መቻል በከነዓን ማርክነህ እና እስራኤል እሸቱ ግቦች ድሬዳዋ ከተማን 2-1 መርታት ችሏል።
9 ሰዓት ላይ በተጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ድሬዳዋ ከተማዎች በራሳቸው የግብ ክልል ውስጥ በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ እና ዝግ ባለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ሲቀር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመግባት እና ክፍት ቦታዎችን ሸፍኖ የተጋጣሚ ቡድንን ክፍት ቦታ በማግኘት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የታዩት መቻሎች 13ኛው ደቂቃ ላይም ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በኃይሉ ኃይለማርያም አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ በግራው የሳጥኑ ክፍል የገባው ከነዓን ማርክነህ በግሩም አጨራረስ አስቆጥሮታል።
በዚሁ የአጨዋወት ሂደት ስኬታማ የሆኑት መቻሎች 22ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። ከነዓን ማርክነህ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ሳይረጋጋ ያገኘው ሳሙኤል ሳሊሶ ኳሱን በጉልበቱ መትቶት የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር እጅግ የተቸገሩት ብርቱካናማዎቹ በቁጥር በዝተው በሚገኙበት ሳጥናቸው ውስጥም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች እና በአቋቋም በነበራቸው ትልቅ ክፍተት 25ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። የተሳካ አጋማሽ ያሳለፈው ወጣቱ በኃይሉ ኃይለማርያም ከሳጥኑ የቀኝ ጠርዝ ላይ ሆኖ የቀነሰውን ኳስ ያገኘው እስራኤል እሸቱ በቀላሉ መረቡ ላይ አሳርፎታል።
መሃል ሜዳው ላይ ብልጫ የተወሰደባቸው ድሬዎች በተለይም የግብ ዕድሎችን መፍጠር የሚጠበቅበት ዳዊት እስጢፋኖስ በተደጋጋሚ በሚሠሩበት ጥፋቶች ልዩነት መፍጠር አለመቻሉ ለመቸገራቸው አንዱ ምክንያት ቢሆንም ሦስቱንም የሜዳ ክፍሎች የሚያገናኝ የግንኙነት መስመር በተደራጀ ሁኔታ ባለመሥራታቸው ተጨማሪ ግብ አለማስተናገዳቸው ዕድለኛ ሲያደርጋቸው አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ አጋማሹ ተገባዷል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በኳስ ቁጥጥሩ ከእጥፍ በላይ ብልጫ የነበራቸው ድሬዳዋ ከተማዎች ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ ይቸገሩ እንጂ የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ችለው ነበር። በአንጻሩ በመቻል በኩል በርካታ ንጹህ የግብ ዕድሎች ቢፈጠሩም ከጨዋታ ውጪ በሆነው አቋቋማቸው ሳይጠቀሙበት ሲቀር አብዛኞቹ ውሳኔዎች ግን አንደኛ ረዳት ዳኛ በነበሩት ሶርሳ ዱጉማ በስህተት በሚነሳው ባንዲራ የተቋረጡ ነበሩ።
የጨዋታው የመጨረሻ 10 ደቂቃ የተሻለ እንቅስቃሴ ሲደረግበት 82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የመቻሉ በረከት ደስታ ከግራ መስመር ወደ መሃል በመግፋት ከሳጥን ውጪ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስበት 88ኛው ደቂቃ ላይ በድሬዳዋ በኩል ጋዲሳ መብራቴ ከእንየው ካሳሁን ጋር በቀኝ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ተቀባብሎ ባመጣው ኳስ ያደረገው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ ይዞታል። ይህም በሁለተኛው አጋማሽ (በድሬዳዋ ከተማ በኩል በሙሉ የጨዋታው ክፍለጊዜ) የተደረገ የመጀመሪያው ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር። ሆኖም 96ኛው ደቂቃ ላይ ሙኸዲን ሙሳ ግብ አስቆጥሮ ብርቱካናማዎቹን ለባዶ ከመሸነፍ አድኗል። ጨዋታውም በመቻል 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ አስራት አባተ በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እንዳልነበሩ እና በጊዜ ያስተናገዷቸው ግቦች ለመነሳት እንዳስቸገሯቸው ገልጸው ተጋጣሚያቸው ኃይል በመቀላቀል የመረጠው በረጃጅም ኳስ መጫወት እንደረበሻቸው እና ከዕረፍት በኋላ አሰላለፋቸውን 4-3-3 በማድረግ የተሻለ እንደተጫወቱ ግን መቻል የመረጠው የመከላከል አጨዋወት እንደፈተናቸው በመጠቆም ከኋላ ያለውን አደረጃጀት በማስተካከል በከፍተኛ ጥረት እና ሥራ ሀዋሳ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው ሦስት ነጥብ ማግኘታቸው ዋናው ጥሩ ነገር እንደሆነ በማስቀደም የመጀመሪያው 30 ደቂቃ እንደፈለጉት እንደተንቀሳቀሱ ከዕረፍት መልስ ግን በስህተት የታጀበ እንቅስቃሴ በማድረግ ከጨዋታው መውጣታቸውን ሲናገሩ የተጋጣሚ ቡድን የሚተወውን ክፍት ቦታ ለመጠቀም አስበው እንደገቡ እና ይህም እንደገጠማቸው በመግለፅ የዛሬው ውጤት ለቀጣዩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ መነቃቃት እንደሚፈጥርላቸው ተስፋ መሰነቃቸውን ሲጠቁሙ የወጣቱን አማካይ በኃይሉ ኃይለማርያም እንቅስቃሴ አድንቀዋል።