መረጃዎች | 86ኛ የጨዋታ ቀን

የ21ኛ ሳምንት የሦስተኛ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወልቂጤ ከተማ

የ14 ነጥቦች ልዩነት በመካከላቸው የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ወልቂጤ ከተማ ነገ የሚያደርጉ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር እንደሚደረግበት ይገመታል። ላለመውረድ የሞት ሸረት ትግል እንደሚያደርግ የሚጠበቅ ኤሌክትሪክ እየራቁት ከሚገኙት ክለቦች ያለውን ልዩነት ለማጥበብ ወልቂጤ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ስጋት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመራቅ ብርቱ ትግል ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሊጉ ደረጃ ሰንጠረዥ ውራ ሆኖ የተቀመጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ20 ሳምንታት የሊጉ ጉዞ አንድ ብቻ ድል ያስመዘገበ ብቸኛው ክለብ ነው። እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በውድድር ዘመኑ ለሁለተኛ ጊዜ አሠልጣኙን አሰናብቷል። ቡድኑ በሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር በርከት ያሉ ተጫዋቾችን አስፈርሞ ከባዱን ፈተና ለመጋፈጥ ቢጥርም ውጥኑ ሳይሰምር አሠልጣኝ ገዛኸኝን ሸኝቷል። እርግጥ ቡድኑ በእንቅስቃሴ ደረጃ ያን ያህል መጥፎ ነገር ባያሳይም በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ያለው ስልነት አሁን ላለበት ደረጃ እንዲገኝ ምክንያት ሆኗል። ይህንን ችግሩን በቶሎ ፈቶ ነገ ከናፈቀው ድል ጋር የማይገናኝ ከሆነ ለከርሞ በሊጉ የመቆየቱ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ይሆናል።
\"\"
ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ በፈታኙ የሲዳማ ቡና ፍልሚያ ያሸነፉት ወልቂጤ ከተማዎች በጥሩ የሥነ-ልቦና ልዕልና ላይ ሆነው የነገውን ጨዋታ የሚያደርጉ ይመስላል። ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ማሸነፉ ብቻ ሳይሆን በዚህ ሳምንት ከስሩ የሚገኙት አርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና አለማሸነፋቸው የመውረድ ስጋቱን ትንሽ ያቃልልለታል። የአሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቡድን ያለፉትን ጨዋታዎች በተለይ ግቡን በማስጠበቅ ረገድ ክፍተቶች ያሉበት ይመስላል። በተከታታይ ስድስት ጨዋታዎችም አንድም ጊዜ መረቡን ሳያስደፍር በድምሩ 14 ግቦች አስተናግዷል። ይህንን የኋላ ሽንቁር በቶሎ አስተካክሎ ከስጋቱ ለመሸሽ ደግሞ በማጥቃቱ ረገድ ጠንካራ ተፋላሚ ካልሆነው የኤሌክትሪክ ጨዋታ አንድ ብሎ መጀመር ይገባዋል።

ወልቂጤ ከተማ ብዙአየሁ ሰይፉ ከቅጣት ሲመለስለት አፈወርቅ ኃይሉ እና አንዋር ዱላ ግን ከጉዳታቸው ባለማገገማቸው በነገው ጨዋታ አይጠቀምባቸውም።

ሁለቱ ቡድኖች ዘንድሮ በፕሪምየር ሊግ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ድሬዳዋ ስታዲየም ላይ በተከናወነው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታም ወልቂጤ ከተማ 2ለ1 አሸንፏል።

ጨዋታውን ዮናስ ካሳሁን በዋና ዳኝነት አሸብር ታፈሰ እና መሐመድ ሁሴን በረዳትነት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

ወላይታ ድቻ ከመቻል

11ኛ እና 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወላይታ ድቻ እና መቻል ከታችኛው የስጋት ቀጠና ለመራቅ እርስ በእርስ የሚያደርጉት ፍልሚያ ምሽት 12 ሰዓት ላይ በጠንካራ የአልሸነፍ ባይነት ስሜት ይከናወናል ተብሎ ይታሰባል።

በውጤት ረገድ ቀስ በቀስ እየወረደ የመጣው ወላይታ ድቻ ሳይጠበቅ ከላይኛው ደረጃ ፉክክር በአንዴ ወደ ታችኛው ፍልሚያ ተንሸራቷል። የሊጉ ውድድር ወደ አዳማ ከተማ ከመጣ በኋላ የአጨዋወት ለውጥ በማድረግ ከመከላከል ወደ ማጥቃት አጨዋወት ትኩረት ለመስጠት የሞከሩት ወላይታ ድቻዎች ሀሳባቸው እየሰራ አይመስልም። ለወትሮ በቁጥር በዝቶ ወደ ራሱ የግብ ክልል ዝቅ ብሎ ለተጋጣሚ ቡድን በቀላሉ ዕድሎችን ላለመስጠት ሲጫወት የነበረው ቡድኑም አሁን አሁን ዘርዘር ብሎ በድፍረት ወደ ፊት ጠጋ ብሎ ለመጫወት እየጣረ ነው። ነገርግን በዚህ ሂደት ሀሳቡ ገና በሚገባ ባለመስረፁ በተለይ ከማጥቃት ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ሲቸገር ይታያል። ፈጣን አጥቂዎች ላለው መቻል ደግሞ ይህ ጥሩ አጋጣሚ እንዳይሰጥ መጠንቀቅ የግድ ይላል።
\"\"
ከሦስት ተከታታይ ሽንፈቶች በኋላ በ20ኛ ሳምንት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘውን ኢትዮጵያ መድን ባለቀ ሰዓት ጎል ያሸነፈው መቻል በጥሩ መነቃቃት በጥቂቱ ካለበት የወራጅነት ስጋት በደንብ ለመራቅ የነገው ጨዋታ እንደሚያደርግ ይታሰባል። በተለይ ደግሞ አካባቢው ያሉትን ሁለት ክለቦች በነጥብ ርቆ ለመሄድ ጥሩ አጋጣሚ ስለሆነ በጥሩ ትኩረት ተከታታይ ያሉበትን የድቻ እና ድሬ ጨዋታዎች እንደሚቀርቡ ይገመታል። በውድድር ዓመቱ የወጥነት ችግር ያለበት መቻል ስብስቡ ጥሩ ቢሆንም እስካሁን አስተማማኝ ቡድን መገንባት አልቻለም። በተለይ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር እና የመጠቀም ችግሩን በቶሎ አርሞ ከስጋት ቀጠናው በደንብ ለመራቅ ክፍተቶቹን ጊዜ ሳይፈጅ ማስተካከል አለበት።

መቻል ምንይሉ ወንድሙን በቅጣት ዳግም ተፈራ እና ፍፁም ዓለሙን ደግሞ በጉዳት ምክንያት በነገው ጨዋታ አያገኝም።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም አስራ አምስት ያክል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ወላይታ ድቻዎች ሰባት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ሲይዙ መቻሎች ደግሞ ሦስት ጨዋታ ሲረቱ የተቀሩት አምስት ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ተፈፅመዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ ከረዳቶቹ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና አብዱ ይጥና ጋር ጨዋታውን በጋራ ይመሩታል።