የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | የ26ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት ዛሬም ቀጥሎ ሲውል አዲስ አበባ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ድል ቀንቷቸዋል።

\"\"

ይርጋጨፌ ቡና 2-3 አዲስ አበባ ከተማ

ረፋድ 4 ሰዓት ላይ መጠነኛ ፉክክር እያስመለከተን በተጀመረው ጨዋታ ቀስ በቀስ ግን ፍጹም የበላይነት እያሳዩ የሄዱት አዲስ አበባዎች 15ኛው ደቂቃ ላይም ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ግቡንም አሥራት ዓለሙ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ውስጥ ሆና የቀነሰችው ኳስ በመዲና ጀማል አቅጣጫ ቀይሮ ያገኘችው ቤተልሔም መንተሎ አስቆጥራዋለች። 32ኛው ደቂቃ ላይም ንግሥት አስረስ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በድንቅ ሁኔታ መረቡ ላይ አሳርፋው የክለቧን መሪነት ስታጠናክር በአራት ደቂቃዎች ልዩነትም መዲና ጀማል ከሳጥን ውጪ ያደረገችው ግሩም ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ ሲመልስባት ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት አዲስ አበባ ከተማዎች በቤተልሔም መንተሎ እና ንግሥት አስረስም ተጨማሪ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ለተመልካች እጅግ ማራኪ በሆነ ፉክክር ታጅቦ ሲቀጥል በአጋማሹ ተሻሽለው የቀረቡት ይርጋጨፌዎች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ 54ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥረዋል። ግቡንም ፍሬሕይወት ተስፋዬ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ያገኘችው ዳግማዊት ሰለሞን በግንባሯ በመግጨት አስቆጥራዋለች። ሆኖም ግብ በተቆጠረባቸው ቅፅበት ፈጣን ምላሽ የሰጡት አዲስ አበባዎች 56ኛው ደቂቃ ላይ አምበሏ ሩታ ያደታ በቀኝ መስመር በድንቅ ክህሎት አታልላ በማለፍ አመቻችታ ባቀበለቻትና ኪፍያ አብዱራህማን በግንባሯ በመግጨት መረቡ ላይ ባሳረፈችው ኳስ በድጋሚ መሪነታቸውን ማስፋት ችለዋል። ተስፋ ባለመቁረጥ ወደ ድንቅ እንቅስቃሴያቸው የተመለሱት ይርጋጨፌዎች 66ኛው ደቂቃ ላይ በፍሬሕይወት ተስፋዬ አማካኝነት ሁለተኛ ግብ ሲያስቆጥሩ 85ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው አደራ አናጋው ያደረገችው ግሩም ሙከራ በግቡ አግዳሚ ተመልሶባታል። ጨዋታውም በአዲስ አበባ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

አዳማ ከተማ 0-2 አርባምንጭ ከተማ

9 ሰዓት ሲል በተጀመረው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በአዳማ ከተማ በኩል 12ኛው ደቂቃ ላይ ሳባ ኃ/ሚካኤል ከሳጥን ውጪ ወደ ግራው የሜዳ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ያደረገችው ግሩም ሙከራ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰባት በአርባምንጭ ከተማ በኩል አጋማሹ ሊገባደድ በተጨመሩ የባከኑ ደቂቃዎች ውስጥ ከአምላክነሽ ሀንቆ ከቀኝ መስመር ያሻገረችው እና መሠረት ወርቅነህ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ የመለሰችባት ኳስ የተሻሉ የግብ ዕድሎች ነበሩ።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል 48ኛው ደቂቃ ላይ የአዳማ የማጥቃት እንቅስቃሴ መነሻ የሆነችው ሳባ ኃ/ሚካኤል ከሳጥኑ የግራ ጠርዝ ላይ ፈታኝ ሙከራ አድርጋ በግብ ጠባቂዋ ሲመክንባት 57ኛው ደቂቃ ላይ የአርባምንጯ ቤተልሔም ታምሩ ተከላካይ በማለፍ ከግብ ጠባቂ ጋር ብትገናኝም የግብ ዕድሉን ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ሆኖም ራሷ ቤተልሔም ታምሩ 67ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ ስታደርግ 89ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ድንቅነሽ በቀለ ተጨማሪ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በአርባምንጭ ከተማ 2-0 አሸናፊነት እንዲጠናቀቅ አስችላለች።