ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ አሰልጣኝ አሰናብቷል

በፕሪምየር ሊጉ ደካማ የውድድር ዘመን እያሳለፈ የሚገኘው አንጋፋው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በያዝነው ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ከአሰልጣኙ ጋር መለያየቱ ታውቋል።
\"\"
በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ በድጋሚ ከታችኛው የሊግ ዕርከን በማደግ በሊጉ ላይ እየተካፈለ የሚገኘው አንጋፋው ክለብ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ አሰልጣኝ አሰናብቷል። ከከፍተኛ ሊጉ ባሳደገው አሰልጣኝ ክፍሌ ቦልተና እየተመራ በፕሪምየር ሊጉ ጥቂት ጉዞን ካደረገ በኋላ አሰልጣኙን ከመንበሩ በማንሳት ረዳቱ የነበሩትን ገዛኸኝ ከተማን በቦታው በመተካት ውድድሩን ሲያከናውን የነበረው ክለቡ አሁን ደግሞ አሰልጣኝ ገዛኸኝ የተጣለባቸውን ውጤት የማስመዝገብ ውጥን በአግባቡ እየፈፀሙ አይደለም በማለት በዛሬው ዕለት ማሰናበቱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ኤሌክትሪክ በሊጉ ለመቆየት በሁለተኛው ዙር በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ሀገር ዜግነት ያላቸውን ተጫዋቾች ማስፈረም ቢችልም ቡድኑ ከወራጅ ቀጠናው ፈቀቅ ማለት ሳይችል በአስር ነጥቦች በደረጃ ሰንጠረዡ 15ኛ ላይ ተቀምጦ ይገኛል።
\"\"
ክለቡ በቀጣይ ዋና አሰልጣኝ እስኪሾምለት ድረስ ረዳት አሰልጣኝ የነበረው ስምዖን አባይ ጊዜያዊ ዋና አሰልጣኝ በመሆን እንዲመሩት ተመድበዋል።