ሪፖርት| ፈረሰኞቹ አዞዎቹን ረቱ

ጠንካራ ፉክክር በታየበት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተጋጣሚው አርባምንጭ ከነማን አንድ ለባዶ አሸንፏል።

አዞዎቹ ከባለፈው ሳምንት ስብስብ አንዷለም አስናቀ ፣ መላኩ ኤልያስ እና አሸናፊ ተገኝን በላርዬ አማኑኤል ፣ መሪሁን መስቀለ እና እንዳልካቸው መስፍን ለውጠው ገብተዋል። ፈረሰኞቹ በበኩላቸው ባለፈው ሳምንት ድል ካደረገ ስብስብ ሱሌማን ሀሚድ ፣ ምኞት ደበበ እና ጋቶች ፓኖምን በሄኖክ አዱኛ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና አማኑኤል ተርፉ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

ሁለት መልክ በነበረው የመጀመርያው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች አዞዎቹ ሁለቱም መስመሮች ተጠቅመው ፈረሰኞቹን ለማጥቃት ጥረት ያደረጉበት ፤ የተቀሩት ደቂቃዎች ደግሞ ፈረሰኞቹ ያንሰራሩበት አጋማሽ ነበር። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ጫና ፈጥረው የተጫወቱት አዞዎቹም ጥቂት የማይባሉ ያለቀላቸው ዕድሎች አምክነዋል። ከነዚህም ተመስገን ደረስ ከግብ ጠባቂው በረጅሙ ተመትቶ አህመድ ሁሴን ታግሎ ያገኛት ኳስ ተጠቅሞ ሞክሯት ግብ ጠባቂው ያዳናት ኳስ እና ኤሪክ ካፓይቶ ከመስመር አሻግሮት የጊዮርጊስ ተከላካዮች እና ግብ ጠባቂው እንደምንም ጨርፈው ያወጡት አዞዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡ ሙከራዎች ናቸው።


በአጋማሹ ደካማ አጀማመር በማድረግ የኋላ ኋላ ያንሰራሩት ፈረሰኞችም ዕድሎች ፈጥረዋል ፤ ዳዊት ተፈራ በጥሩ መንገድ ያሻገራት ኳስ ተጠቅሞ ኦሮ አጎሮ ያደረጋት ሙከራ ቡድኑ ከፈጠራቸው ዕድሎች የተሻለች ነበር ፤ አጎሮ ከመአዘን የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራም በአጋማሹ ሌላ የምትጠቀስ ሙከራ ነች።

ቀዝቃዛ በነበረው ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ደካማ የማጥቃት አጨዋወት እና እጅግ ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታዩበት ነበር። አጋማሹም እስከ ስልሳ አንደኛው ደቂቃ ምንም ሙከራ ሳያስተናግድ ቢቆይም ፈረሰኞቹ በተጠቀሰው ደቂቃ በኦሮ አጎሮ የረዥም ርቀት ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። አጥቂው ሄኖክ አዱኛ ያቀበለውን ኳስ በግራ እግሩ አክርሮ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን መሪ ማድረግ የቻለው።


ፈረሰኞቹ በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በአጎሮ እና አዲስ ጥሩ ተግባቦት ተፈጥሮ ግቧን ያስቆጠረው አጥቂ ሞክሮት ተከላካዮች ተደርበው ያወጡት ሙከራም ልዩነቱ ለማስፋት የተቃረቡበት አጋጣሚ ነበር።

ጨዋታው በፈረሰኞቹ መሪነት ከቀጠለ በኋላ አቻ ለመሆን የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ያሳዩት አዞዎቹ በአህመድ ሁሴን አማካኝነት አቻ ለመሆን ተቃርበው ነበር። አጥቂው እንዳልካቸው በጥሩ መንገድ ያሻገረለት ኳስ ተጠቅሞ ነበር ከረዥም ርቀት ሙከራ ያደረገው።

\"\"

የአርባምንጩ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጨዋታው ከሞላ ጎደል ጥሩ እንደነበር ገልፀው ተጋጣምያቸው በሜዳቸው እንደፈለገ እንዳይጫወት እንዳደረጉትም ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በማጥቃቱ በኩል እንደተፈለገ ጥሩ እንዳልነበሩ ጠቅሰዋል። የቅዱስ ጊዮርጊስ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው \”ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር\” ካሉ በኋላ ጨዋታው ጥንቃቄ የተሞላበት ጨዋታ እንደነበር ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም \”በሁለተኛው አጋማሽ በተሻለ ወደ ግብ ሄደናል\” ብለዋል።