ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ቅጣት ተላልፎባቸዋል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር አመራር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ በ20ኛ ሳምንት በታዩ የዲሲፕሊን ግድፈቶች ላይ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።

በተጫዋች እና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች ተሾመ ሸዋነህ(አርባምንጭ ከተማ) የክለቡ የቡድን መሪ ሆነው የዳኛን ውሳኔ በመቃወምና ቁሳቁስ በመወርወር ከጨዋታ ሜዳ የተወገዱ ስለመሆኑ ሪፖርት ቀርቦባቸው ለፈፀሙት ጥፋት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ 10 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ እንዲሁም በተጫዋቾች ምንይሉ ወንድሙ(መቻል) እና ሱሌይማን ሀሚድ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ 1500 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍሉ ተወስኗል።
\"\"
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶች ደግሞ በሶስት ክለቦች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች መተላለፋቸው ተመላክቷል። በቅድሚያ አርባምንጭ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ስድስት ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 5 ሺ ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል ሲወሰን ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በደጋፊዎቻቸው ተከስቷል በተባለ ግድፈት ቅጣቶች ተላልፎባቸዋል።
\"\"
ኢትዮጵያ ቡና በተጫወተበት እለት የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛ አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት በመቅረቡ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 50 ሺ ብር እንዲከፍል እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫወተበት እለት ደግሞ የክለቡ ደጋፊዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ጥላ ፎቅ የሚገኙትን 22 የፕላስቲክ ወንበሮችን ስለመስበራቸው ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ክለቡ የተሰበሩትን ወንበሮች እንዲያሰራ ወይም የዩኒቨርስቲው አሰተዳደር የሚያቀርበውን የንብረትን ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል።