በጨዋታ ሳምንቱ ተጠባቂ በነበረው ፍልሚያ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በእስማኤል ኦሮ-አጎሮ ብቸኛ ግብ ፋሲል ከነማን አሸንፈዋል።
ፈረሰኞቹ ባለፈው ሳምንት ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ አማኑኤል ተርፉ እና ናትናኤል ዘለቀን በምኞት ደበበ እና በረከት ወልዴ ተክተው ገብተዋል። ዐፄዎቹ በበኩላቸው መቻልን ካሸነፈው ስብስብ ወንድማገኝ ማርቆስ ፣ ከድር ኩሊባሊና ታፈሰ ሰለሞንን በአምሳሉ ጥላሁን ፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ይሁን እንደሻው ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
እንደተጠበቀው ብርቱ ፉክክር ባስመለከተው ጨዋታ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ኳስ ቁጥጥር ላይ የተመሰረት አጨዋወት ለመተግበር ቢሞክሩም በአጨዋወቱ ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች ለመፍጠር የቻሉባቸው አጋጣሚዎች ግን ጥቂት ናቸው። ይህንን ተከትሎም ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ከተፈጠሩ ጥቂት ሙከራዎች ውጭ ዕድሎች አልተፈጠሩም።
በፈረሰኞቹ በኩል በቢንያም እና ኦሮ አጎሮ አማካኝነት በተጠቀሰው የመስመር አጨዋወት የተፈጠሩ ዕድሎችም ይጠቀሳሉ ፤ በተለይም ረመዳን አሻምቶት ቢንያም በላይ ከግቡ ፊት ለፊት ሆኖ በግንባር ያደረገው ሙከራ የአጋማሹ ወርቃማ ዕድል ነበር።
በሙከራ ረገድ ሙሉ ብልጫ የነበራቸው ፈረሰኞቹ ከመዐዝን በተሻማ ኳስ በአቤል ያለው አማካኝነት የሞከሩት ያለቀለት የግብ ሙከራም ሌላው ቡድኑን መሪ ለማድረግ የተቃረበ ኳስ ነበር ፤ በሂደቱ ሚኬል ሳማኪ ሙከራውን ለማክሸፍ ያሳየው ንቃትም የምያስደንቅ ነበር። ኦሮ አጎሮ ከርቀት አክርሮ የሞከራት ሙከራም በፈረሰኞቹ በኩል ከተፈጠሩት ዕድሎች ትጠቀሳለች። በአጋማሹ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ካሳዩት እንቅስቃሴ ውጭ በመከላከል ላይ ተጠምደው የዋሉት ዐፄዎቹ መናፍ አወል ከርቀት ካደረገው ሙከራ ውጭ ዕድሎች መፍጠር አልቻሉም።
ሁለተኛው አጋማሽ በፋሲል ከነማ በኩል የአጨዋወት ለውጥ የተደረገበት ነበር ፤ በመጀመርያው አጋማሽ ጥራት ባይኖረውም አጫጭር ኳሶች ለመጫወት ጥረት ስያደርግ የታየው ቡድን በሁለተኛው አጋማሽ ረዧዥም ኳሶች እና መልሶ ማጥቃት ምርጫው አድርጓል። ዐፄዎቹ ከፈጠሯቸው ዕድሎችም ባልተለመደ ቦታው በመስመር ተከላካይነት ጨዋታውን የጀመረው ናትናኤል ከመስመር ያደርገው ሙከራ እና አስቻለው በግንባር የላከው ሙከራ ይጠቀሳሉ።
በተለይም በሙከራ ረገድ በአጋማሹ ሙሉ ብልጫ የነበራቸው ፈረሰኞቹ በሰባ አንደኛው ደቂቃ በሱሌይማን ፣ አጎሮ እና አቤል ጥሩ መናበብ የተፈጠውን ንፁህ የግብ ዕድል ተጠቅመው ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። ቶጓዊው አጥቂ ከአቤል ያለው የተቀበለውን ኳስ ግብ ጠባቂውን አታሎ በማለፍ ነበር ያስቆጠረው።
በጉዳት ምክንያት አስገዳጅ ቅያሬዎች ለማድረግ የተገደዱት ቅዱስ ጊዮርጊሶች በቸርነት ጉግሳ እና ቢንያም በላይ አማካኝነት ሙከራዎችም ማድረግ ችለዋል ፤ በተለይም ቸርነት ጉግሳ በተከላካዮች መሀል አልፎ መቷት ሳማኪ የመለሳት ኳስ የፈረሰኞቹ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ለማድረግ የተቃረበች ኳስ ነበረች።
በመጨረሻው ደቂቃም ዐፄዎቹ በጨዋታው እጅግ ለግብ የቀረበች ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ሙከራዋም ዱላ ኳሷን ወደ ሳጥን ይዟት ለመግባት ጥረት በምያደርግበት ጊዜ የቅዱስ ጊዮርጊስ ተጫዋች ጨርፏት የተገኘችውን ኳስ መቶ ቻርለስ ሉክዋን እንደምንም አድኗታል። ጨዋታው አንድ ለባዶ መጠናቀቁ ተከትሎ ፈረሰኞቹ ከተከታዮቻቸው የነበረውን የነጥብ ልዩነት ማስፋት ችሏል።
በቀዳሚነት አስተያየታቸውን የሰጡት የዐፄዎቹ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ለመሸናነፍ የነበረው ፉክክር ጥሩ እንደነበር ገልፀው በሁለተኛው አጋማሽ ዕድሎች አለመጠቀማቸውን ገልፀዋል። \”የመጀመርያው አጋማሽ የነበረው ክፍተት ለማስተካከል ሞክረናል ግን የተፈጠሩ የግብ ዕድሎች መጠቀም አልቻለም \” ካሉ ስለ ወረጅነት ስጋት ተጠይቀውም ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል። \”ፋሲል ጠንካራ ቡድን ነው ፤ በተከታታይ ዓመታት የነበረው ውጤት ይታወቃል ስለ ወራጅነት መናገር አያስፈልግም \”ብለዋል።
የፈረሰኞቹ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ገልፀው ለመሸናነፍ የነበረው ፉክክርም በበጎነቱ አንስተዋል። \”በመጀመርያው አጋማሽ ዕድሎች መጠቀም አልቻልንም ነበር ፤ በሁለተኛው አጋማሽ ግን ክፍተቶቻችን እነሱ ባልጠበቁት መንገድ ነው ግን ያስቆጠርነው\” ብለዋል። አሰልጣኙ ቀጣይ ሳምንት ከአርባምንጭ ላለባቸው ጨዋታም ክፍተቶቻቸው አርመው እንደሚቀርቡ ገልፀዋል።