ሪፖርት| አራት ግቦች ከሳቢ እንቅስቃሴ ጋር የታየበት ጨዋታ ቡና እና አዳማ አቻ ተለያይተዋል

ኢትዮጵያ ቡና እና አዳማ ከተማን ያገናኘው ጨዋታ በዛሬው ዕለት ሁለት ለሁለት አቻ የተጠናቀቀ ሁለተኛ ጨዋታ ሆኗል።

\"\"

የዛሬው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች አሸናፊ ቡድናቸው ሳይቀይሩ የጀመሩበት ጨዋታ ነበር። ሁለት ተመሳሳይ ለኳስ ቁጥጥር ብልጫ ለመውሰድ የሚሞክሩ ቡድኖችን ያገናኘው ጨዋታ እንደተጠበቀው ጥሩ የኳስ ፍሰት የታየበት ጨዋታ ነበር። በጨዋታው ግብ በማስቆጠር ረገድ ቀዳሚ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች ሲሆኑ በሶስተኛው ደቂቃ ላይ መሐመድኑር ናስር ከመዓዘን የተሻማን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ በኋላ አዳማዎች በማጥቃት አጨዋወታቸው ላይ የተወሰኑ ለውጦች በማድረግ ዮሴፍ ታረቀኝን ዒላማ ያደረጉ አጨዋወት መርጠው የበለጠ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል። ይህንን ተከትሎም በሀያ ሁለተኛው ደቂቃ ዮሴፍ ከግራ መስመር የተቀበለው ኳስ ተከላካይ ቀንሶ ለአድናን አቀብሎት ተጫዋቹ ግቧን አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።


በሁለቱም ቡድኖች በኩል በሚደረጉ ፈጣን የማጥቃት አጨዋወቶች የቀጠለው ጨዋታው በሁለቱም ረገድ የነበረው ማራኪ እንቅስቃሴ ጨዋታው ሳቢ እንዲሆን አስችሎታል ፤ በሰላሳ ሰባተኛው ደቂቃም በኢትዮጵያ ቡና ሳጥን ውስጥ በተሰራው ጥፋት ተከትሎ የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ደስታ ዮሐንስ ወደ ግብነት ቀይሮ አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል። አጋማሹም በአዳማ ከተማ መሪነት ተጠናቋል።


በመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ የማጥቃት አጨዋወት ሲጫወቱ የነበሩት አዳማ ከተማዎች በዚህኛው ግማሽ በእጃቸው የገባውን ውጤት ለማስጠበቅ ሲጥሩ ታይቷል። እርግጥ አጋማሹ እንደተጀመረ በመስዑድ እና ተቀይሮ በገባው ቢኒያም አማካኝነት መሪነታቸውን ሊያሳድጉ ነበር። ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ፍለጋ መታተር የያዙት ኢትዮጵያ ቡናዎች በበኩላቸው በ64ኛው ደቂቃ የአቻነት ግብ ቢያገኙም ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ተሽሮባቸዋል። ይህ ጎል የተሻረበት አንተነህ ከደቂቃዎች በፊት ሌላ ሙከራ ሰንዝሮ ተመልሷል።

ጨዋታው 74ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ አዳማዎች ጨዋታውን የሚገሉበትን ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል አግኝተው ነበር። በዚህም ቢኒያም አይተን በተከላካዮች መሀል የደረሰውን ኳስ በወረደ አጨራረስ አምክኖታል። ይህ ተጫዋች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም ሌላ ዕድል አግኝቶ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በሁለቱ የአዳማ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች መሐል ግን ቡናማዎቹ በረጅም ኳስ አቻ ለመሆን ተቃርበው የግብ ዘቡ ሰዒድ ሀብታሙ አምክኖባቸዋል።


ኢትዮጵያ ቡናዎች በ79ኛው ደቂቃ የልፋታቸውን ውጤት አግኝተዋል። በዚህም የቡድኑን የመጀመሪያ ጎል ያስቆጠረው መሐመድኑር ከግራ መስመር ኃይለሚካኤል ያሻማውን ኳስ በሚገርም ሁኔታ በግራ እግሩ መረብ ላይ አሳርፎታል። ሳቢ ፉክክር ያሳየው ጨዋታው በቀሪ ደቂቃዎች መሪ ሳያገኝ በአቻ ውጤት ተጠናቋል።


ከጨዋታው በኋላ የኢትዮጵያ ቡናው አሠልጣኝ ዮሴፍ ከመጀመሪያው አጋማሽ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ እንደተንቀሳቀሱ ገልፆ እንደ ቡድን እያደገ የመጣ እንደሆነ አመላክተው የአቻ ውጤቱ በቂ እንደሆነ ሲገልፁ ተሰምቷል። የአዳማ ከተማው አሠልጣኝ ይታገሱ እንዳለ በበኩሉ ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ፈጣን እንደነበር ተናግረው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች በማጥቃቱ ረገድ መሻሻል ቢያሳዩም ያገኙትን ዕድል መጠቀም አለመቻላቸው ዋጋ እያስከፈላቸው እንደሆነ ተናግረው በጨዋታው ከአቻ ውጤት በላይ እንደሚገባቸው ገልፀዋል።

\"\"