ነገ በሚጀመረው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22ኛ ሣምንት የሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እነሆ!
ወላይታ ድቻ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ
በሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር 27 ነጥቦችን በመያዝ 9ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠውን ወላይታ ድቻን 11 ነጥቦች በመያዝ በደረጃው ግርጌ ላይ ከተቀመጠው ለገጣፎ ለገዳዲ ሲያገናኝ ድቻዎች ናፍቀው ያገኙትን ድል በተከታታይ ለማስመዝገብ ጣፎዎች በሊጉ ለመቆየት አስፈላጊያቸው የሆነ ውጤት ለማግኘት ጥሩ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይገመታል።
ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት መቻልን 1-0 በመርታት ወደ ድል የተመለሱት ወላይታ ድቻዎች በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ ያደረጉት የአጨዋወት ቅርፅ ለውጥ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን ያስደነቀ ነበር። በተለይም ቡድኑ ከአራት ጨዋታዎች በኋላ ግቡን አለማስደፈሩ ሌላኛው ጥንካሬው ሲሆን በነገው ዕለትም በሊጉ ግርጌ ላይ ተቀምጠው የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ከገቡት ለገጣፎዎች ጋር ብርቱ ፍልሚያ አድርገው ለመጨረሻ ጊዜ በዘጠነኛው እና በአሥረኛው የጨዋታ ሳምንት ያሳኩትን ተከታታይ ድል በድጋሚ ለማስመዝገብ ጥረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከወራጅ ቀጠናው አንድ ደረጃ ከፍ ብሎ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ በ 11 ነጥቦች ዝቅ ብለው መጨረሻ ላይ የተቀመጡት ለገጣፎዎች ካለፉት ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ግብ አለማስተናገዳቸው ጥሩ ጎናቸው ቢሆንም አሁንም ባላቸው ጭላንጭል የመትረፍ ተስፋ ብርቱ ትግል አድርገው የውድድሩ ዝቅተኛ የግብ መጠን (14) ያስመዘገበው የአጥቂ ክፍላቸውን በማጠናከር ድሎችን ማስመዝገብ ግድ ይላቸዋል። በእንቅስቃሴ ደረጃ እየተሻሻለ የመጣው ቡድኑ በነገው ዕለትም ከድል ከተመለሰው ወላይታ ድቻ ጋር ፈታኝ ፍልሚያ ይጠብቀዋል።
በለገጣፎ በኩል የሱለይማን ትራኦሬ እና መሐመድ አበራ መሰለፍ ሲያጠራጥር ኮፊ ሜንሳህ በቅጣት የነገው ጨዋታ ያልፈዋል።
ሁለቱ ቡድኖች ድሬዳዋ ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ግንኙነታቸው ወላይታ ድቻ 4-3 መርታቱ ይታወሳል።
ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት አዳነ ወርቁ ሲመራው አሸብር ታፈሰ እና ታምሩ አደም ረዳቶች ሀብታሙ መንግስቴ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነዋል።
ፋሲል ከነማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
በምሽቱ መርሐግብር በ 30 ነጥቦች 8ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ፋሲል ከነማዎች በ 31 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ከተቀመጡት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጋር ሲያገናኝ ዐጼዎቹ ከናፈቃቸው ተከታታይ ድል ጋር ለመታረቅ ነብሮቹ ደግሞ ባለፈው ሳምንት ያላሳኩትን ድል ለማሳካት ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።
አዳማ ላይ ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች በሦስቱ ድል አድርገው በሁለቱ የተሸነፉት ፋሲል ከነማዎች ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ራሱ ላይ ባስቆጠረው ግብ ሀዋሳ ከተማን 1-0 ሲረቱ ያደረጉት ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና የፈጠሯቸው በርካታ የግብ ዕድሎች ቡድኑ ሜዳሊያ ደረጃ ውስጥ ለመግባት ለሚያደርገው ግስጋሴ ትልቅ ተስፋን የሚሰጥ ነበር። ሆኖም በ7ኛው እና በ 8ኛው የጨዋታ ሳምንት ብቻ ተከታታይ ድል ያስመዘገበው ቡድኑ እንደ እነዚህ ሳምንታት ሁሉ ተከታታይ ድል ለመቀዳጀት በነገው ዕለት በጥሩ ወቅታዊ ብቃት ላይ ከሚገኘው ሀዲያ ሆሳዕና የሚገጥመው ፈተና አይሆንም። አዲሱ ፈራሚያቸው ዱላ ሙላቱ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ያደረገው መልካም እንቅስቃሴ በነገው ዕለትም ቀዳሚ ተሰላፊነት ቦታን አግኝቶ ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋች ሊሆን ይችላል።
እንደ ተጋጣሚያቸው ሁሉ በአዳማ ቆይታቸው ሦስት ድሎችን ያሳኩት ሆሳዕናዎች በአንዱ ሲሸነፉ ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ከለገጣፎ ለገዳዲ ጋር ነጥብ ተጋርተዋል። ቡድኑ ከእነዚህ አምስት ጨዋታዎች በአንዱ ብቻ ግብ ሲቆጠርበት በአንጻሩ ደግሞ በአራቱ ጨዋታዎች ግብ ማስቆጠር ችሏል። በሜዳሊያ ደረጃው መጨረሻ ላይ ከሚገኘው ኢትዮጵያ መድን በሰባት ነጥቦች ዝቅ ብሎ የሚገኘው ሆሳዕና ይህንን ደረጃ ለመረከብ ተከታታይ ድሎች ያስፈልጉታል። አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ዓላማችን ከደረጃው ወገብ በላይ መጨረስ ነው ብለው በአንድ ወቅት የተናገሩት አስተያየት የሚሰምርላቸው ቢመስልም ባላቸው ወቅታዊ ጠንካራ እንቅስቃሴ ከዚህም በላይ መጠበቃቸው የሚቀር አይመስልም። በነገው ዕለትም ከፋሲል ከነማ ሙሉ ሦስት ነጥብ ለመውሰድ ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል።
በፋሲል ከነማ በኩል ዓለምብርሀን ይግዛው ከቅጣት ሲመለስ ፍቃዱ ዓለሙም ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ማገገሙ ተሰምቷል። በሀዲያ በኩል ቃልአብ ውብሸት እና ቤዛ መድህን በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ናቸው።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለአምስት ጊዜያት ሲገናኙ ፋሲል ከነማ ሁለቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ይወስዳል። ቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ የተጠናቀቁ ነበሩ። ዐጼዎቹ ስድስት ነብሮቹ ደግሞ ሦስት ግቦችን ማስቆጠርም ችለዋል።
የምሽቱን መርሐግብር ለመምራት ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በዋና ዳኝነት ፣ ዳንኤል ጥበቡ እና መሐመድ ሁሴን በረዳትነት እንዲሁም ተካልኝ ለማ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።