በ21ኛው የሊጉ የጨዋታ ሳምንት ላይ ጎልተው የወጡ ተጨዋቾች እና አሰልጣኝን የመረጥንበት የሳምንቱ ምርጥ ቡድን ይህንን ይመስላል።
አሰላለፍ 3-5-2
ግብ ጠባቂ
ሚኬል ሳማኬ – ፋሲል ከነማ
ፋሲሎች ሀዋሳን በረቱበት ጨዋታ ላይ ቡድኑ ሦስት ነጥብ ለማግኘቱ ይህ ማሊያዊ ግብ ጠባቂ ያለው ድርሻ ከፍ ያለ ነው። በሁለት አጋጣሚዎች በአንድ ለአንድ ግንኙነት ሙጂብ ቃሲም ያደረጋቸውን ግልፅ የማግባት ዕድሎችን ባመከነበት አስደናቂ ብቃቱ በሳምንቱ የምርጥ ስብስብ አካል ሊሆን ችሏል።
ተከላካዮች
ፈቱዲን ጀማል – ባህር ዳር ከተማ
ምንም እንኳን ባህር ዳር ከተማ ከመድን ጋር ያደረገውን ወሳኙን ጨዋታ ነጥብ ተጋርቶ ቢወጣም የመከላከል አደረጃጀቱን በጥሩ ሁኔታ በመምራት እና የቡድኑን ጥቃት የሚያስጀምሩ ኳሶችን ወደ ፊት በማድረስ የፈቱዲን ጀማል ብቃት ወሳኝ መሆኑን አስመልክቶናል።
አስቻለው ታመነ – ፋሲል ከነማ
በጉዳት ምክንያት የቀደመ ብቃቱን ለማግኘት እየተቸገረ የሚገኘው አስቻለው ታመነ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ወደ ብቃቱ እየተመለሰ መሆኑን እያሳየ ይገኛል። በተለይም በሀዋሳው ጨዋታ ላይ የቡድኑን የኋላ መስመር በመምራት ያሳየው ብቃት በስብስባችን እንዲካተት ምክንያት ሆኗል።
እዮብ ማቲያስ – አዳማ ከተማ
አዳማ ከተማ ከሰሞኑ በሜዳው ተከታታይ ድሎችን እያስመዘገበ ሲመጣ በወጥነት የኋላ መስመሩ ላይ ጫናዎች እንዳይበዙ በመታተር ሲከላከል ይስተዋላል። እዮብ ቡድኑ በሲዳማ ላይ ድልን ሲጎናፀፍ የተቃራኒ ቡድንን የጥቃት ሒደት በማምከን በምቹነት ሲከላከል የተመለከትነው በመሆኑ የምርጥ ቡድናችን አካል ሆኗል።
አማካዮች
በረከት ወልዴ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
የተከላካይ አማካዩ በረከት ቡድኑ በፈታኙ የአርባምንጭ ጨዋታ ድል ሲያደርግ አካላዊ ፍትጊያ ያየለበትን የመሐል ሜዳውን ፍልሚያ ለመቆጣጠር ሲሞክር ተስተውሏል። በተለይ ደግሞ በሁለተኛው አጋማሽ ቅዱስ ጊዮርጊ በተሻለ ደህንነት ማጥቃቱ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የበኩሉን ሲወጣ ነበር።
አማኑኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ቡና
ቡናማዎቹ አራት ግቦችን አስቆጥረው ባሸነፉበት ጨዋታ ምርጥ እንቅስቃሴ ካሳዩት ተጫዋቾች አንዱ አምበሉ አማኑኤል ዮሐንስ ነው። አሰልጣኙ የተሻለ የማጥቃት ነፃነት ከሰጡት በኋላ ጥሩ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኘው ይህ አማካይ በዚህ ሳምንት አንድ ግብ አስቆጥሮ አንተነህ ተፈራ ባስቆጠራት ግብም ጉልህ አስተዋፅኦ አድርጓል።
አማኑኤል ጎበና – አዳማ ከተማ
ከሁለት ጨዋታዎች በኋላ ወደ መጀመሪያ አሰላለፍ የተመለሰው አማካይ ጥሩ የጨዋታ ቀንን አሳልፏል። አዳማዎች በሲዳማ የአማካይ ክፍል ላይ ለወሰዱት ብልጫ በታታሪነት ከሳጥን ሳጥን ባደረገው እንቅስቃሴ የበኩሉን ሲያደርግ ራሱ ባስጀመረው ጥቃት ከቡድን አጋሮቹ ጋር በማራኪ ሁኔታ የተቀባበለውን ኳስም ከመረብ ማገናኘት ችሏል።
ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ
በሳምንቱ በተደረጉ ጨዋታዎች ላይ ጎልቶ የወጣ የመስመር ተከላካይ ባለመኖሩ የአሰላለፍ ለውጥ ስናደርግ እንደማጥቃቱ ሁሉ በመከላከሉ ረገድም ጥሩ ተሳትፎ የሚያደርገው ዮሴፍን በተመላላሽነት ተጠቅመነዋል። ማንፀባረቁን የቀጠለው ወጣቱ አዳማ ሲዳማ ቡናን ሲረታ ለቀዳሚው ጎል መገኘት ምክንያት መሆን ሲችል ሦስተኛውን ግብ ደግሞ ከቅጣት ምት ማስቆጠር ችሏል።
ሱራፌል ዐወል – ለገጣፎ ለገዳዲ
ድሎች እየራቁት የመጣው ለገጣፎ ለገዳዲ ከሦስት ነጥብ ጋር ለመታረቅ ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ብርቱ ትግል ባደረገበት እና ያለ ጎል በፈፀመው ጨዋታው በአማካይ ስፍራው ላይ አልፎ አልፎም ወደ መስመር ጭምር በመውጣት የጎል ዕድሎችን ሲፈጥር የተመለከትነው ሱራፌል በጨዋታው ከነበረው ተሳትፎ አንፃር በቀኝ መስመር ተመላላሽነት መርጠነዋል።
አጥቂዎች
መስፍን ታፈሰ – ኢትዮጵያ ቡና
ቡናማዎቹ ድሬዳዋ ከተማን ባሸነፉበት ጨዋታ በማጥቃት ሽግግር ወቅት ጉልህ ሚና ሲጫወት የተስተዋለው ይህ አጥቂ ለቡድኑ ዐይን ገላጭ የሆነች የመጀመርያው ግብ አስቆጥሮ አማኑኤል ላስቆጠራት አራተኛ ግብም አመቻችቶ አቀብሏል። ያደረገው ጉልህ አስተዋፅዖም በሳምንቱ ምርጥ ቡድን እንዲካተት አስችሎታል።
ሳይመን ፒተር – ኢትዮጵያ መድን
ዩጋንዳዊው አጥቂ ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ያሳየው ብቃት እጅግ መልካም ነበር። ተጫዋቹ ቡድኑን አቻ ያደረገች የጭንቅላት ግብ ከማስቆጠሩ በተጨማሪ ከመመራት ወደ መምራት ወስዳ የነበረውን የሀባቢ ጎልም አመቻችቶ አቀብሏል። ከጎሎቹ ውጪም በእንቅስቃሴ ረገድ ያሳየው ነገር በምርጥ ቡድናችን እንዲገኝ አድርጎታል።
አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ – አዳማ ከተማ
ከታችኛው የደረጃ ሰንጠረዥ ስጋት ወደ አስተማማኝ ቦታ ቡድናቸውን እየወሰዱ የሚገኙት አሠልጣኝ ይታገሱ በጨዋታ ሳምንቱ በወራጅ ቀጠናው የሚገኘውን ሲዳማ ቡናን የረቱበት መንገድ እና ጨዋታውን የተቆጣጠሩበት ሂደት የምርጥ ቡድናችን አሠልጣኝ አድርጓቸዋል። ከኳስ ጋር ጊዜ የሚያሳልፍ ቡድን እየሰሩ የሚገኙት አሠልጣኙም በጨዋታው የተጋጣሚን ጠንካራ ጎኖች አክሽፈው በሦስት ግቦች ታጅበው ዘጠነኛ ድላቸውን አሳክተዋል።
ተጠባባቂዎች
ቻርለስ ሉኩዋጎ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
አብነት ደምሴ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ
ዱላ ሙላቱ – ፋሲል ከነማ
ባሲሩ ዑመር – ኢትዮጵያ መድን
ዘላለም አባቴ – ወላይታ ድቻ
መሐመድኑር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና
እስማኤል ኦሮ አጎሮ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ጌታነህ ከበደ – ወልቂጤ ከተማ