ሪፖርት | ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ በመጨረሻ ደቂቃ ጎሉ አፄዎቹን ታድጓል

ፋሲል ከነማዎች በጭማሪ ደቂቃ ባስቆጠሯት ግብ ታግዘው ሀድያ ሆሳዕናን 2ለ1 በመርታት የአዳማ ቆይታቸውን በድል ፈፅመዋል።

ፋሲል ከነማ ድል አድርጎ የመጣው ስብስቡ ላይ ምንም ቅያሪ ያላደረገ ሲሆን ሀድያ ሆሳዕና ከለገጣፎው የአቻ ውጤት አንፃር ባደረገው ለውጥ ራምኬል ሎክ እና ፀጋዬ ብርሀኑን ፣ በዳግም ንጉሴ እና ተመስገን ብርሀኑ ተክተዋል።

\"\"

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ፋሲሎች የአማካይ ክፍላቸውን ተጠቅመው ወደ ኦሴ ማውሊ በሚጣሉ ተሻጋሪ ኳሶች ላይ ያነጣጠረ እንቅስቃሴን ተግባራዊ ለማድረግ የጣሩበትን ሒደት ብናይም ጋናዊው አጥቂ በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ እየተገኘ ኳስን ይቀበል ስለነበር ቡድኑ አጋጣሚን ከመፍጠር አንፃር ቁጥብ ሆኖ ሊቆይ ተገዷል። በአንፃሩ በሽግግር በጥልቀት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቀላሉ በመድረስ ሙከራዎችን ያደርጉ የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ከተጋጣሚያቸው በተሻለ ፈጥረዋል። 7ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን ብርሀኑ የግል አቅሙን ተጠቅሞ ሳጥን ውስጥ በግራ እግሩ ባደረጋት ሙከራ ጥቃትን ቡድኑ መሰንዘርን ጀምሯል። ወጥ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን ጨዋታው ቢያስመለክተንም ሀድያ ሆሳዕናዎች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በተሻለ የተጠቀሙበት ነበር።

\"\"

20ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከሳጥኑ ጠርዝ አክርሮ ወደ ጎል መቶ ግብ ጠባቂው ሳማኪ ሚካኤል እና የግቡ ቋሚ ብረት ተጋግዘው የወጣችው ኳስ የጨዋታው ጥራት ያላት ሙከራ ነበረች። 32ኛ ደቂቃ ላይ ጨዋታው እንደደረሰ ግን ለመቋረጥ ተገዷል። በመብራት መጥፋት ምክንያት ጨዋታው አስር ያህል ደቂቃዎችን ተቋርጦ ከቆየ በኋላ መብራት ዳግም መምጣቱን ተከትሎ ሲጀምር ፋሲሎች ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ሙከራን ያደረጉበት ሆኗል። 35ኛው ደቂቃ ታፈሰ ሰለሞን ወደ ቀኝ ያደረሰለትን ኳስ ዱላ ከቀኝ ወደ ውስጥ አሻግሮ ኦሴ ማውሊ በግንባር ገጭቶ ፔፕ ሰይዶ በጥሩ ቅልጥፍና ያወጣበት አስቆጪዋ የቡድኑ ሙከራ ነች። በአጋማሹ በተሻለ ከጎል ጋር የመገናኘት ዕድልን በድግግሞሽ የፈጠሩት ሀድያዎች ግርማ በቀለ ከርቀት ሞክሮ ሳማኪ ካወጣበት ሙከራ በኋላ ጎል አግኝተዋል። 45ኛው ደቂቃ ላይ ሳማኪ ሚካኤል ባዬ ገዛኸኝ ላይ በሳጥን ውስጥ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘችውን የፍፁም ቅጣት ምት ባዬ ራሱ ላይ ከመረብ አሳርፏት አጋማሹ ወደ መልበሻ ክፍል በ1ለ0 ውጤት አምርቷል።

\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ፋሲሎች ወደ ጨዋታ ቅኝት በቶሎ ለመመለስ ቅፅበታዊ ሙከራን አድርገዋል። ከዓለምብርሀን ይግዛው ከቀኝ የሀድያ የሜዳ ክፍል ናትናኤል ያገኛትን ኳስ በግንባር ገጭቶ ፔፕ ሰይዶ በሚገርም ብቃት አውጥቶበታል። ፈጣን ሙከራን ካስተናገዱ በኋላ ሀድያዎች ሁለቱን መስመሮች በተሻጋሪ ኳሶች ተጠቅመው ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ጥረት ያደረጉበትን እንቅስቃሴን ታዝበናል። ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን ከርቀት አክርሮ መቶ ሳማኪ ካወጣት መከራ መልስ ፋሲሎች ሱራፌል እና ሽመክትን ወደ ሜዳ ቀይረው በማስገባት በአንድ ሁለት ቅብብሎች ወደ መስመር ለጥጠው በመንቀሳቀስ ቀዳዳዎችን ለመፍጠር በብርቱ ሀድያን ፈትነዋል።

\"\"

60ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከቅጣት ምት ወደ ጎል አክርሮ መቶ ፔፕ ሰይዶ በመለሰበት ሙከራ ማድረጋቸውን ቀጥለው ሀድያዎች የመጨረሻውን ሀያ ደቂቃዎች በጥብቅ መከላከል ላይ ተጠምደው ማሳለፋቸው በፋሲሎች በተደረገባቸው ጫና ያለው እንቅስቃሴ ጎል ተቆጥሮባቸዋል። 

\"\"

74ኛው ደቂቃ ሽመክት ጉግሳ በጥሩ ዕይታ ያሾለከለትን ኳስ ከተከላካዮች አምልጦ በመውጣት የፔፕ ሰይዶን ከግብ ክልሉ ለቆ መውጣቱን ተመልክቶ ኦሴ ማውሊ ፋሲልን ወደ አቻነት የመለሰች ጎል ከመረብ አዋህዷል። ከፉክክር ይልቅ የዕርስ በዕርስ ሽኩቻዎች እየጎሉ የመጡበት ጨዋታው መደበኛው ደቂቃ ተሰጥቶ በተጨማሪ ደቂቃ 90+3 ላይ ፋሲሎች ከቅጣት ምት ሱራፌል አሻምቶ ሽመክት በግንባር ገጭቶ ፔፕ ሲመልሳት ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ አግኝቷት ወደ ጎልነት ቀይሯታል።

\"\"

የግቧ መቆጠርን ተከትሎ ሀድያዎች በፈጠሩት ተቃውሞ ባዬ ገዛኸኝ ከዕለቱ ዳኛ ለሚ ንጉሴ ጋር በፈጠረው ውዝግብ በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል። ጨዋታውም ፋሲልን 2ለ1 አሸናፊ በማድረግ ተጠናቋል።