የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ | ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቻምፒዮን ሆኗል

ዛሬ በተደረጉ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አንድ ጨዋታ እየቀረው የዋንጫው አሸናፊ መሆኑን ያረጋገጠበትን ድል ሲያሳካ መቻልም ሌላኛው የዕለቱ ባለ ድል ሆኗል።

ልደታ ክ/ከተማ 0-0 ድሬዳዋ ከተማ

ጠዋት 4 ሰዓት ላይ በሳምንቱ ቀዳሚ መርሐግብር ልደታ ከ ድሬዳዋ ሲገናኙ መጠነኛ ፉክክር በተደረገበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ቢታይበትም የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። በልደታዎች በኩል 22ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት በተነሳ ኳስ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው በግቡ አግዳሚ ሲመለስባቸው በድሬዎች በኩል 35ኛው ደቂቃ ላይ ታደለች አብርሃም ከሳጥን ውጪ ሞክራው በግብ ጠባቂዋ ስመኝሽ ፍቃዱ እና በግቡ የግራ ቋሚ ተመልሶባታል።
\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል 60ኛው ደቂቃ ላይ የልደታዋ አለሚቱ ድሪባ ከቅጣት ምት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠበቂዋ ሣራ ብርሃኑ ስታስወጣባት በሴኮንዶች ልዩነት የድሬዳዋ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ የነበረችው ሥራ ይርዳው በቀኝ መስመር በግሩም ሁኔታ ገፍታ በወሰደችው ኳስ ያደረገችው ሙከራ በግራው ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል። ሆኖም 69ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው የልደታዋ አሰገደች ሸጎ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ሆና ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ሣራ ብርሃኑ መልሳባታለች። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4-0 ይርጋጨፌ ቡና

8 ሰዓት ላይ በጀመረው ጨዋታ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲደረግበት የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ንግድ ባንኮች የተሻሉ ነበሩ። ሆኖም በባንኮች በኩል 12ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገችው እና የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰባት ሙከራ በይርጋጨፌዎች በኩል ደግሞ 27ኛው ደቂቃ ላይ ፍሬሕይወት ተስፋዬ ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ አድርጋ የግቡ አግዳሚ ሲመልስባት ኳሱን ሳትዘጋጅ ያገኘችው ዳግማዊት ሰለሞን በደረቷ ገፍታ ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ በቀላሉ ይዛዋለች። 30ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ሙከራ አድርጋ በግብ ጠባቂዋ ምህረት ተሰማ የተመሰባት መሳይ ተመስገን 41ኛው ደቂቃ ላይ ግን የይርጋጨፌ ተከላካዮች ከጨዋታ ውጪ ናት ብለው በተዘናጉበት ቅፅበት በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ኳሱን ይዛ በመግባት አስቆጥራው ክለቧን አጋማሹን መርቶ እንዲወጣ አስችላለች።
\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች ግን ተጨማሪ ሦስት ግብ ባስቆጠሩት ንግድ ባንኮች በኩል ማራኪ እንቅስቃሴ ተደርጎበታል። ሎዛ አበራ 81ኛው ፣ 89ኛው እና 90ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ግቦች አስቆጥራ ሐትሪክ መሥራት ስትችል ጨዋታውም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ንግድ ባንክ አንድ ጨዋታ እየቀረ የውድድሩ አሸናፊ መሆኑን አረጋግጧል።

ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ 0-4 መቻል

10፡00 ላይ የዕለቱ የመጨረሻ መርሐግብር በንፋስ ስልክ እና መቻል መካከል ሲደረግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ ሙሉ ብልጫውን የወሰዱት መቻሎች 13ኛው ደቂቃ ላይ ምርቃት ፈለቀ በግራ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ባስቆጠረችው ግብ ጨዋታውን መምራት ሲጀምሩ በሁለት ደቂቃዎች ልዩነትም እፀገነት ግርማ ከቀኝ መስመር ያደረገችው ሙከራ የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው ቢያሳልፉም የመቻልን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመግታት የተቸገሩት ንፋስ ስልኮች 25ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ግቡንም በሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ የነበረችው ምስር ኢብራሂም ከመረቡ ላይ አሳርፋዋለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ይበልጥ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል መቻሎች 47ኛው ደቂቃ ላይ እፀገነት ግርማ እና 60ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ቤዛዊት ተስፋዬ ባስቆጠሩት ግብ ጨዋታውን በአራት ግብ ልዩነት መምራት ጀምረዋል። ከዚህ ግብ በኋላም ጨዋታው እጅግ ተቀዛቅዞ በመቻል 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።