ዛሬ በተጠናቀቀው 24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ እና መቻል ድል ሲቀናቸው የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የይርጋጨፌ ቡና ጨዋታ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ሀዋሳ ከተማ 1-0 አርባምንጭ ከተማ
በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ሁለት መልክ በነበረው የመጀመሪያው አጋማሽ በመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረስ የተሻሉ የነበሩት አርባምንጮች ነበሩ። ሆኖም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው 45ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ታምሩ ከረጅም ርቀት የቅጣት ምት ካደረገችው ሙከራ ውጪም በአጋማሹ ተጠቃሽ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ቀስ በቀስ ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ የመጡት ሀዋሳዎች 26ኛው ደቂቃ ላይ ዙፋን ደፈርሻ ከረጅም ርቀት በመታችውና የግቡን አግዳሚ ታክኮ በወጣው ኳስ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ሲያደርጉ ከአንድ ደቂቃ በኋላም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።
ፀሐይነሽ ጁላ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ቱሪስት ለማ በግንባሯ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ተጭነው መጫወት የቀጠሉት ሀዋሳዎች በረድዔት አስረሳኸኝ አማካኝነት ተጨማሪ ሁለት ሙከራዎችን ማድረግ ችለውም ነበር።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ከተጠበቀበት ፉክክር በተቃራኒው እጅግ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ተጠቃሽ እንቅስቃሴም ያልተደረገበት ነበር። በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን የወሰዱት ሀዋሳዎች ተጭነው መጫወት ቢችሉም ተጨማሪ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ አርባምንጭ ከተማዎች ባልተለመደ ደካማ አቋም ተጠቃሽ እንቅስቃሴ ለማድረግ ተቸግረው ጨዋታውም በሀዋሳ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
አዲስ አበባ ከተማ 0-3 መቻል
ከምሳ መልስ 8 ሰዓት ላይ በተደረገው የዕለቱ ሁለተኛ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲታይበት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ ረገድ የተሻሉ የነበሩት መቻሎች 23ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ምርቃት ፈለቀ ከግራ መስመር ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ መቆጣጠር ተስኗት ስትለቀው ኳሱን ያገኘችው ሴናፍ ዋቁማ ያደረገችውነ ሙከራ ግብ ጠባቂዋ በድጋሚ አስወጥታዋለች። ያው ኳስ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ሲሻማ ያገኘችው ትሁን አየለም በግንባሯ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፋዋለች። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም ሴናፍ ዋቁማ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት አክርራ በመምታት ያደረገችውን ግሩም ሙከራ የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶባታል። በተለይም በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው ከቤተልሔም መንተሎ በሚነሱ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩት አዲስ አበባዎች የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረው አጋማሹ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት መቻሎች በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዋል። 54ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ የተከላካዮችን ስህተት በመጠቀም ግብ አስቆጥራ የመቻልን መሪነት ስታጠናክር 62ኛው ደቂቃ ላይም ለግብ የቀረበ ሙከራ አድርጋ በግብ ጠባቂዋ መክኖባታል። 66ኛው ደቂቃ ላይም በመቻል በኩል ተቀይራ የገባችው ማዕድን ሳህሉ ከሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ አድርጋ ግብ ጠባቂዋ ስርጉት ተስፋዬ ስትመልስባት ያንኑ ኳስ ያገኘችው አብራት ተቀይራ የገባችው ቤዛዊት ተስፋዬ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ የግብ ዕድሏን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ሆኖም ሴናፍ ዋቁማ 80ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በመቻል 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 0-0 ይርጋጨፌ ቡና
10፡00 ላይ በተደረገው የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በመጀመሪያው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች በቁጥር በዝቶ ወደ ተጋጣሚ የግብ ሳጥን ለመድረስ ይርጋጨፌዎች ደግሞ ወደ የራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ ጥቅጥቅ ብለው በመቆም በሚያገኙት ኳስ በተለይም በዳግማዊት ሰለሞን እና መስታዎት አመሎ በመታገዝ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲጥሩ ተስተውሏል። በአጋማሹም በኤሌክትሪኮች በኩል ሁለት ፈታኝ ሙከራዎች ተደርገው ነበር። በቅድሚያም 16ኛው ደቂቃ ላይ ምንትዋብ ዮሐንስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ይዛው የገባችውን ኳስ ለ ትንቢት ሳሙኤል ስታቀብል ትንቢት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ መልሳባታለች። በቀጣይም 26ኛው ደቂቃ ላይ በቀኙ የማጥቂያ መስመራቸው ከ መስከረም ካንኮ የተነሳውን ኳስ ያገኘችው ትንቢት በድጋሚ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ በግሩም ቅልጥፍና አግዳባታለች። የመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይም ኤሌክትሪኮች ሳጥን ውስጥ በርካታ ሙከራ አድርገው አይበገሬ በነበሩት ይርጋጨፌዎች ርብርብ መክኖባቸዋል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 52ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይራ የገባችው የኤሌክትሪኳ ሰብለወንጌል ወዳጆ ከሳጥን ውጪ ያደረገችው ግሩም ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ በኋላ በሁለቱም በኩል ጥድፊያ የበዛበት እንቅስቃሴ ሲያስመለክተን የነበረው ጨዋታ በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ብቻ የጠራ የግብ ዕድል ተፈጥሮበታል። ትዕግሥት ያደታ ያቀበለቻትን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆና ያገኘችው የመስመር ተከላካይዋ ቤተልሔም አስረሳኸኝ ኃይል ባልነበረው ሙከራ የግብ ዕድሏን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።