የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቤንች ማጂ ቡና ጨዋታ ያለጎል ሲጠናቀቅ ሀምሪቾ ዱራሜ በበኩሉ መሪነቱን ዳግም የሚይዝበትን ዕድል ሳይጠቀም ጨዋታውን አቻ ፈፅሟል።
በጫላ አቤ
ምድብ ሀ
በዚህ ምድብ በተደረገ የቀኑ የመጀመሪያ ጨዋታ ሀላባ ከተማ እና አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል። ቀትር ስድስት ሰዓት ላይ በደረጃ ሰንጠረዡ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ቤንች ማጂ ቡናን ያገናኘው ጨዋታ መሪነቱን ለማግኘት ፉክክር ቢደረግበትም አሸናፊ ሳያገኝ 0ለ0 ተገባዷል።
ቀሪው የ8 ሰዓት ጨዋታ የሆነው የሰበታ ከተማ እና ሰንዳፋ በኬ ጨዋታም አቻ ተጠናቋል። የሰበታን ጎል ብሩክ ግርማ ሲያስቆጥር የሰንዳፋ በኬን የአቻነት ጎል ደግሞ የሰበታው ተጫዋች ናትናኤል ጋንጩላ በራሱ ላይ አስቆጥሯል።
ምድብ ሐ
በምድብ ሐ የተደረገው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ የሆነው የደሴ ከተማ እና የካ ክ/ከተማ መርሐ-ግብርም በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ክለቦች በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን ደሴ ከተማዎች በመሀል ተጫዋቾቻቸው ኳስን ተቆጣጥረው በእርጋታ ለመጫወት ሲሞክሩ የካ ክ/ከተማዎች ደግሞ ያገኙትን ኳስ ወደ ግብ ለመለወጥ ጥረት አድርገዋል። ይህንንም ተከትሎ የካ ክ/ከተማዎች ጨዋታው በተጀመረ በ1ደቂቃ ውስጥ ያገኙት ግልፅ የማግባት እድል ማቲያስ ሹመቴ ማባከተን ችሏል። ደሴ ከተማዎችም ጥሩ ጥሩ የሚባሉ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለው ቢሆንም መጠቀም ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ አጨዋወትን ሲያስመለክት በማናዬ ፋንቱ የሚመራው የደሴ ከተማው የፊት መስመር ጥሩ ጥሩ የሚባሉ የግብ እድሎችን መፍጠር የቻለ ሲሆን የሁለቱም ክለቦች የኋላ መስመር ጥንካሬ የተመለከትንበት ጨዋታ በመሆኑ በጨዋታው ምንም ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የምድቡ ተጠባቂ ጨዋታ የሆነው የነጌሌ አርሲ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ ጨዋታ ስድስት ግቦች ተቆጥረውበት በአቻ ውጤት ተጠናቋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና ፈጣን የሆነ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት እና አጓጊ የሆነ የአልሸነፍ ባይነት ስሜት የተሞላበት ጨዋታ ሲሆን የመጀመሪያው አጋማሽ የአርሲ ነጌሌዎች የበላይነት የታየበት እና በመሀል ክፍላቸው ብሩክ ቦጋለ ድንቅ አጨዋወትና ጥሩ ፍሰት ያለው አጨዋወትን ሲያስመለክተን ይህንንም ተከትሎ ጨዋታው በተጀመረ በ6ኛው ደቂቃ ላይ ነጌሌ አርሲዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ብሩክ ቦጋለ ድንቅ በሆነ ሁኔታ በማስቆጠር መሪ መሆን ችለዋል። ከግቧ መቆጠር በኋላም ነጌሌ አርሲዎች የበለጠ ተነቃቅተው ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ በ25ኛው ደቂቃ ሀምበሪቾ ዱራሜዎችም የሚያገኙትን ኳስ ወደ ግብ ለመቀየር ወደ ፊት ተስበው ለመጫወት ሲሞክሩ ነጌሌ አርሲዎች ያገኙትን ክፍተት ብሩክ ቦጋለ ያሻገረለትን ኳስ ምስጋናው መላኩ ግብ አስቆጥሮ ነጌሌ አርሲ በሁለት ግብ ልዩነት እዲመራ አድርጓል። ከግቡ በቆጠር በኋላ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ውጤቱን ለመገልበጥ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በ33ኛው ደቂቃ ያገኙትን የግብ እድል ትዕግስቱ አበራ በማስቆጠር አጋማሹ ተጠናቆ በነጌሌ አርሲ የበላይነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ነጌሌ አርሲ የበላይነቱን የወሰደበት አጋማሽ ሲሆን በ62ኛው ደቂቃ ላይ ነጌሌ አርሲዎች ያገኙትን ኳስ በያሬድ መሀመድ አማካኝነት ወደ ግብ ቀይረው በሁለት ግብ ልዩነት ድጋሚ ነጌሌ አርሲ እንዲመራ ማረግ ሲችል ሀምበሪቾ ዱራሜ ከሽንፈት ለመዳን ያላቸው አቅም ተጠቅመው ግብ ለማስቆጠር ጫና የፈጠሩ ሲሆን በ85ኛው ደቂቃ ተቀይሮ የገባው ሰለሞን ጌታቸው የተሻማውን ኳስ ጨርፎ በማስቆጠረ ለሀምበሪቾ ዱራሜ ሁለተኛውን ግብ አስቆጥሮ የግብ ልዩነቱን ወደ አንድ ዝቅ አድርጓል። ብዙም ሳይቆይ በ88ኛው ደቂቃ በድጋሜ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ያገኙትን ኳስ በረከት ወንድሙ በማስቆጠር ክለቡን ከሽንፈት መታደግ ችለዋል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተገባዷል።
የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የኮልፌ ክ/ከተማ እና ዳሞት ከተማ ጨዋታ ግን በመሸናነፍ ተጠናቋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ እና እልህ የተሞላበት አጨዋወት የተመለከትን ሲሆን ኮልፌ ክ/ከተማ በኳስ ቁጥጥሩ ተሽለው ሲገኙ በአንፃሩ ዳሞት ከተማ ወደኋላ በማፈግፈግ በፊት አጥቂያቸው ሱልጣን አቢዩ አማካኝነት የመልሶ ማጥቃትን በማፋጠን የግብ እድል ለመፍጠር ሲጥሩ ተስተውሏል። ይህንንም ተከትሎ በ21ኛው ደቂቃ ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን ኳስ ጌታቸው ካሳሁን ግብ አስቆጥሮ መሪ መሆን ሲችሉ ኮልፌ ክ/ከተማዎች በፊልሞን ገ/ፃድቅ እየተመሩ በ35ኛው ደቂቃ ያገኙትን ኳስ በሙባረክ ጅላል አማካኝነት አስቆጥረው ኮልፌ ክ/ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ የኮልፌ ክ/ከተማ የበላይነት የታየበት አጋማሽ ሲሆን ግብ ለማስቆጠር ጫና ሲፈጥሩ በ60ኛው ደቂቃ ፊልሞን ገ/ፃዲቅ ወደ ግብ በመቀየር ኮልፌ ክ/ከተማ መሪ ማድረግ ሲችል ካገቡ በኋላ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው በ79ኛው ደቂቃ ዮናስ ወልዴ ለኮልፌ ክ/ከተማ ሶስተኛውን ግብ አስቆጥሯል። ብዙም ሳይቆይ በ84ኛው ደቂቃ ዳሞት ከተማን ከሽንፈት ያላዳነች ግብ አበበ ታደሰ ግብ ያስቆጠረ ሲሆን ጨዋታውም በኮልፌ ክ/ከተማ አሸናፊነት ተጠናቆ ሶስት ነጥብ አሳክቷል።