ለገጣፎ ለገዳዲ እና ሀድያ ሆሳዕና በተገናኙበት የሳምንቱ ቀዳሚ ጨዋታ 0-0 ተለያይታዋል።
ለገጣፎዎች ባለፈው ሳምንት ከተሸነፈው ስብስብ አቤል አየለ ፣ ያሬድ ሀሰን እና ጋብርኤል አህመድን በመዝገቡ ቶላ ፣ ፍቅሩ አለማየሁ ፣ ሱራፌል ዐወል ለውጠው ገብተዋል። ሀድያዎች በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ከተጠቀሙበት ቀዳሚ አሰላለፍ ዘካርያስ ፍቅሬ እና ስቴቨን ናይራኮን በፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን እና ራምኬል ሎክ ቀይረው ገብተዋል።
በጨዋታው የመጀመርያ ደቂቃዎች ተመጣጣኝ ፉክክር በነበረው እንቅስቃሴው ሁለቱም ቡድኖች ተመሳሳይ አጨዋወት የተከተሉበት ነበር ፤ የኋላኋላ ግን ሀድያዎች ከተጋጣምያቸው በተሻለ መንቀሳቀስ ችለዋል። በአጋማሹ የተሻሉ የነበሩት ሀድያዎች በቁጥር ጥቂት የማይባሉ የግብ ዕድሎች ፈጥረው ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ውስጥ ካሌብ በየነ ከመስመር አሻግሮት ራምኬል ሎክ በጥሩ አዟዟር መትቶት ግብ ጠባቂው የመለሰው ኳስ እና ብርሀኑ በቀለ ከርቀት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።
በመጀመርያው አጋማሽ ደካማው የለገጣፎ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ዕድሎች ለመፍጠር ያልተቸገሩት ነብሮች ብልጫ በፈጠሩባቸው ደቂቃዎችም ተጨማሪ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። ከነዚህም ፀጋዬ ለማሻማት ወደ ሳጥን የላካት ኳስ መዝገቡ አቅጣጫዋን አስቀይሯት አግዳሚውን ለትማ የወጣችው ኳስ ፤ ፍሬዘር ከመስመር የተሻማው ኳስ ተጠቅሞ በግምባር ያደረጋት ሙከራ እና ብሩክ ማርቆስ ከቅጣት ምት መትቶ ግብ ጠባቂው እንደምንም ያወጣት ኳስ ነብሮቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙኩራዎች ነበሩ። ጥሩ አጀማመር ካደረጉ በኋላ በጀመሩበት መንገድ መቀጠል ያልቻሉት ለገጣፎዎችም በመሐመድ አበራ አማካኝነት በመልሶ ማጥቃት አንድ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።
ከመጀመርያው አጋማሽ በተሻለ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ሁለተኛ አጋማሽ ጥቂት ሙከራዎች የተደረጉበት ነበር። በለገጣፎ በኩል አማኑኤል አረቦ ከመስመር የተሻገረለት ኳስ በጥሩ የመጀመርያ ንክኪ ካበረደ በኋላ ከመሞከሩ በፊት ተከላካዮች ያወጡት ኳስ የአጋማሹ ወርቃማ ዕድል ነበር ፤ ተስፋዬ ነጋሽ ከርቀት ያደረገው ሙከራ እና መሐመድ በመጨረሻው ደቂቃ ያልተጠቀመባት ዕድል ሌሎች የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው።
መጀመርያው አጋማሽ በሁሉም ረገድ ከተጋጣሚያቸው የተሻሉ የነበሩት ሀድያዎች በሁለተኛው አጋማሽ ብልጫን ማስቀጠል አልቻሉም ፤ ሆኖም ግን ሙከራ ከማድረግ አልቦዘኑም። ከነዚህም ብርሀኑ በቀለ ተጫዋቾች አልፎ በቀጥታ መቶ ሚክያስ ያወጣው ኳስ እና ካሌብ በየነ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ። ነብሮቹ በመጨረሻው ደቂቃ መሪ ለመሆን ተቃርበው ነበር ፤ ሙከራውም ሬችሞንድ አዶንጎ ከቆመ ኳስ የተገኘውን ኳስ ተጠቅሞ መትቶ ፍቅሩ ዓለማየሁ እንደምንም ከመስመር መልሶታል።
ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸው የሰጡት የሀድያ ሆሳዕና አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ጨዋታው ጠንካራ እንደነበር ገልፀው ዕድሎች አለመጠቀማቸው ዋጋ እንዳስከፈላቸው ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ከቦታው የማይንቀሳቀስ የተጋጣሚ ተከላካይ ክፍል ጨዋታው እንዳከበደው ገልፀዋል። የለገጠፎ ለገዳዲ አሰልጣኝ ዘማርያም ወልደግዮርጊስ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር ጠቅሰው የማሸነፍ ፍላጎታቸው አሪፍ እንደነበር ተናግረዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ተከላካይ ክፍል በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ እንዳደረገ በመግለፅ ከሁሉም በላይ የማሸነፍ ፍላጎታቸው የጨዋታው በጎ ጎን እንደነበር አውስተዋል።