የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ጨዋታዎች የቦታ ለውጥ ይደረግባቸው ይሆን?

አስራ አራት ቡድኖች ይዞ በአሰላ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የከፍተኛ ሊግ የምድብ ሀ ውድድር የቦታ ለውጥ ሊደረግበት እንደሚገባ ክለቦች አሳውቀዋል።

በ2016 የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድጉ ሦስት ቡድኖችን ለመለየት ብርቱ ፉክክር የሚደረግበት የከፍተኛ ሊግ ውድድር በሦስት ምድብ ተከፍሎ በተለያዩ ከተሞች እየተካሄደ ይገኛል። እስካሁን ባለው ሁኔታ ሻሸመኔ ከተማ ከምድብ ለ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጉን ያረጋገጠ የመጀመርያው ክለብ መሆኑ ሲታወቅ የቀሩትን ሁለት ቡድኖችን ለመለየት በባቱ ከተማ እና በአሰላ ከተማ የሚካሄዱ ቀሪ ሦስት ጨዋታዎችን መጠበቅ ግድ ሆኗል።
\"\"
በአሰላ ከተማ አረንጓዴ ስታዲየም የሚካሄዱት የምድብ ሀ ጨዋታዎች ገና ከውድድሩ ጅማሮ አንስቶ ከዝናብ ጋር ተያይዞ መጫወቻ ሜዳው አመቺ ካለ መሆኑ ጋር ተደምሮ ተግዳሮት ገጥሞት መዝለቅ ችሎ ነበር። ሆኖም ከሰሞኑ በከተማው ከበድ ያለ ዝናብ እየዘነበ በመሆኑ ጨዋታዎችን ለማድረግ አዳጋች ሆኗል። በ24ኛ ሳምንት መካሄድ ከነበረባቸው ሰባት ጨዋታዎች መካከል ስድስቱ በዝናብ ምክንያት ሳይካሄዱ ቀርተዋል።

በዛሬው ዕለትም አወዳዳሪው አካል የአስራ አራት ክለቦች ተወካዮች በተገኙበት በወቅታዊ ሁኔታ ዙርያ ውይይት አድርጓል። በዕለቱም የክለቦች ተወካዩች በሜዳው አለመመቸት በሚያስመዘግቡት ውጤት አሉታዊ ተፅዕኖ እያጋጠማቸው እንደሆነ እና ነገሮች በዚህ መልኩ የሚቀጥሉ ከሆነ በቀጣይ በመውጣት እና በመውረድ በሚያደጉት ፉክክር አስቸጋሪ እንደሚሆንባቸው በአንድ ድምፅ በመግለፅ ውድድሩ አሁን ካለበት አሰላ ከተማ ወደ አዳማ ከተማ ሳይንስ እና ቴክሎኖጂ ዩኒቨርስቲ ሜዳ እንዲደረግ ደብዳቤ በመፃፍ በፊርማቸው አረጋግጠው ምክረ ሀሳብ አቅርበዋል።
\"\"
በአሰላ ከተማ የሚገኘውን ውድድር በበላይነት የሚመራው አካል የክለቦቹን አቋም መነሻ በማድረግ ለሚመለከተው የበላይ አካል በደብዳቤ ሪፖርት ማቅረቡን ሰምተናል። አሁን የሚጠበቀው የፌዴሬሽኑ በጉዳዮ ዙርያ የሚሰጠው አቅጣጫ ሲሆን የመጨረሻው ውሳኔም በቅርቡ ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።