ሪፖርት | ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኋላ በመነሳት ከወልቂጤ ከተማ አንድ ነጥብ አሳክቷል

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐግብር ኢትዮ ኤሌክትሪክ በወልቂጤ ከተማ 2-0 ከመመራት ተነስቶ 2-2 ተለያይቷል።

\"\"

9 ሰዓት ላይ በዋና ዳኛው ዮናስ ካሳሁን ፊሽካ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ተደራጅቶ በመግባት አስደናቂ አጀማመር ማድረግ የቻሉት ኤሌክትሪኮች 7ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። አብዱልራህማን ሙባረክ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ያገኘው ታፈሰ ሠርካ በግንባሩ በመግጨት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው መልሶበታል። ያንኑ ኳስ አጥቂው ፍጹም ገብረማርያም እንዳይጠቀምበትም ተከላካዮቹ ተረባርበው አርቀውታል።

ጨዋታው 10ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ ወልቂጤ ከተማዎች ግብ አስቆጥረዋል። ጌታነህ ከበደ በድንቅ ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ ጥሩ ሩጫ አድርጎ ሳጥን ውስጥ መግባት የቻለው አቤል ነጋሽ  በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። 

\"\"

ኤሌክትሪኮች ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ተጨማሪ የግብ ዕድል ለመፍጠር እስከ 30ኛው ደቂቃ መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም አምበሉ ስንታየሁ ዋለጨ በግሩም ዕይታ ያመቻቸለትን ኳስ ያገኘው ፍጹም ገብረማርያም አደጋ ከመፍጠሩ በፊት የወልቂጤው ግብ ጠባቂ ጀማል ጣሰው ከሳጥን በመውጣት ከልክሎታል።

ወደ አጋማሹ መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ እንደ መጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በተሻለ የጨዋታ ስሜት ላይ መሆን የቻሉት ኤሌክትሪኮች 37ኛው ደቂቃ ላይም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በዚህም ፀጋ ደርቤ ጥቂት ገፍቶ በወሰደው ኳስ ከሳጥን አጠገብ መሬት ለመሬት ያደረገውን ጥሩ ሙከራ ግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው በግሩም ቅልጥፍና ማስወጣት ችሏል።

\"\"

የራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በቁጥር በዝቶ በመገኘት ወደ ፊት የሚወስዱትን ኳስ ጌታነህ ከበደ ላይ በማድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲጥሩ የነበሩት ሠራተኞቹ አጋማሹ ሊጠናቀቅ በተጨመረው የባከነ አንድ ደቂቃ ውስጥ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ሳሙኤል አስፈሪ ከተመስገን በጅሮንድ ጋር ጥሩ ቅብብል በማድረግ ከቀኙ የሜዳ ክፍል ላይ ለማሻማት በሚመስል መልኩ ያሻገረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ ወደ ግብ ሲሄድ ግብ ጠባቂው ዘሪሁን ታደለ መልሶታል። ሆኖም ያንን ኳስ ያገኘው ጌታነህ ከበደ በግንባሩ በመግጨት በቀላሉ አስቆጥሮታል።

ከዕረፍት መልስም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት ኤሌክትሪኮች 53ኛው ደቂቃ ላይም ወደ ጨዋታው ሊመልሳቸው የሚችል ግብ አስቆጥረዋል። 

\"\"

ስንታየሁ ዋለጨ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አብዱልራህማን ሙባረክ ኳሱን በትክክል ሳያገኘው ቀርቶ መሬቱ ላይ ሲነጥር ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው አብነት ደምሴ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎ በውድድር ዓመቱ ሰባተኛ ግቡ አድርጎታል።

በሁለተኛው አጋማሽ ከተጠበቀባቸው መነቃቃት በተቃራኒው ተዳክመው የቀረቡት ወልቂጤዎች በአጋማሹ የተሻለውን የግብ ዕድል 62ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈጥሩ ጌታነህ ከበደ ከቀኙ የሜዳ ክፍል ላይ ሆኖ በግራ እግሩ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ተከላካዩ ዋሀብ አዳምስ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበት የግብ ዕድሉን አባክኖታል።

ጨዋታውን በመቆጣጠር የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች 69ኛው ደቂቃ ላይ የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። አማረ በቀለ ከረጅም ርቀት ያሻገረውን ኳስ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው አብዱልራህማን ሙባረክ የግብ ጠባቂው ጀማል ጣሰው አቋቋም ስህተት ተጨምሮበት በጠበበው የግቡ የግራ ቋሚ በኩል አስቆጥሮታል።

\"\"

ከግቧ መቆጠር በኋላ ውጤቱን ከእጃቸው ለማጣት በመቃረባቸው ቁጭት ውስጥ የገቡት ወልቂጤዎች ጌታነህ ከበደ 85ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት 92ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ፍጹም ግርማ ከግራ መስመር ባሻማው ኳስ ጥሩ ሙከራዎችን አድርጎ በግብ ጠባቂው ተመልሶበታል።

ከጨዋታው በኋላ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ስምኦን ዓባይ ጨዋታውን ጫና ውስጥ ሆነው ማድረጋቸው እና ዕረፍት ላይም እየተመሩ ከመውጣታቸው አንጻር እናጣለን ብለው የሚሰጉት ባለመኖሩ በድፍረት መጫወታቸውን ሲገልጹ በመጀመሪያው አጋማሽ የግራ የተከላካይ መስመራቸው ደካማ እንደነበር በሁለተኛው አጋማሽ ግን የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ አንድ ነጥብ ማሳካታቸውን ተናግረዋል።

\"\"

የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው ተጫዋቾች በተለይም ተከላካዮች ከጨዋታው ይልቅ ነጠብ ስሌት ውስጥ በመግባት ትኩረት ማጣታቸው ውጤት ለማጣታቸው ምክንያት እንደሆነ በተጨማሪም ተጫዋቾች ላይ የድካም ስሜት ይታይ እንደነበር እና የተጫወቱበት መንገድ በርሳቸው ፍላጎት እንዳልነበር ሲገልጹ ከአሰልጣኞቹ በፊት አስተያየት የሰጠው ጌታነህ ከበደ \”ለግብ የሚሆን ኳስ አመቻችቶ የሚሰጠኝ ባለመኖሩ ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱ ወደኋላ ቀርቻለሁ\” ያለውን ሀሳብ እንደማይቀበሉ እና እግርኳስ የቡድን ሥራ ስለሆነ በብዛት ላያገኝ ይችላል እንጂ የለም ማለቱን ግን አልደግፍም ብለዋል። አሰልጣኙ አክለውም በውጤቱ በጣም መከፋታቸውንም ገልጸዋል።