የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | የ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ዛሬ በተደረጉ ሦስት ጨዋታዎች ሲጀመር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ቦሌ ክ/ከተማ ድል ተቀዳጅተዋል።

\"\"

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 7-0 ድሬዳዋ ከተማ

04፡00 ላይ በተደረገው የሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች ጥሩ መንቀሳቀስ ችለው የነበሩት ድሬዎች 4ኛው ደቂቃ ላይ የጨዋታውን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። ወርቅነሽ ሚልሜላ ከቅጣት ምት ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስባት በአንድ ደቂቃ ልዩነት የንግድ ባንኳ መሳይ ተመስገን ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ የግብ ዕድሏን ሳትጠቀምበት ብትቀርም 11ኛው ደቂቃ ላይ ብዙዓየሁ ታደሠ ከግራ መስመር ባሻገረችላት ኳስ ግብ አስቆጥራ ንግድ ባንክ ጨዋታውን እንዲመራ አስችላለች። 16ኛው ደቂቃ ላይ ብርቱካን ገብረክርስቶስ ለመዲና ዐወል አመቻችታ ስታቀብል መዲና ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ መልሳባታለች። ያንኑ ኳስ ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ሆና ያገኘችው ናርዶስ ጌትነት  ያደረገችውን ሙከራ ተከላካይዋ አብነት ለገሠ ስታግድባት 26ኛው ደቂቃ ላይ ግን አረጋሽ ካልሳ ከ ሰናይት ቦጋለ በተቀበለችው ኳስ ከግብ ጠባቂዋ ከፍ አድርጋ ድንቅ ግብ በማስቆጠር የቡድኗን መሪነት ስታጠናክር በድሬዳዋ ከተማ በኩል የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በግሏ ጥረት ስታደርግ የነበረችው ወርቅነሽ ሚልሜላ 30ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ስትመልስባት 37ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በጨዋታው ዕድለኛ ያልነበረችው የንግድ ባንኳ መዲና ዐወል ከግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ሳትጠቀምበት የቀረችው ኳስ አስቆጪ አጋጣሚዋ ነበር።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ንግድ ባንኮች ፍጹም ብልጫውን ሲወስዱ 48ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ስትመልስባት ኳሱን ያገኘችው አረጋሽ ካልሳ በአጨቃጫቂ ሁኔታ አስቆጥራዋለች። በሁለተኛው አጋማሽ እጅግ የተቸገሩት ድሬዎች የተሻለውን ሙከራቸውን 52ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ቤዛዊት ንጉሤ ከረጅም ርቀት ያደረገችውን ግሩም ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ታሪኳ በርገና መልሳባታለች። 56ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ከቀኝ መስመር ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስባት ያንኑ ኳስ ከሳጥን አጠገብ ላይ ሆና ያገኘችው ሰናይት ቦጋለ በግሩም ሁኔታ መረቡ ላይ ስታሳርፈው 67ኛው ደቂቃ ላይም መዲና ዐወል ከቀኙ የሜዳ ክፍል ውስጥ ሆና ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘችው ራሷ ሰናይት ቦጋለ ተረጋግታ መረቡ ላይ ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችላለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት አረጋሽ ካልሳ ጥሩ ሙከራ አድርጋ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ሲመለስባት 72ኛው ደቂቃ ላይ የምሥራች ላቀው ተቀይራ በገባችበት ቅፅበት በሁለት ንክኪዎቿ ሁለት ግሩም ሙከራዎችን ማድረግ ችላ ነበር። የመጀመሪያ ሙከራዋ የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ሲወጣ ሁለተኛ ሙከራዋ በግብ ጠባቂዋ ጥሩ ቅልጥፍና መክኖባታል። ሆኖም ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረጓን የቀጠለችው የምሥራች ላቀው 82ኛው ደቂቃ ላይ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ያገኘችው ሎዛ አበራ ከግብ ጠባቂዋ ከፍ አድርጋ ግብ ስታስቆጥር 89ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ የጨዋታው ኮከብ የነበረችው ሰናይት ቦጋለ ለራሷ ሦስተኛ ለቡድኗ ሰባተኛ ግብ በማስቆጠር ሐትሪክ መሥራት ስትችል ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 7-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ 0-2 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ዐ8፡00 ላይ በተደረገው የቀኑ ሁለተኛ መርሐግብር ቀዝቃዛ የነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ያልተደረገበት ነበር። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል 12ኛው ደቂቃ ላይ ብዙዓየሁ ጸጋዬ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ዐይናለም ዓለማየሁ በግራ እግሯ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ሸዊት አበረ ስትመልስባት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ የንፋስ ስልኳ ዓየም በየቻ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ በረከት ዘመድኩን መልሳባታለች። ጨዋታው በሁለቱም በኩል በሚታዩ የሚቆራረጡ ቅብብሎች አሰልቺ እየሆነ ሲሄድ 39ኛው ደቂቃ ላይ የጊዮርጊሷ ሶፋኒት ተፈራ ባልታሰበ የማጥቃት እንቅስቃሴ ባቀበለቻት ኳስ ተከላካዮችን አታልላ ማለፍ የቻለችው ዐይናለም ዓለማየሁ ያደረገችውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂዋ ሸዊት አበረ ይዛዋለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እንደተቀዛቀዘ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩት ጊዮርጊሶች 65ኛው ደቂቃ ላይ ሶፋኒት ተፈራ አንድ ተከላካይ በመቀነስ ከሳጥን አጠገብ ባስቆጠረችው ብቃቷን ያስመሰከረ ድንቅ ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት የተቸገሩት ንፋስ ስልኮች በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድላቸውን 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ በሬዱ በቀለ ከሳጥን ውጪ ያደረገችው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል። ሆኖም ጊዮርጊሶች 84ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ ሲያስቆጥሩ ኢየሩስ ወንድሙ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆና ወደ ውስጥ ያሻገረቸውን ኳስ ያገኘችው ትዕግሥት ዘውዴ ተቀይራ በገባችበት ቅጽበት መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቦሌ ክ/ከተማ 3-0 አዳማ ከተማ

