ሪፖርት| ፍሊፕ አጄህ ለተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ ሲዳማን አሸናፊ አድርጓል

ሦስት ቀይ ካርዶች እና አስራአንድ ቢጫ ካርዶች በተመዘዙበት ጨዋታ ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድል አሳክቷል።

\"\"

09:00 ላይ በጀመረው ጨዋታ መድኖች ባለፈው ሳምንት ካሸነፈው ቋሚ አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ወደ ጨዋታ ሲገቡ ሲዳማ ቡናዎችም ሀዋሳን ካሸነፈው ስብስብ አማኑኤል እንዳለ እና ቡልቻ ሹራ በደግፌ አለሙ እና ፍሊፕ አጄህ ተክተው ጨዋታው ጀምረዋል።

የሲዳማ ቡና በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ ባሳየበት ፤ ኢትዮጵያ መድን ለወትሮ የሚታወቁበት አጨዋወት ለመተግበር የተቸገሩበት የመጀመርያው አጋማሽ በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠረበት ነበር። በፈጣን የማጥቃት አጨዋወቶች ታጅቦ የጀመረው ጨዋታው ግብ ያስተናገደው ገና በአምስተኛው ደቂቃ ነበር ