መረጃዎች | 89ኛ የጨዋታ ቀን

ነገ የሚከናወኑትን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

ባህር ዳር ከተማ ከ አርባምንጭ ከተማ

በሰንጠረዡ ሁለት ጫፎች ላይ ባሉት ፉክክሮች ውስጥ ተሳታፊ የሆኑት ባህር ዳር ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ  በየፊናቸው አስፈላጊ የሆኑ ሦስት ነጥቦችን ፍለጋ 09:00 ላይ ይፋለማሉ።

\"\"

ባህር ዳር ከተማ እጅግ ወሳኝ በነበረው የኢትዮጵያ መድን ጨዋታ ነጥብ ተጋርቶ ለነገው ጨዋታ ይደርሳል። አሁን ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ያለው ልዩነት አምስት የደረሰ በመሆኑም ከዚህ በላይ እንዳይሰፋ አዞዎቹን መርታት ይጠበቅበታል። ቡድኑ አምስት ተከታታይ ድሎችን አሳክቶ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ወጥ የሆነ ተሳትፎ ሲያደርግ ቆይቷል። ከመድኑ አቻ በኋላ በፍጥነት ወደ ቀደመው መንፈስ ለመመለስም ነገ ከፍ ባለ የማጥቃት ተነሳሽነት ጨዋታውን እንደሚጀምር ይጠበቃል። በእርግጥ ከተጋጣሚው ጠንከር ያለ የመከላከል ምላሽ ሊጠብቀው እንደሚችል ሲገመት ቡድኑ ከወገብ በላይ ያሉት የተጨዋቾች ጥራት ጥሩ አማራጮች እንደሚሰጡት ይገመታል። ይልቁኑም በመጨረሻዎቹ አራት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣት አለመቻሉ በደካማ ጎንነት ይነሳበታል።

የውድድር ዓመቱ ቀላል ያልሆነላቸው አርባምንጭ ከተማዎች ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ እና በአንድ ደረጃ ብቻ ከፍ ብለው ተቀምጠዋል። በመጨረሻው ሳምንት በሊጉ መሪ ሽንፈት ከገጠማቸው በኋላ ነገ በሌላ ጠንካራ ፍልሚያ የሊጉን ሁለተኛ ቡድን ያገኛሉ። ዓመቱ ከመጀመሩ አስቀድሞ ጥቂት ጎሎችን ሊያስተናግዱ ይችላሉ ተብለው ከሚገመቱ ቡድኖች ውስጥ የነበሩት አዞዎቹ አሁን ላይ 29 ጎሎች ተቆጥረውባቸው በሊጉ በርካታ ግቦች ያስተናገዱ ሰባተኛ ክለብ ሆነዋል። ይህ መሆኑም ቡድኑ ቢያንስ ከኋላ በነበረው ጠንካራ ጎኑ ላይ ተመስርቶ ሌሎች ድክመቶቹን በማሻሻል ላይ እንዳያተኩር እንቅፋት የሆነበት ይመስላል። ነገም ከሊጉ 3ኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ጋር እንደመገናኘቱ የመከላከል አደረጃጀቱን በቀደመ ጥንካሬው ላይ እንዲገኝ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ባህር ዳር ከተማ በነገው ጨዋታ አለልኝ አዘነን በአምስት ቢጫ ካርድ የሚያጣ ሲሆን በአርባምንጭ ከተማ ግን በኩል የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና የለም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ነገ ለአራተኛ ጊዜ የሚገናኙ ይሆናል። በእስካሁኖቹ ጨዋታዎች አርባምንጭ ከተማ ሁለት ጊዜ ባህርዳር ከተማ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ሲያደርጉ ሁለቱም ዕኩል ሦስት ጎሎችን አስመዝግበዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በመሐል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና አስቻለው ወርቁ ረዳቶች ፣ ሀብታሙ መንግስቴ አራተኛ ዳኛ በመሆን ለዚህ ጨዋታ ተመድበዋል።

ኢትዮጵያ ቡና ከ አዳማ ከተማ

በዕኩል 30 ነጥቦች 6ኛ እና 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ቡና እና አዳማ በጥሩ ድሎች ከደመደሙት 21ኛው ሳምንት በኋላ ነገ ተጠባቂ ፉክክር እንደሚያስተናግድ በሚጠበቀው ጨዋታ ምሽት 12:00 ላይ ይገናኛሉ።