10፡00 ላይ የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር በቦሌ ክ/ከተማ እና በአዳማ ከተማ መካከል ሲደረግ በመጀመሪያው አጋማሽ የቦሌ ክ/ከተማ ፍጹም የበላይነት የታየበት ነበር። ንግሥት በቀለ 10ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ 14ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ጤናዬ ለታሞ ባሻገረችላት ኳስ ሳጥን ውስጥ ባስቆጠረቻቸው ግቦች ቦሌን በሁለት ግብ ልዩነት መሪ ስታደርግ 21ኛው ደቂቃ ላይም መሬት ለመሬት ጥሩ ሙከራ አድርጋ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። ከጨዋታው የመጀመሪያ ሰዓት አርፍደው የደረሱት እና ምንም ዓይነት የመጫወት ፍላጎት ያልነበራቸው አዳማዎች 33ኛው ደቂቃ ላይ ትዕግሥት ዘውዴ ልትጠቀምበት ሞክራ ግብ ጠባቂዋ ሊንጎ ዑማን ወጥታ ከመለሰችው ኳስ ውጪ የተጋጣሚ ሳጥን ናፍቋቸው አጋማሹን አጠናቀዋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 54ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ ኢርኮ ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ግሩም ግብ አስቆጥራ የቦሌን መሪነት ማስፋት ስትችል 72ኛው ደቂቃ ደቂቃ ላይ አዲስ ንጉሤ ከቅጣት ምት ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም ስንታየሁ ኢርኮ እና ንግሥት በቀለ በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ የነበረችው ስንታየሁ ኢርኮ ወደ ግብ ሞክራው በግብ ጠባቂዋ መክኖባታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ቦሌዎች ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር ቢችሉም በተደጋጋሚ ጊዜ የታየባቸው ከጨዋታ ውጪ መሆን የግብ መጠናቸውን ከፍ እንዳያደርጉ ምክንያት ሆኗቸው ታይቷል። ሆኖም ጨዋታው በቦሌ ክ/ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።