-0 የፎርፌ ውጤት አግኝተዋል።

ተጠባቂውን ጨዋታ ለመምራት ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በ24 ነጥቦች 10ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ድሬዳዋ ከተማዎች  በ31 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ጋር ሲያገናኝ  ብርቱካናማዎቹ  ካሉበት የውጤት ቀውስ በቶሎ ለማገገም ኃይቆቹ ያሉበትን የአሸናፊነት ስነልቦና አስቀጥለው ከመሪዎቹ ለመጠጋት ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

በውድድር ዓመቱ ካደረጓቸው 19 ጨዋታዎች በ 18ቱ ግብ ያስተናገዱት ድሬዳዋ ከተማዎች አሠልጣኝ አሥራት አባተን በቀጠሩ ማግስት ወደ ድል መመለስ ቢችሉም ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ግን በባህር ዳር ከተማ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። በየ ጨዋታው ከመከላከሉ በተሻለ ባልተገደበው የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው በሚታወቁት የመስመር ተከላካዮቻቸው በርካታ የግብ ዕድሎችን ቢፈጥሩም የራሳቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ ደካማ የሆኑት ድሬዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተደራጅቶ በመግባት ክፍት ቦታቸውን መሸፈን ይገባቸዋል። ቁጥሮች እንደሚገልጹትም በነገው ዕለት ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አምስት ግቦችን ካስቆጠሩት ሀዋሳ ከተማዎች እጅግ ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ይታመናል።

\"\"

ከነበራቸው ወጥ ያልሆነ አቋም በመጠኑ እያሻሻሉ የመጡት ሀዋሳ ከተማዎች ካለፉት አራት ጨዋታዎች በሦስቱ ድል ማድረጋቸው ይህንን ይደግፋል። በተለይም በእነዚህ ጨዋታዎች በነሱ ተጫዋቾች የተቆጠሩት 4  ግቦች በአራት የተለያዩ ተጫዋቾች መቆጠራቸው  ለሚመርጡት የማጥቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ ግብዓት እንደሚሆንላቸው ይጠበቃል። በነገው ዕለትም ድል ተቀዳጀተው በውድድር ዓመቱ  ለመጀመሪያ ጊዜ ሦስት ተከታታይ ድል ለማስመዝገብ ከብርቱካናማዎቹ የሚገጥማቸው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ይጠበቃል።

በድሬዳዋ ከተማ በኩል ጉዳት ላይ የነበረው ሙኸዲን ሙሳ አገግሞ ለነገው ጨዋታ ዝግጁ ሲሆን ሌላኛው የቡድን አጋሩ ያሬድ ታደሰ ግን የነገው ጨዋታም የሚያመልጠው ይሆናል። ሀዋሳዎች በበኩላቸው ሙጂብ ቃሲም እና መድሀኔ ብርሀኔን በቅጣት ወንድማገኝ ሀይሉ እና ብርሀኑ አሻሞን ደግሞ በጉዳት አያገኙም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ 20 ጊዜያት ሲገናኙ ሀዋሳ ከተማ ለሰባት ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ ለአምስት ጊዜያት ድል ሲያደርጉ ስምንቱ ጨዋታዎች አቻ ተጠናቀዋል። ሀዋሳዎች 20 ድሬዎች ደግሞ 18 ግቦችን ማስቆጠር ችለዋል።

የምሽቱን መርሐግብር ዮናስ ካሳሁን በዋና ዳኝነት አብዱ ይጥና እና መሐመድ ሁሴን በረዳትነት ተካልኝ ለማ በበኩላቸው በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።