የሊጉ 21ኛ ሳምንት የነገ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
አርባምንጭ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በሰንጠረዡ የተለያየ ፅንፍ ላይ የሚገኙት አዞዎቹ እና ፈረሰኞቹ ነገ 09:00 ላይ ይፋለማሉ።
የወራጅ ቀጠናው መግቢያ ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ነገሮችን የሚቀይርለት ድል ያስፈልገዋል። በእርግጥ ካለው የነጥብ ቅርርብ አንፃር አዞዎቹ ሦስት ነጥብ ማሳካት ከቻሉ ከአደጋው ዞን ይልቅ ለሰንጠረዡ አጋማሽ መቅረብ ይቻላቸዋል። ይህንን ለማድረግ ግን ከሊጉን መሪ ከበድ ያለ ፈተና ይጠብቃቸዋል። በመጨረሻ ጨዋታቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ የተጋሩት አርባምንጮች ቀድመው መሪ ቢሆኑም አስጠብቀው መውጣት አልቻሉም። ዘንድሮ ያስተናገዱት የጎል ብዛት (28) ሲታይም አዞዎቹ የቀደመ ጠንካራ ጎናቸውን ያጡ ይመስላል። ለወትሮው በጠንካራ መከላከል የሚታወቀው ቡድኑ የተሻለ የማጥቃት እሳቤን ተላብሶ ቢታይም በአስፈላጊ ጊዜያት ላይ የግብ ክልሉን ያለማስደፈር ብቃቱ እንደከነገ ዓይነት ጨዋታዎች በፊት በእጅጉ ያስፈልገዋል።
ከአራት ተከታታይ ድሎች በኋላ በሲዳማ ቡና ነጥብ ጥለው የነበሩት ፈረሰኞቹ ሁለት ተከታታይ ድሎችን አሳክተው ለነገው ጨዋታ ይደርሳሉ። በተለይም ባለፉት ዓመታት ሲፎካከራቸው ከነበረው ፋሲል ከነማ ጋር ያደረጉትን ጨዋታ በድል መወጣታቸው የቡድኑን ተነሳሽነት እንደሚጨምረው ዕሙን ነው። ሆኖም ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ባህር ዳር ከተማ የነጥብ ልዩነታቸው ከሦስት እንዳይሰፋ በማድረጉ የነገው ጨዋታም እንዳለፈው ሳምንት ሁሉ ለጊዮርጊሶች ወሳኝ ይሆናል። የፋሲሉ ጨዋታ በድል ይቋጭ እንጂ ምኞት ደበበ ፣ ሱለይማን ሀሚድ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ቸርነት ጉግሳ ግጭቶችን አስተናግደው የነበረ መሆኑ የቡድኑ ፈተና ይመስላል። የእነዚህ ተጫዋቾች ለነገ መድረስ ገና እርግጥ ባይሆንም በጥሩ ዜናነት ሀይደር ሸረፋ እና አማኑኤል ተርፉ ከጉዳት ተመልሰዋል።
ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ በ17 አጋጣሚዎች እርስ በእርስ የተፋለሙ ሲሆን በዚህም ቅዱስ ጊዮርጊስ 11 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ 2 ጊዜ ድል አድርጎ የተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።
ጨዋታውን አዳነ ወርቁ በዋና ዳኝነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ሙሉነህ በዳዳ በረዳትነት ተካልኝ ለማ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው በጋራ ይመሩታል።
ፋሲል ከነማ ከ ሀዋሳ ከተማ
ያሳለፍነውን የጨዋታ ሳምንት በተመሳሳይ የ1-0 ሽንፈት የደመደሙት እና ወጥ አቋም ለማሳየት እየተቸገሩ የሚገኙት ፋሲል እና ሀዋሳ ነገ ምሽት እርስ በእርስ ይገናኛሉ።
የውድድር ዓመቱን ሰባተኛ ሽንፈት በቅዱስ ጊዮርጊስ እጅ ያስተናገደው ፋሲል ከነማ በሰንጠረዡ ወገብ ላይ ይገኛል። ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች በሁለቱ ብቻ ሦስት ነጥብ ማሳካት የቻሉት ፋሲሎች በእርግጥም ተነቃቅተው የታዩባቸው በተለይም የማጥቃት ሂደታቸው የተሻሻሉባቸው ቅፅበቶች ቢታዩም በቀጣይነት ማስኬድ ላይ ተቸግረው ይታያሉ። ቡድኑ ከነበረው ደካማ የውድድር ዓመት ጅማሮ አንፃር በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ከፊት የሚገኙት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማን ማሸነፍ አለመቻሉ በአዕምሮ ረገድ ሊያገኝ ይችል የነበረውን የበላይነት አሳጥቶታል። ከዚህ አንፃር ፋሲሎች እንደ አምናው ሁሉ በቀሪ አስር ጨዋታዎች የውድድር ዘመናቸውን ማቅናት ለመጀመር የነገው ጨዋታ እጅግ አስፈላጊያቸው ይሆናል።
ሀዋሳ ከተማም እንደተጋጣሚው ሁሉ ሜዳ ላይ የሚያሳየውን ጥሩ አቋም በተከታታይ ጨዋታዎች የማስቀጠል ድክመት እያሳየ ይገኛል። ከኢትዮጵያ ቡናው የአቻ ውጤት በኋላ ቡድኑ በአዳማ ከተማ እና በወልቂጤ ከተማ ላይ ድል ያስመዘገበበትን ሂደት መድገም ባለመቻሉ በድሬዳዋ ከተማ ለሽንፈት ተዳርጓል። ከውጤቱ ባሻገር በጨዋታው አንድ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ብቻ ማድረጉም እንዲሁ ከዚያ ቀደም ወልቂጤን ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ከማሸነፉ አንፃር ሲታይ የማጥቃት መዋቅሩ ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ሆኖ አልፏል። ሀዲያ ሆሳዕና ዛሬ ነጥብ መጣሉን ተከትሎ ሀዋሳ ከተማ ወደ አራተኛነት ከፍ የማለት ዕድልን ይዞለት በሚመጣው የነገው ጨዋታ በተለይም በፊት መስመሩ የትኛውን መልክ ተላብሶ ይመጣል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ይሆናል።
በጨዋታው የሀዋሳ ከተማዎቹ ሙጂብ ቃሲም እና መድሀኔ ብርሀኔ ከጉዳት ሲመለሱ ረዘም ያለ ጉዳት የገጠማቸው ወንድማገኝ ኃይሉ እና ቀዶ ጥገና ያደረገው ብርሀኑ አሻሞ በጉዳት አይኖሩም። በፋሲል ከነማ በኩል ደግሞ ዓለምብርሀን ይግዛው በቅጣት ፍቃዱ ዓለሙ ደግሞ በጉዳት ጨዋታው ያልፋቸዋል።
ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም በ11 አጋጣሚዎች ሲገናኙ ሀዋሳ ከተማ አራት ፋሲል ከነማ ደግሞ ሦስት ድሎችን አሳክተዋል። ቀሪዎቹ አራት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል።
12:00 ላይ በሚጀምረው ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ በመሐል ዳኝነት ዳንኤል ጥበቡ እና አስቻለው ወርቁ በረዳትነት ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተሰይመውበታል።