ሪፖርት | ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

 


የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተገባዷል።

የወጥነት ጥያቄ የሚነሳባቸው ድሬዳዋ ከተማዎች በባህር ዳር ከተማ ከተረቱበት ጨዋታ ብሩክ ቃልቦሬ፣ አሳንቴ ጎድፍሬድ ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ፣ ሄኖክ ሀሰን እና አቤል አሰበን በመሳይ ጳውሎስ፣ እንየው ካሣሁን፣ ጋዲሳ መብራቴ፣ ዩሴፍ ተስፋዬ እና ዳዊት እስጢፋኖስ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል። ተከታታይ ጨዋታ በማሸነፍ ደረጃቸውን እያሻሻሉ የሚገኙት ሀዋሳ ከተማዎች ወልቂጤ ከተማን ካሸነፉበት ስብስባቸው መድሃኔ ብርሀኔ፣ አዲሱ አቱላ እና ሙጂብ ቃሲምን በዳንኤል ደርቤ፣ አብዱልባሲጥ ከማል እና እዮብ አለማየሁ ለውጠው ለጨዋታው ዝግጁ ሆነዋል።

\"\"

ባልተረጋጋ እንቅስቃሴ የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በሀዋሳ በኩል ለድሬደዋ ከተማ ተጫዋቾች ጊዜ እና ክፍት ቦታ ባለመስጠት በተወሰነ መልኩ በቁጥር በዝተው የማጥቃት ፍላጎት ቢያሳዩም ያን ያህል ውጤታማ አልነበሩም። በአንፃሩ ድሬደዋ ከተማዎች መሐል ሜዳ ላይ ብልጫ ለመውሰድ የሚያስችላቸውን ቅብብሎሽ ቢያደርጉም ቶሎ ቶሎ ኳሶቻቸው እየተቆራረጡ ወደ ማጥቃት ክልል ለመግባት ሲቸገሩ እያስተዋልን እንቅስቃሴው አስራ ሰባት ደቂቃ መዝለቅ ችለዋል።


ሆኖም በ18ኛው ደቂቃ በቅብብሎሽ መሐል የድሬደዋ ተከላካዮች የፈጠሩትን ስህተት ተከትሎ ዓሊ ሱሌይማን በፍጥነት ኳሱን ቀምቶ ወደ ፊት በመሄድ የፈጠረው አደጋ በጨዋታው የተመለከትነው የተሻለ ለጎል የቀረበ ሙከራ ነበር። ከደቂቃዎች በኋላ በቃሉ ገነነ ከተሻጋሪ ኳስ ያቀበለውን ዓሊ ሱሌማን በተገቢው መንገድ ኳሱን ቢቆጣጠረውም የመጨረሻው ውሳኔ ጥሩ ባለመሆኑ ግልፅ የማግባት አጋጣሚውን በቀላሉ አምክኖታል። የማጥቃት ሽግግራቸው በሚቆራረጡ ኳሶች ምክንያት ዕድሎችን መፍጠር የተቸገሩት ድሬደዋ ከተማዎች በአንበላቸው ዳዊት እስጢፋኖስ አማካኝነት ከሳጥን ውጭ በተመታ ኳስ የመጀመርያ የጎል እድላቸውን ማግኘት ችለዋል። በአጠቃላይ የመጀመርያው አጋማሽ በሁለቱም በኩል ውጤት የሚቀይር ሙከራ ሳንመለከት ተጠናቋል።


በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ድሬደዋ ከተማዎች በተሻለ መንቀሳቀስ ቢችሉም አደገኛው የማጥቃት ዞን ሲደርሱ ለአጥቂዎቻቸው የተሳካ ኳስ ማድረስ ባለመቻላቸው የወሰዱትን ብልጫቸውን በጎል ማገዝ ባይችሉም 71ኛው ደቂቃ ፀጋአብ ዮሐንስ የፈጠረውን ስህተት ተጠቅሞ ቻርልስ ሙሴጌ በመጠንቅ በጥሩ አቋቋም የሚገኘው ዳዊት እስጢፋኖስ ተቀብሎ ወደ ጎልነት ቀየረው ሲባል ወደ ሰማይ የሰደዳት ኳስ ለቡርትካናማዎቹ የምታስቆጭ አጋጣሚ ነበረች። አስቀድሞ ከነበረው ጥረት ወረድ ብሎ የተመለሱት ሀዋሳ ከተማዎች ዓሊ ሱሌማንን ትኩረት ያደረገው የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ትርጉም አልባ ሆኖ ጎል ለማስተናገድ ችለዋል።


አሰልጣኝ አስራት አባተ ደቂቃዎች በገፋ ቁጥር ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ ጎል ፍለጋ ያደረጉት ጥረት ተሳክቶ በ79ኛው ደቂቃ መሪ ያደረገቻቸውን ጎል አግኝተዋል። ከግራ መስመር ኤልያስ አህመድ በግል ጥረቱ ወደ ሳጥን በመግባት ወደ ጎል የመታውን ኳስ ተቀይሮ የገባው አቤል ከበደ ኳሱን አግኝቶ አስቆጥሮታል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ በቀሩት ደቂቃዎች ቡርትካናማዎቹ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ዕድሎች ቢፈጥሩም የተለየ ነገር ሳንመለከት ጨዋታው በድሬደዋ አንድ ለምንም አሸናፊነት ተገባዷል። ውጤቱን ተከትሎ ድሬዳዋዎች ነጥባቸውን 27 አድርሰው 9ኛ ደረጃ በመያዝ በአንድ ሲያሻሽሉ ሀዋሳዎች በበኩላቸው ባሉበት 31 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ረግተው ተቀምጠዋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ የመጀመርያ ድላቸውን ያሳኩት አሰልጣኝ አስራት አባተ የዛሬው ጨዋታ አስፈላጊ በመሆኑ መሰዋዕትነት ከፍለው ውጤቱን ማግኘት መቻላቸው ጥሩ መሆኑን ተናግረው ቡድናቸው እየተሻሻለ መምጣቱን በመግለፅ ውጤቱ በቀጣይ መነሳሳትን እንደሚፈጥር በንግግራቸው አክለው አንስተዋል። ሽንፈት ያስተናገዱት አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው ከስምንት ጨዋታ በኋላ መሸነፋቸው ቡድናቸው ጥንካሬውን ማሳያ መሆኑን እና ተጭነው ጎል ለማስቆጠር መጫወት ባሰቡበት ወቅት ጎል ማስተናገዳቸው በውጤት ረገድ እንዳልተሳካለቸው ገልፀው ቀጣይ ላለባቸው ጨዋታዎች ራሳቸውን አዘጋጅተው እንደሚመጡ ተናግረዋል።