ኢትዮጵያ ቡና በውድድር ዓመቱ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ድሬዳዋ ከተማን ከረታ በኋላ ለነገው ጨዋታ ደርሷል። ከዚያ ቀደም ከወልቂጤ ከተማው የ1-0 ድል ውጪ ሰባት ተከታታይ አቻዎችን ላስመዘገበው ቡድን ይህ ዓይነት ድል አስፈላጊው ነበር። በጨዋታው በተለይም የፊት መስመር ተሰላፊዎቹ ያሳዩት መነቃቃት ደግሞ ይበልጥ የቡድኑ በጎ ዜና ነው። ይህንን ድል ለማስቀጠል ግን በጥሩ ወቅታዊ አቋም ላይ ከሚገኘው አዳማ ከተማ ቀላል ፈተና የሚጠብቀው አይመስልም። በተለይም በኢትዮጵያ ቡና የጨዋታ ሂደት ጉልህ ሚና ያለው አማካይ ክፍሉ ከነገ ተጋጣሚው መሀል ሜዳ የሚገጥመውን ፍልሚያ በበላይነት መቆጣጠር ዋነኛ ፈተናው እንደሚሆን ይገመታል። በመጨረሻ ሰባት ጨዋታዎቹ ሦስት ግቦች ብቻ የተቆጠረበት የኋላ መስመሩም የተጋጣሚውን ፈጠን ያሉ ጥቃቶች የሚመክትበት አኳኋን ከጨዋታው ተጠባቂ ነጥቦች ውስጥ ይካተታል።

በወጣት ተጫዋቾቹ ወጥ አቋም እየታገዘ ከሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ተላቆ 30 ነጥብ ላይ የደረሰው አዳማ ከተማ መልካም የሚባል ጊዜ ላይ ይገኛል ። በመሀል በቅዱስ ጊዮርጊስ እና ሀዋሳ ከተማ ገጥመውት የነበሩትን ሽንፈቶች በመጨረሻዎቹ ሁለት ድሎች አካክሶም ለነገው ፍልሚያ የሚደርስ ይሆናል። አዳማ በመከላከል ወቅት አልፎ አልፎ የሚታዩበት ግለሰባዊ ስህተቶች ለአደጋ ሲያጋልጡት ይታይ እንጂ በማጥቃቱ ረገድ ጠንካራ ጎኑ ጎልቶ ይታያል። አማካይ ክፍል ላይ ልምድ ያላቸው የእነመስዑድ እና አማኑኤል ጥምረት ከአዳናን እና ስድስተኛ ጎሉ ላይ በደረሳው ዮሴፍ ታረቀኝ በሚመራው የፊት መስመሩ ጋር ያለው ተግባቦት እያደገ ይገኛል። ይህ ሂደት በመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት ተሳትፎ ታጅቦ አዳማ በመጨረሻዎቹ ስምንት ጨዋታዎች ከአንዱ በቀር በሌሎቹ ላይ ግብ እያስቆጠረ እንዲወጣ አስችሎታል። ነገ ደግሞ ይህንን ጥሩ የማጥቃት ተግባቦት ከካስ ጋር ጥሩ ከሆነው ተጋጣሚው ጋር መድገም የአዳማ ቀጣዩ ፈተና ይሆናል።

በጨዋታው ኢትዮጵያ ቡና ከአስራት ቱንጆ ሌላ ጫላ ተሺታ እና አብዱልሀፊስ ቶፊቅ ከጉዳት ያልተመለሱለት ሲሆን አዳማ ከተማ ዳዋ ሆቴሳ በጉዳት አብዲሳ ጀማል እና ዊሊያም ሰለሞን በዲስፕሊን ምክንያት የማይጠቀምባቸው ተጫዋቾች ናቸው።

\"\"

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም 41 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 23 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። አዳማ ከተማ በበኩሉ 7 ጊዜ ድል ሲቀናው በ11 ጨዋታዎች ደግሞ ቡድኖቹ አቻ ተለያይተዋል። በሁለቱ የእርስ በርስ ግንኙነት ቡና 73 ፤ አዳማ 35 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና አብዱ ይጥና በረዳትነት ፣ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ ይመሩታል።