ሪፖርት| አዞዎቹ እና የጣና ሞገዶችን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

የባህር ዳር ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ጨዋታ ሁለት ለሁለት በሆነ አቻ ውጤት ተፈፅሟል።

አዞዎቹ በፈረሰኞቹ ከተረታው ስብስብ አቡበከር ሻሚልን በእንዳልካቸው መስፍን ተክተው ሲገቡ የጣና ሞገዶቹ በበኩላቸው ከመድን ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ የአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያለበት አለልኝ አዘነን በፍቅረሚካኤል ዓለሙ ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

ሁለቱም ቡድኖች በምያደርጓቸው ፈጣን እንቅስቃሴዎች ታጅቦ አሀዱ ያለው ጨዋታው በመጀመርያዎቹ አምስት ደቂቃዎች ሁለት ድንቅ የቅጣት ምት ግቦች ተቆጥረውበታል። በመጀመርያ ግብ ያስቆጠሩት የጣና ሞገዶቹ ሲሆኑ ፍራኦል መንግሥቱ በቀኝ መስመር አከባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ መትቶ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም አዞዎቹ በተመሳሳይ መንገድ አፀፋዊ ምላሽ ለመስጠት አልሰነፉም። እንዳልካቸው መስፍን በተመሳሳይ ቦታ በቀኝ መስመር የተገኘውን ቅጣት ምት በቀጥታ ወደ ግብነት ቀይሮ አዞዎቹ አቻ ማድረግ ችሏል።

ሁለቱም ቡድኖች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ የተወሰነ ተቀዛቅዞ ጥራት ያላቸው ሙከራዎች ያላስመለከተን ጨዋታው በኳስ ቁጥጥር ረገድ የጣና ሞገዶቹ ብልጫ የታየበት አጋማሽ ነበር። አርባምንጮችም ለወትሮው በሚታወቁበት የጥብቅ መከላከል ላይ የተመሰረት አጨዋወት ተከትለው በረዣዥም ኳሶች ያልተሳኩ የማጥቃት ሙከራዎች አድርገዋል። ከግቦቹ በኋላም በሁለቱም ቡድኖች እስከ አጋማሹ መባቻ ድረስ ጥራት ያላቸው የግብ ዕድሎች አልተፈጠሩም።

ከዕረፍት መልስም በተመሳሳይ መንገድ የቀጠለው ጨዋታው ጣና ሞገዶቹ ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው ጥረታቸው የቀጠሉበት ነበር ፤ ጫናው ተከትሎም በአደም አባስ አማካኝነት ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ችለዋል። ተጫዋቹ በሀብታሙ እና ፉዐድ ጥረት በፈጣን የመልሶ ማጥቃት የመጣው ኳስ በነፃ አቋቋም ላይ ሆኖ ነበር ያመከነው። 

በ68ኛው ደቂቃም በፈጠሩት ጫና ጥረታቸው ሰምሮ በፉዐድ ፈረጃ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዋል። ከአሸናፊ ፊዳ ወደ መኮንን የተመለሰው ኳስ ግብ ጠባቂው ሀብታሙን ለማለፍ በሰራው ስህተት ኳሷ ተነጥቆ ፉዐድ ወደ ግብነት ቀይሯታል። በግቧ መቆጠር የሀብታሙ ድርሻ ትልቅ ነበር።

ከጨዋታው መጀመር አንስተው በረዣዥም ኳሶች ለማጥቃት ጥረት ያደረጉት አዞዎቹ በሰባ ስድስተኛው ደቂቃ ላይ አሕመድ ሁሴን ከተከላካዮች ጀርቦ አምልጦ በመግባት ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ከአዞዎቹ የአቻነት ግብ በኋላ ሁለቱም ቡድኖች በረዣዥም ኳሶች ዕድሎች ለመፍጠር ቢሞክሩም ምንም ሙከራ ሳይደረግ ጨዋታው ተጠናቋል።

ከጨዋታው መጠናቁቅ በኋላ በመጀመርያ አስተያየታቸው የሰጡት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በተከታታይ ትላልቅ ቡድኖች መግጠማቸው ድካም እንደፈጠረላቸው ገልፀው በቀጣይ ጨዋታዎች ድክመቶቻቸው ለማሻሻል እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።

አሰልጣኝ ደግአረግ በበኩላቸው በሁለቱም አጋማሾች ባሳዩት እንቅስቃሴ ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልፀው ለመከተል ያሰቡት አጨዋወት እንዳልተገበሩም ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም አቻ ብንወጣም ጊዜው ገና ስለሆነ በድክመቶታችን ሰርተን ለቀጣይ ጨዋታዎች እንዘጋጃለን ካሉ በኋላ ተጫዋቾቻቸው ጨዋታውን ለማሸነፍ ያሳዩት ተነሳሽነት ቀዝቃዛ እንደነበር ገልፀዋል።

\"\"