ሪፖርት | ሲዳማ ቡና ከወራጅ ቀጠናው ቀና ብሏል

ሲዳማ ቡና ከእንቅስቃሴ ብልጫ ጋር ሀዋሳ ከተማን በመርታት አንድ ደረጃ ማሻሻል ችሏል።

ሲዳማ ቡናዎች ባለፈው ጨዋታ ከተጠቀሙበት አሰላለፍ ሰለሞን ሀብቴ ፣ መሐሪ መና ፣ ፀጋዬ አበራ እና ፍሊፕ አጄህን በደስታ ደሙ ፣ አማኑኤል እንዳለ ፣ አቤል እንዳለ እና ቡልቻ ሹራ ቀይረው ገብተዋል። ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው በፋሲል ከነማ ከተሸነፈው ስብስብ ሰዒድ ሐሰንን አሳርፈው ዳንኤል ደርቤን ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

እንደተጠበቀው ብርቱ ፉክክር ያልታየበት ቀዳሚው አጋማሽ ንፁህ የግብ ዕድሎች እና ሙከራዎች ያልታዩበት ነበር። ሆኖም በኳስ ቁጥጥር ረገድ ሲዳማ ቡናዎች የተሻለ በመንቀሳቀስ በይገዙ እና ደስታ አማካኝነት ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም ከቆመ ኳስ ፍሬው ሰለሞን አሻምቶት ደስታ ደሙ በግንባር ያደረገው ሙከራ የተሻለ ለግብ የቀረበ ነበር። ይገዙ ቦጋለ ከቀኝ መስመር የተሻማውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራም ሌላ የሚጠቀስ ነው። በአጋማሹ ትኩረት ሳቢ ክስተት በ36ኛው ደቂቃ ፍሬው ሰለሞን በገጠመው ከበድ ያለ ጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል።

በጨዋታው ወደ ራሳቸው ግብ ክልል አፈግፍገው ጠጣር ሆነው ለመከላከል የሞከሩት ሀዋሳዎችም በሙጂብ ቃሲም አማካኝነት ለግብ የቀረበ ማድረግ ችለዋል። አጥቂው ኤፍሬም ያሻገረለትን ኳስ በቀጥታ መትቶ ግብ ጠባቂው በጥሩ ንቃት ያከሸፈበት ሙከራም የቡድኑ ብቸኛ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከመጀመርያው አጋማሽ በተለየ የሲዳማ ቡና ሙሉ ብልጫ የታየበት ሁለተኛው አጋማሽ ቡናማዎቹ ብልጫ ወስደው በርካታ የግብ ዕድሎች የፈጠሩበት ነበር። በአጋማሹ የመጀመርያ ደቂቃዎችም በእንዳለ አማካኝነት ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነው። ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች በሳጥን ያገኘው ኳስ ተጫዋች አልፎ መቶት ሰለሞን እና አላዛር ተጋግዘው ግብ ከመሆን አድነውታል።

በ63ኛው ደቂቃ ሲዳማዎች ጥረታቸው ሰምሮ በፍሊፕ አጄህ የግንባር ግብ መሪ መሆን ችለዋል። አጥቂው እንዳለ ከበደ ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ በግንባር በመግጨት ነበር ግቡን ያስቆጠረው።

ተቀይሮ ከገባ በኋላ በቡድኑ የማጥቃት አጨዋወት የሚታይ ለውጥ ያመጣው አጄህ ከርቀት አክርሮ መቶት አላዛር በድንቅ ብቃት የመለሰው ኳስም የሲዳማን የግብ መጠን ከፍ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር።
አጥቂው የጨዋታው ማጠናቀቅያ ፊሽካ ከመነፋቱ በፊትም በሳጥን ውስጥ ተጨዋቾችን አልፎ ሞክሮ ተቀይሮ ገብቶ ጥሩ እንቅስቃሴ ያሳየው ወጣቱ ግብ ጠባቂ አላዛር መልሶበታል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ \” ቡድኑ የተሻለውን ነገር አድርጓል ፤ ይህ ድል ይገባናል \” ያሉት አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በእያንዳንዷ ደቂቃ የምንችለው ነገር ለማድረግ ጥረናል ካሉ በኋላ ይህ ድል ለቀጣይ ጨዋታዎች የሞራል ስንቅ እንደሚሆናቸው ጠቅሰዋል። አሰልጣኙ በስተመጨረሻም ደጋፊዎችን አመስግነዋል።

\"\"

\”ጨዋታው እንደ ጠበቅኩት አይደለም\” ያሉት የሀዋሳ ከተማው አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ ያለፉት ሽንፈቶች በሥነ ልቦና ረገድ እንደጎዳቸው ገልፀው ያገኙትን ዕድሎች ያለመጠቀም ችግርም ዋጋ እንዳስከፈላቸው ገልፀዋል አሰልጣኙ ጨምረውም በሁለቱም ቡድኖች የታየው እንቅስቃሴ ጥንቃቄ የበዙበት የደርቢ ጨዋታ እንደማይመስልም ጠቅሰው በቀጣይ ተሻሽለው እንደሚመጡ ገልፀዋል።