መረጃዎች | 91ኛ የጨዋታ ቀን

በሀዋሳ የሚከናወኑትን የ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች የተመለከቱ መረጃዎችን እነሆ።

ሀዋሳ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአዳማ ቆይታውን አጠናቆ ወደ ሀዋሳ ሲሻገር የመጀመሪያው ጨዋታ መቀመጫቸውን በከተማዋ ባደረጉት ሁለቱ ቡድኖች መካከል ይደረጋል።

ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና እስካሁን በሱብሰቡት የነጥብ ብዛት ደረጃቸው ተራርቆ ይገኛል። ለወትሮው በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የማይጠፋው ሲዳማ ቡና ዘንድሮ በደካማ የውድድር ዓመት ውስጥ አልፎ በ21 ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ይገኛል። በአስር ነጥቦች ልቆ የተቀመጠው ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በሰንጠረዡ አጋማሽ ተቀምጧል። ይሁን እንጂ የሀዋሳ የመጨረሻ የአዳማ ትዝታም ጥሩ የሚባል አልሆነም። በፋሲል ከነማ እና ድሬዳዋ ከተማ የገጠሙት ሁለት የ1-0 ሽንፈቶች ቡድኑ እስከ አራተኛ ደረጃ ከፍ ማለት የሚችልበትን ዕድል አሳጥተውታል። በአንፃሩ በሲዳማ ቡና የውጤት ዝርዝር ውስጥ የመጨረሻውን ድል ለማግኘት ሰባት ጨዋታዎችን ወደ ኋላ መጓዝ ይኖርብናል። ወቅታዊ አቋማቸው ይህን መሳይ ይሁን እንጂ ወደ መቀመጫ ከተማቸው በሚመለሱበት የነገው ጨዋታ ቡድኖቹ የሚያደርጉት ፍልሚያ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

\"\"

በጨዋታው ሀዋሳ ከተማ ወንድምአገኝ ኃይሉ እና ብርሀኑ አሻሞን በጉዳት ሲያጣ ሲዳማ ቡናም ሙሉዓለም መስፍን ፣ ቴዎድሮስ ታፈሰ እና ሳላሀዲን ሰይድን በጉዳት የማያገኝ ሲሆን ያኩቡ መሐመድ ግን ተመልሶለታል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በ25 ጨዋታዎች ተገናኝተዋል። ሲዳማ ቡና ዘጠኝ ሀዋሳ ከተማ ደግሞ ስምንት ጊዜ ሲያሸንፉ ቀሪዎቹ ስምንት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በጨዋታዎቹ በድምሩ 56 ኳሶች መረብ ላይ ሲያርፉ ሲዳማ 30 ሀዋሳ ደግሞ 26 ጎሎች አስቆጥረዋል።

ኢንተርናሽናል ዳኛ ኃይለየሱስ ባዘዘው በመሐል ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ፋሲካ የኋላሸት በረዳትነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ አራተኛ ዳኛ ሆነው ይህንን ጨዋታ በጋራ ይመራሉ።

ወልቂጤ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የጨዋታ ሳምንቱ የመጨረሻ ፍልሚያ ሰራተኞቹን ከፈረሰኞቹ ያገናኛል።

ከወራጅ ቀጠናው እምብዛም ያልራቀው ወልቂጤ ከተማ ከቅርብ ተፎካካሪዎቹ ሲዳማ ቡና እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር ካደረጋቸው ጨዋታዎች አራት ነጥቦች ካሳካ በኋላ የሊጉን መሪ ይገጥማል። ቡድኑ በመጨረሻ የአዳማ ጨዋታው ኤሌክትሪክን የመርታት ዕድሉን ከ2-0 መሪነት ነጥብ ወደ መጋራት በመምጣቱ ነበር ያጣው። በወቅቱ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አምበሉ ጌታነህ ከበደ የሰጠው አስተያየት መነጋገሪያ ሆኖ መሰንበቱም አይረሳም።

ተከታዩ ባህር ዳር ከተማ ነጥብ የጣለለት ቅዱስ ጊዮርጊስ መሪነቱን ወደ ሰባት የሚያሰፋበትን ዕድል ይዞ ወደ ሜዳ ይገባል። ነገ ወደ ሀዋሳ የሚያቀናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመሪነት ባሻገር በሦስት ተከታታይ ድሎች ነበር የአዳማ ጊዜውን የፈፀመው። ሜዳ ላይ ቢፈተኑም ተፈላጊውን ነጥብ ይዘው እየወጡ በሚገኙት ፈረሰኞቹ በኩል የትኩረት ማረፊያ የሆነው እስማኤል ኦሮ አጎሮም የግብ ብዛቱን 20 አድርሷል። ወደ አቡበከር ናስር ሪከርድ ለመድረስ የነገን ጨምሮ 9 ጨዋታዎች እጁ ላይ ያሉት ቶጓዊው አጥቂ የሀዋሳ ቆይታ ጅማሮም ከነገው ጨዋታ ይጠበቃል።

የወልቂጤ ከተማው አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ባጋጠማቸው መጠነኛ የጤና ዕክል ያለፉትን ቀናት ቡድኑን ልምምድ ያላሰሩ ሲሆን በነገው ጨዋታም ሜዳ እንደማይገኙ ታውቋል። በምክትል አሠልጣኙ ዳዊት እንደሚመራ የሚጠበቀው ቡድኑ ፋሲል አበባየሁ ፣ አንዋር ዱላ እና አፈወርቅ ኃይሉን በጉዳት ምክንያት ከነገው ጨዋታ አይጠቀምም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የጋቶች ፓኖም መድረስ አጠራጣሪ ሲሆን አማኑኤል ገብረሚካኤል ፣ ምኞት ደበበ እና አቤል ዮናስ ጉዳት ላይ ይገኛሉ።

\"\"

ሁለቱ ቡድኖች ነገ በሊጉ ስድስተኛ ጨዋታቸውን ሲያደርጉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቀዳሚዎቹን አራቱን አሸንፎ ዘንድሮ በመጀመሪያው ዙር ነጥብ ተጋርተዋል። በዚህም ጊዮርጊስ 15 ግቦችን ሲያስመዘግብ ወልቂጤ ሰባት አስቆጥሯል።

ለዚህ ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ በረዳትነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ ደግሞ አራተኛ ዳኛ በመሆን ይመሩታል።