የኢ ቢ ሲ የአጋር ተቋማት የእግርኳስ ውድድር እጣ ማውጣት መርሐ-ግብር ተካሂዷል

የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን አዲሱን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ምርቃት አስመልክቶ አጋር ተቋማት የሚሳተፉበት የእግርኳስ ውድድር አዘጋጅቷል።

የሀገራችን ብሔራዊ ጣቢያ የሆነው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ ሸጎሌ አካባቢ ያስገነባውን አዲሱን የሚዲያ ኮምፕሌክስ ምርቃትን በማስመልከት ስምንት አጋር ተቋማት የሚሳተፉበት የወዳጅነት የጥሎ ማለፍ እግርኳስ ውድድር ለማካሄድ ዝግጅቱን ያገባደደ ሲሆን በዛሬው ዕለትም በአዲሱ መስሪያ ቤቱ የዕጣ ማውጣት ሥነ-ስርዓት አከናውኗል።

\"\"

ረፋድ ላይ በተከናወነው ሥነ-ስርዓት ላይ የኢቢሲ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ፍሰሀ ይታገሱ፣ የተቋሙ አምባሳደር ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ፣ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የአጋር ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የብዙሃን መገናኛ አባላት ተገኝተዋል። የእጣ ማውጣቱ ከመከናወኑ በፊት ደግሞ አቶ ፍሰሀ እና አቶ ነብዩ መጠነኛ ገለፃ አድርገዋል።


በቅድሚያ አቶ ፍሰሀ አዲሱ መስሪያ ቤት በአጋሮች ድጋፍ እንደተገነባ ገልፀው ከተቋሞቹ ጋር ያለውን ግንኙነት በስፖርት ለማጠናከር ይህ ውድድር እንደተዘጋጀ አመላክተው በውድድሩ ከትብብር ወደ ፉክክር እንደሚገባም ገልፀዋል። አቶ ነብዩ አስከትለው የስፖርትን ዓለም ከኢትዮጵያውያን ጋር ያቆራኘው ኢቲቪ ወደ አዲስ ምዕራፍ ሲሸጋገር በስፖርት ማብሰሩ ትልቅ ነገር እንደሆነ ገልፀው በግቢውም ያሉት የስፖርት ማዘውተሪያዎች ለሀገር ለሀገር ትልቅ ትቅም እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

በውድድሩ ላይ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሮሽን፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ፣ ኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ ሀላፊዎች የሚሳተፉ ይሆናል።

\"\"

በስፍራው በክብር እንግድነት የተገኙት የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዕጣውን አውጥተው በመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከኢቢሲ፣ ገቢዎች ሚኒስቴር ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከኢትዮጵያ መድን እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም ከኢትዮጵያ ልማት ባንክ ጋር ተደልድለዋል። ውድድሩም ከነገ በስትያ በአዲሱ የኢቢሲ የእግርኳስ ሜዳ የሚጀመር ይሆናል።

በመጨረሻ ጎፈሬ ያዘጋጀው የመወዳደሪያ ትጥቅ ለስምንቱም ቡድኖች ተሰጥቶ አዲሱን መስሪያ ቤት የማስጎብኘት መርሐ-ግብር የከናውኖ የዕለቱ ሥነ-ስርዓት ተጠናቋል።