ሪፖርት | ተጠባቂው ጨዋታ በብርቱ ፉክክር ታጅቦ አቻ ተጠናቋል

ለተመልካች ማራኪ የሆነ ፉክክር የተደረገበት የ21ኛ ሳምንት ተጠባቂው የባህር ዳር ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል።

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር በባህር ዳር ከተማ እና በኢትዮጵያ መድን መካከል ሲደረግ ባህር ዳር ከተማ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ለገጣፎ ለገዳዲን 3ለ1 ከረታበት የመጀመሪያ ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ሲገባ በተመሳሳይ ሳምንት በመቻል አንድ ለምንም የተረታው ኢትዮጵያ መድን በበኩሉ ተካልኝ ደጀኔን በኪቲካ ጅማ ብቻ ተክቶ ጨዋታውን ቀርቧል።

\"\"

በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ለተመልካች ሳቢ የሆነ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በተሻለ የጨዋታ ስሜት አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ባህር ዳር ከተማዎች 5ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ፉዐድ ፈረጃ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ በግንባሩ በመግጨት መረቡ ላይ አሳርፎታል። ግብ ካስቆጠሩ በኋላም በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝተው መድረስ የቻሉት የጣና ሞገዶቹ ተጨማሪ ንጹህ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለው ነበር። በተለይም 10ኛው ደቂቃ ላይ የአብሥራ ተስፋዬ ከራሱ የግብ ክልል ውስጥ ሆኖ በግሩም ዕይታ በረጅሙ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ ኳሱን እየገፋ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል በመግባት ያደረገው ሙከራ በግራው ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል።


የጣና ሞገዶቹን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት የተቸገሩት እና ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ክፍት ቦታዎችን በመፈለግ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ ሲጥሩ የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች 23ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው አቻ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ባሲሩ ኦማር ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሳይመን ፒተር በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮታል።

ባህርዳሮች ግብ ባስተናገዱበት ቅጽበት ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ሲፈጥሩ ፍጹም ጥላሁን ወደ ሳጥን ይዞት የገባውና በተከላካይ ሲመለስበት በድጋሚ ተደርቦ የመለሰውን ኳስ ያገኘው ዱሬሳ ሹቢሳ ኳሱን በኃይል ወደ ውጪ በመምታት ትልቁን የግብ ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሆኖም በፍጹም ጥላሁን እና በፉዐድ ፈረጃ የቅጣት ምቶች ተጨማሪ የግብ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ 39ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ዱሬሳ ሹቢሳ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ሆኖ ያገኘው መሳይ አገኘሁ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ሲመለስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ ተገልብጦ ለማስቆጠር ያደረገውን ሙከራም ግብ ጠባቂው አቡበከር በድጋሚ በግሩም ቅልጥፍና አግዶበታል።


ከዕረፍት መልስ ከነበራቸው የማጥቃት እንቅስቃሴያ ተዳክመው የቀረቡት ባህርዳሮች 47ኛው ደቂቃ ላይ አለልኝ አዘነ ከሳጥን ውጪ መትቶት ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ ከመለሰው ኳስ የተሻለ ሙከራ ለማድረግ ብዙ ደቂቃዎችን መታገስ ግድ ሲላቸው በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽለው የቀረቡት ኢትዮጵያ መድኖች 51ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በግሩም የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ኪቲኪ ጅማ ያቀበለውን ኳስ በግራው የሜዳ ክፍል ላይ ሆኖ የተቀበለው ሳይመን ፒተር መሬት ለመሬት ወደ ውስጥ ሲያሻግረው ያገኘው ሀቢብ ከማል ኳሱ የግብ ጠባቂውን ታፔ አልዛየር እጅ በመጣስ መረቡ ላይ እንዲያርፍ አድርጎታል።

የግብ ብልጫ ከተወሰደባቸው በኋላ የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት የጣና ሞገዶቹ ባልተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል። ሆኖም 59ኛው ደቂቃ ላይ ፍራኦል መንግሥቱ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻማው ኳስ በያሬድ ባዬህ ግንባር እና ሀብታሙ ታደሠ እግር ተጨርፎ ቢቆጠርም ከጨዋታ ውጪ ሆኖ ተሽሯል። በስድስት ደቂቃዎች ልዩነትም ተቀይሮ የገባው አደም አባስ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ታደሠ ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ሆኖ ያደረገው ሙከራ በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።


ጨዋታውን መምራት ከጀመሩ በኋላ በመጠኑ የተቀዛቀዙት መድኖች 82ኛው ደቂቃ ላይም መሪነታቸውን ሊያጠናክሩበት የሚችሉበትን ትልቅ የግብ ዕድል ፈጥረው ነበር። ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ የነበረ የሚመስለው ሳይመን ፒተር አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ ግብ ጠባቂውን ማለፍ የቻለው ኪቲኪ ጅማ እጅግ በወረደ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ከአንድ ደቂቃ በኋላም ባህር ዳር ከተማዎች አቻ ሆነዋል። ፍራኦል መንግሥቱ በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ የመድኑ ተከላካይ ሀቢብ መሐመድ በግንባሩ በመግጨት በትክክል ሳያርቀው ቀርቶ ኳሱን ያገኘው አደም አባስ አስቆጥሮታል። ሆኖም ጨዋታው በቀሪ ደቂቃዎችም ጥሩ ፉክክር ተደርጎበት 2-2 ተጠናቋል

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ውጤቱን እንዳላስደሰታቸው ነገር ግን እንደላስከፋቸውም ሲናገሩ መሃል ሜዳው ላይ  በመጀመሪያው አጋማሽ ባህርዳሯች ብልጫ ቢወስዱም በሁለተኛው አጋማሽ የተሻሉ እንደነበሩ ሲገልጹ ውጤቱ በቂ እንዳልሆነ እና ያገኙትን ዕድል አለመጠቀማቸውንም እንደ ምክንያት ጠቅሰዋል። የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግ አረገ ይግዛው በበኩላቸው ሦስት ነጥብ ይገባቸው እንደነበር አበክረው በመግለጽ ተጫዋቾች የቻሉትን ሁሉ እንደሞከሩና በመጀመሪያው አጋማሽ በጉጉት የተነሳ የግብ ዕድሎችን አለመጠቀማቸው ድል ላለማሳካታቸው እንደ ምክንያት ሲናገሩ መድን ትልቅ ቡድን ከመሆኑ አንጻር ከመመራት በመነሳት አቻ መውጣታችው ጥሩ እንደሆነ እና ስለ ዋንጫ ለማሰብ ጊዜው ገና ስለመሆኑም ተናግረዋል። አሰልጣኙ አክለውም ውጤት ቀያሪ የዳኝነት ስህተቶች በተለይም ለዋንጫ ግስጋሴ በሚያደርጉ ቡድኖች ላይ ስሜት እንደሚጎዱ እና ተጨዋቾቹ በየ ጨዋታው የሚሰጡት ትኩረት ሲያደንቁ የቡድኑን ተጓዥ ደጋፊዎች በማመስገን ሲመለሱ መልካም ነገር እንዲገጥማቸው ተመኝተዋል።