ወላይታ ድቻ እና አዳማ ከተማ 1-1 ተለያይተዋል።
ወላይታ ድቻዎች ባለፈው ሳምንት ካሸነፈው ስብስብ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ሜዳ ሲገቡ አዳማ ከተማዎችም አቻ ከተለያየው አሰላለፍ ጀሚል ያዕቆብበ አዲስ ተስፋዬ ቀይረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
ሁለት የተለያዩ አቀራረብ ይዘው የቀረቡ ቡድኖች ያገናኘው ጨዋታ በንፁህ የግብ ዕድል ፈጠራ ረገድ ጥቂት ዕድሎች የተፈጠሩበት ነበር። በአጋማሹ ወላይታ ድቻዎች ወደ ራሳቸው ግብ ክልል ተጠግተው በመከላከል በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች ለመፍጠር ሙከራ ያደረጉበት ፤ አዳማ ከተማዎችም የኳስ ቁጥጥር ብልጫ በመውሰድ ለመጫወት ቢሞክሩም የወላይታ ድቻ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው ሙከራዎች ያደረጉባቸው አጋጣሚዎች ጥቂት ናቸው።
ሆኖም በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ዮሴፍ በመልሶ ማጥቃት የሄደው ኳስ ተጠቅሞ ባደረገው ሙከራ የግብ ዕድሎች ለመፍጠር ችለዋል። አዳማዎች ከተጠቀሰው ሙከራ ውጭም በቁጥር በርከት ብለው መስዑድ ፣ አሜ እና አድናን ሆነው በጥሩ ቅብብል ወደ ሳጥን ያስቀጠሉት የማጥቃት እንቅስቃሴ አድናን መትቶት ግብ ጠባቂው ያዳነው ኳስ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ቢቃረብም የወላይታ ድቻው ግብ ጠባቂ ቢንያም ገነቱ አድኖታል። ወላይታ ድቻዎችም በጨዋታው ጥቂት የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም ወደ ሙከራነት የተቀየረ ንፁህ የግብ ዕድል አልነበረም።
እንደ መጀመርያው አጋማሽ የአዳማ ከተማ የኳስ ቁጥጥር ብልጫና የወላይታ ድቻ ጠጣር የመከላከል አደረጃጀት ያስመለከተን ሁለተኛው አጋማሽ በፉክክር ረገድ ከመጀመርያው አጋማሽ የተሻለ ነበር። ከተፈጠሩት ዕድሎችም በአዳማዎች በኩል አማኑኤል ከመስመር አሻግሮት ዮሴፍ ጨርፎት ደስታ የሞከረው ኳስ ቀዳሚ ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩልም ስንታየሁ ከቆመ ኳስ ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።
በስልሣ አምስተኛው ደቂቃም ዮሴፍ በጥሩ መንገድ እየገፋ ወደ ሳጥን የተጠጋውን ኳስ ከአሜ ጋር አንድ ሁለት ተቀባብሎ ወደ ግብነት በመቀየር አዳማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቡ በኋላም የወላይታ ድቻ አምበም ደጉ ደበበ በሁለት ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
ከግቡ በኋላ ሙከራ ያላስመለከተው ጨዋታው በሰማንያ አንደኛው ደቂቃ ግብ አስተናግዷል። ተቀይሮ የገባው ቢንያም ፍቅሩ አናጋው ባደግ ያሻገረለትን ኳስ ከሁለት ተጫዋቾች ጋር ታግሎ በማስቆጠር ወላይታ ድቻዎችን አቻ ማድረግ ችሏል።
ከጨዋታው መፈፀም በኋላ መጀመርያ ላይ አስተያየታቸው የሰጡት የአዳማ ከተማው አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ጨዋታውን አሸንፈው መውጣት ይገባቸው እንደነበር እና ከዚህ በላይ ግቦች አስቆጥረው አሸንፈው መውጣት የሚችሉበት ዕድል እንደነበር ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ተጋጣሚያቸው አንድ ዕድል ፈጥሮ አንድ ግብ እንዳስቆጠረባቸው ገልፀዋል።
ቀጥለው አስተያየታቸው የሰጡት የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም በበኩላቸው ፕሪምየር ሊጉ ሊጠናቀቀ በመቃረቡ እያንዳንዱ ጨዋታ በትኩረት መጫወት እንዳለባቸው ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም በመልሶ ማጥቃት ዕድሎች መፍጠራቸው ጠቅሰው ጨዋታውም ተመጣጣኝ እንደነበር ተናግረዋል። በስተመጨረሻም \”ያደረግናቸው ቅያሬዎች ውጤታማ አድርጎናል\” ብለዋል።