ሪፖርት | ቡናማዎቹ በጎል ተንበሽብሸው ወደ ድል ተመልሰዋል

አምስት ግቦች በተቆጠሩበት ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ድሬዳዋ ከተማን አራት ለአንድ አሸንፏል።

ኢትዮጵየ ቡናዎች ከመጨረሻው ጨዋታ ቋሚ አሰላለፋቸው ጫላ ተሺታን በቃልአብ ፍቅሩ ለውጠው ሲገቡ ብርቱካናማዎቹም ከመጨረሻው ስብስብ ቢንያም ጌታቸው በሙኸዲን ሙሳ ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

ኳስ ለመቆጣጠር ጥረት በምያደርጉ ቡናማዎች እና በፈጣን ሽግግር ዕድሎች ለመፈጠር በሚሞክሩ ድሬዳዋ ከተማዎች መካከል የተደረገው ጨዋታ በሁለቱም አጋማሾች ብርቱ ፉክክር የታየበት ነበር። በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎችም ብርቱካናማዎቹ በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። እነዚህም እንየው ከመስመር ያሻገረው ሙኸዲብ ሳያገኘው የቀረው ሙከራ እና ኤልያስ አሕመድ ከመሀል ጀምሮ በግሩም መንገድ ተጫዋቾች አልፎ በመምታት ያደረገው ሙከራ ብርቱካናማዎቹን መሪ ለማድረግ የተቃረቡበት ሙከራዎች ነበር።


በአጋማሹ በመስፍን እና መሐመድ ኑር ሁለት ጥሩ ዕድሎች የፈጠሩት ቡናማዎቹ በተጋጠሚ ሳጥን ውስጥ በነበረ አለመናበብ ምክንያቱ ወርቃማ ዕድሎቹን ወደ ሙከራነት አልተቀየሩም። አማኑኤል ከመስፍን የተቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ በረዥሙ ያደረገው ሙከራ እና አማኑኤል ለብሩክ አሾልኮለት አጥቂው መቶ የግቡን አግዳሚ የመለሰለት ኳስ በአጋማሹ በቡናማዎቹ የተፈጠሩ የግብ ዕድሎች ነበሩ።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያው ደቂቃ መሐመድኑር ከመስመር የተሻገረው ኳስ ተጠቅሞ ድንቅ ሙከራ ካደረገ ከደቂቃዎች በኋላ ኢትዮጵያ ቡናዎች በመስፍን ታፈሰ ድንቅ የረዥም ርቀት ግብ መሪ መሆን ችለዋል። አጥቂው በድሬዳዋ ከተማ ተከላካይ የቅብብል ስህተት ያገኘው ኳስ በግራ እግሩ አክርሮ በመምታት ነበር ያስቆጠረው። ቡናማዎቹ ከግቧ በኋላም በብሩክ የግንባር ሙከራ እና በሮቤል አማካኝነት መሪነታቸው ለማስፋት ተቃርበው ነበር።


በስልሳ ሥስተኛው ደቂቃም በብርቱካናማዎቹ ሳጥን በተሰራው ጥፋት የተገኘው ፍፁም ቅጣት ምት ሮቤል ተክለሚካኤል ወደ ግብነት ቀይሮ ቡናማዎቹ መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል። የተጋጣሚን አማካይ ክፍል በልጠው በርካታ ዕድሎች ለመፍጠር ያልተቸገሩት ቡናዎች የተጫዋች ቅያሬ ካደረጉ በኋላ ሥስተኛው ግብ አስቆጥረው የግብ ልዩነቱን አስፍተዋል። በጨዋታው ድንቅ የነበረው አማኑኤል ለመሐመድ ኑር አቀብሎት አጥቂው ወደ ሳጥኑ ያሻማው ኳስ አንተነህ ተፈራ ወደ ግብነት ቀይሮታል።


በሁለተኛው አጋማሽ በሁሉም ረገድ ወርደው የታዩት ብርቱካናማዎቹ በአጋማሹ በጋዲሳ እና ሙኸዲን አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ችለዋል። በተለይም አቤል ከመስመር አሻግሮት ሙኸዲን ሳያገኘው ለጥቂት የወጣው ኳስ በድሬዳዋ በኩል አስቆጪ ነበር። በሰባ ዘጠነኛው ደቂቃ ግን ጥረታቸው ሰምሮ በያሲን ጀማል አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል ፤ የመስመር ተከላካዩ አቤል ከመስመር አሻምቶት ተከላካዮች የጨረፉት ኳስ አግኝቶ በመምታት ነበር ግቧን ያስቆጠረው። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩትም ቡናዎች በመስፍስ ታፈሰ በመልሶ ማጥቃት የሄደውን ኳስ ለአማኑኤል አቀብሎት አምበሉ ወደ ግብነቱ ቀይሮ የቡናማዎች መሪነት ወደ አራት ከፍ አድርጓል።


ከጨዋታው በኋላ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ \”እንደዚ አይነት ቀኖች እንደሚመጡ እናውቅ\” ነበር ካሉ በኋላ \”በጨዋታው ያሰብነው ነገር አሳክተናል\” ብለዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም አቻ መብዛቱ ውጥረት እንደፈጠረባቸው ገልፀው ይህ ውጤት እንደማያዘናጋቸው አውስተዋል። የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ አስራት አባተ በበኩላቸው \”በመጀመርያው አጋማሽ ለጨዋታው የሰጠነው ትኩራት ትልቅ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ ግን የወሰናቸው ውሳኔዎች ጥሩ አልነበሩም ፤ ቸኩለናል ካሉ በኋላ \”የሜዳው ሁኔታ ፣ የአየር ሁኔታው እና ተጋጣምያችን ለመቆጣጠር ጥረታችን ጥሩ አልነበረም\” ብለዋል።

\"\"