ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ በሰባት ነጥብ ልዩነት መምራት ጀምሯል

በ22ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለት ደቂቃ ልዩነት በተቆጠሩ ጎሎች ወልቂጤ ከተማን 2-1 በማሸነፍ አራተኛ ተከታታይ ድል አስመዝግቧል።

\"\"

ሁለቱ ተጋጣሚዎች ከመጨረሻ ጨዋታዎቻቸው የአሰላለፍ ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ የገቡበት ጨዋታ ፈጠን ባለ እንቅስቃሴ ቢጀምርም አጋማሹ ሙከራዎች በብዛት የታዩበት አልሆነም። የተሻለ የማጥቃት ጫና አሳድረው የታዩት ጊዮርጊሶች በኩል 9ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው ከማዕዘን ምት በተነሳ ኳስ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጓል። ጊዮርጊሶች አጎሮን መዳረሻ ያደረጉ ቀጥተኛ ኳሶችን መላክ ሲቀጥሉ ወልቂጤ ከተማዎች ቀስ በቀስ በቅብብሎቻቸው ወደ ተጋጣሚ ሳጥን መድረስ ጀምረዋል። ሆኖም ቀጣዩ አደገኛ ሙከራም በፈረሰኞቹ በኩል ተደርጓል። 23ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ያለው በግራ ሰብሮ በመግባት ያመቻቸለትን ኦሮ አጎሮ ከሳጥን ውስጥ አክርሮ መትቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል።

\"\"

ወልቂጤዎች የኳስ ቁጥጥር ብልጫን እየወሰዱ ወደ ሳጥን የሚጠጉባቸው ቅፅበቶች ቀጥለው ቢታዩም ወደ ሙከራነት መቀየር አልቻሉም። ይልቁኑም የጊዮርጊስ ከመስመር የሚነሱ ኳሶች አደጋ ሊፈጥሩ ተቃርበው ነበር። 30ኛው ደቂቃ ላይ ረመዳን የሱፍ ከግራ መስመር ለቢኒያም በላይ ፣ ከሁለት ደቂቃ በኋላ ቢኒያም በላይ ከቀኝ መስመር ለአቤል ያለው እንዲሁም ጥቂት ቆይቶ ኦሮ አጎሮ ከግራ በድጋሚ ለአቤል ያለው ያደረሷቸው ኳሶች ወደ አደገኛ የግብ ዕድልነት ለመቀየር ተቃርበው ነበር። በወልቂጤ ከተማዎች በኩልም 44ኛው ደቂቃ ላይ ተመስገን በጅሮንድ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አቤል ነጋሽ በግንባሩ ሳያገኘው ቀረ እንጂ ቡድኑ በጎል ቀዳሚ ሊሆን ይችል ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ቀዝቅዘ ያለ አጀማመር ነበረው። የቡድኖቹ የማጥቃት እሳቤ እንዳለ ቢሆንም በሁለቱም ጎሎች ያሉት የመከላከል ውቅሮች እንቅስቃሴው በአመዛኙ መሀል ሜዳ ላይ እንዲገደብ አድርገዋል። ነገሮች በዚህ በቀጠሉበት ቅፅበት ግን ከአቤል ያለው እግር ስር የተነሱ ሁለት ኳሶች ጨዋታውን ሙሉ ለሙሉ ቀይረውታል።

\"\"

62ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ በግራ የተቀበለው ረመዳን የሱፍ ከሳጥን ውስጥ መትቶ ከመረብ አገናኝቶታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላም አቤል ከመሀል ወደ ቀኝ አድልቶ ወደ ፊት የለቀቀው ጊዜውን የጠበቀ ኳስ ይዞ በመግባት እስማኤል ኦሮ ኦጎሮ ሌላ ግብ አስቆጥሯል።

የግቦቹ ተከታታይነት ወልቂጤ ከተማዎች በቅብብሎች ወደ ፊት ይሄዱ የነበሩባቸው ሂደቶች ላይ ተፅዕኖ አሳድረው ቡድኑ በቶሎ ወደ ግብ ለመድረስ ሲሞክር ይታይ ነበር። ተከታታይ ቀያሪዎችን ያደረጉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ በአመዛኙ ለጨዋታ ቁጥጥር ቦታ በመስጠት በተረጋጉ ቅብብሎች የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ጥረዋል። ጨዋታው ወደ ማብቂያው ሲቃረብ ወልቂጤዎች ግብ አስቆጥረዋል። ተስፋዬ መላኩ በግል ጥረቱ ሳጥን ውስጥ ይዞ የገባውን ኳስ የጊዮርጊስ ተከላካዮች በአግባቡ ሳያርቁ ያገኘው ጌታነህ ከበደ ነበር ጎሏን ያስቆጠረው። ሆኖም ቀሪ ደቂቃዎች የውጤት ለውጥ ሳያመጡ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ 2-1 አሸናፊነት ተቋጭቷል።

\"\"

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የወልቂጤ ከተማው ምክትል አሰልጣኝ ዳዊት ሀብታሙ የመጀመሪያው ጎል እንደረበሻቸው እና ሁለተኛው በቶሎ መደገሙ ለመረጋጋት ዕድል እንዳልሰጣቸው ያነሱ ሲሆን ግብ ለማግኘት ባደረጉት ጥረት ውስጥ ጥድፊያ እንደታየባቸውም አንስተዋል። ጨዋታቸው ጥሩ ቢሆንም የመጨረሻ ኳሶች ላይ የመሳት ችግር እንደታየባቸው ያነሱት አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ሁሌም ለኳስ ቁጥጥር ትኩረት እንደሰጡ አስረድተው ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ ሳይረበሹ የቀሩትን ደቂቃዎች በአግባቡ ጨርሰው መውጣታቸውን ተናግረዋል።

\"\"