ጋናዊው ግብ ጠባቂ ራሱ ላይ ባስቆጠራት ብቸኛ ጎል ፋሲል ሀዋሳን 1-0 አሸንፏል።
ከሽንፈት መልስ የተገናኙት ሁለቱ ቡድኖች ባደረጓቸው ለውጦች ፋሲል ከነማ ሽመክት ጉግሳ ፣ ሀብታሙ ገዛኸኝ እና ሱራፌል ዳኛቸውን በከድር ኩሊባሊ ፣ ዱላ ሙላቱ እና ታፈሰ ሰለሞን ሲተካ ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው ፀጋአብ ዮሐንስ ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ አቤኔዘር ኦቴ እና እዮብ ዓለማየሁን በሰለሞን ወዴሳ ፣ ሰዒድ ሀሰን ፣ መድሀኔ ብርሀኔ ሙጂብ ቃሲም ተተክተው ገብተዋል።
ጨዋታውን ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ያስጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች የመጀመሪያዎቹን አስር ያህል ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በሽግግር የጨዋታ መንገድ በፍጥነት ቶሎ ቶሎ የደረሱበት ቢሆንም ጥራት ያላቸውን አጋጣሚወች በመፍጠሩ ረገድ ግን አልታደሉም። 2ኛው ደቂቃ ላይ አብዱልባሲጥ ከማል ወደ ቀኝ የሜዳው ክፍል የደረሰውን ኳስ ወደ ሳጥን ገፍቷት ከገባ በኋላ መሬት ለመሬት አሳልፎ ዓሊ ሱለይማን ተንሸራቶ ባመለጠችው ቅፅበት ሙከራን በማድረግ ቀዳሚ ሆነዋል። ኳስን በሚያገኙበት ወቅት በጥልቀት ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ሲደርሱ ይታይ እንጂ ኢላማውን የጠበቀ ዕድልን በማግኘቱ ያልተሳካላቸው ሀዋሳዎች በሌላ ሙከራቸው በዓሊ በረጅሙ ከተከላካይ ጀርባ የተጣለለትን ኳስ የሳማኪን መውጣት ተመልክቶ ወደ ጎል ሲመታ የግቡን ቋሚ ታካ ኳሷ ከወጣች በኋላ ፋሲሎች ጨዋታውን ወደ ራሳቸው ቁጥጥር ስር አድርገውታል።
ከአስራ አምስት ደቂቃዎች መልስ ኳስን በመቆጣጠር በይበልጥ ወደ ግራ ባዘነበለ ቅርፅ ወደ ጨዋታ የተመለሱት አፄዎቹ ናትናኤል እና ማውሊን በዋናነት ተጠቅመው ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ጥረዋል። 11ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት አምሳሉ ጥላሁን ሲያሻማ አስቻለው ታመነ ደርሶት ቢሞክራትም የግቡ ቋሚ ብረት አግዞት መሐመድ ሙንታሪ ተቆጣጥሯታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ ፋሲሎች በናትናኤል ፣ ዱላ እና ማውሊ ሙከራን አድርገው ነበር። በተለይ 25ኛው ደቂቃ ኦሴ ማውሊ ከግራ የሀዋሳ የሜዳ ክፍል መትቶ መሐመድ ሙንታሪ የያዘበት አጋጣሚ የጎላችዋ ነበረበች። ሀዋሳ ከተማ ከቅጣት ምት በኤፍሬም ፣ ፋሲሎች በማውሊ አማካኝነት ዕድልን አግኝተው ማየት ብንችል በጠሩ ሙከራዎች ያልታጀበው ደካማው አጋማሽ ያለ ጎል ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ ፋሲሎች በተዝናኖት ኳስን በመቀባበል ሀዋሳ ላይ የጨዋታ የበላይነቱን መያዝ ሲችሉ በአንፃሩ ሀዋሳ በጥብቅ መከላከል ነገር ግን ኳስን ሲያገኙ በመልሶ ማጥቃት የዓሊ ሱለይማንን ፍጥነት ተጠቅመው ጎልን ለማግኘት የጣሩበት ሒደት ተመልክተናል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ሙጂብ ቃሲም ከኤፍሬም አሻሞ ከሳጥን ውጪ ሞክሮ ሳማኪ ሚካኤል ካወጣበት ሙከራ በኋላ ሀዋሳዎች በቀላሉ የፋሲል አጥር መሻገር ተስኗቸዋል። በተረጋጋ የጨዋታ መንገድ ከመስመር አልያም ከመሐል ክፍሉ በሚፈጠሩ መነሻቸውን አድርገው ቀዳዳ ፍለጋን የቀጠሉት ፋሲል ከነማዎች 57ኛው ደቂቃ ላይ ከጎል ጋር ተገናኝተዋል። ከማዕዘን ታፈሰ አስጀምሮ ለአምሳሉ ሰጥቶት አምበሉ ወደ ውስጥ ሲያሻማ ጋናዊው ግብ ጠባቂ በቀላሉ ከተቆጣጠረው በኋላ በድጋሚ ኳሷን በመልቀቁ እንደገና ለመያዝ ሲሞክር በራሱ መረብ ላይ አሳርፏታል።
ፋሲል ከነማዎች ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ተጨማሪ ጎልን ከመረብ ጋር ለማገናኘት በናትናኤል እና ኦሴ ማውሊ አማካኝነት ግልፅ ዕድልን ፈጥረው ታይተዋል። በተለይ ናትናኤል ከሙንታሪ ጋር ተገናኝቶ የሞከራትን ግብ ጠባቂው ያዳነበት ተጠቃሿ ሙከራ ነች። መከላከል ላይ ትኩረት ቢያደርጉም ኳስን ሲያገኙ በተሻጋሪ ፈጣን ሽግግር ዓሊን ይጠቀሙ የነበሩት ሀዋሳዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ የሚያስቆጭ አጋጣሚን ሙጂብ አምክኗል። አጥቂው ከዓሊ ሱለይማን የደረሰውን ኳስ በቀላሉ ከመረብ አገናኘ ተብሎ ሲጠበቅ ነው ሳማኪ ሚካኤል የመለሰበት። ጨዋታውም የሀዋሳው ግብ ጠባቂ መሐመድ ሙንታሪ ራሱ ላይ ያገባት ብቸኛ ጎል ፋሲል ከነማን 1ለ0 አሸናፊ አድርጋለች።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ ጥሩ ፉክክር እና የታክቲክ ፍልሚያ የታየበት ጨዋታ እንደ ነበር ጠቅሰው ወደ ፊት በመሄድ ቡድናቸው ብዙ አጋጣሚን የፈጠረ ቢሆንም መሸነፍ እንደቻሉ ጠቁመው በእንቅስቃሴው እንዳልተከፉ ፣ በቡድናቸውም ለውጦች መኖራቸውን ገልፀው ማሸነፍም ይገባን ነበርም ሲሉ ተደምጠዋል። በግብ ጠባቂ ስህተት ጎል መቆጠሩም እንዳላስከፋቸውም ጭምር በንግግራቸው አካተዋል። የፋሲሉ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በበኩላቸው ሀዋሳ ጠንካራ ቡድን መሆኑን ከገለፁ በኋላ በመስመር አጨዋወት በዓሊ አማካኝነት ዕድሎችን ለመፍጠር መሞከራቸውን እንዲሁም ቡድኑ ጠንካራ መሆኑን ተናግረው ኳስን ይዘው በመጫወት ድል እንዳሳኩም ያሰቡትም መንገድ መሳካቱን ተናግረዋል።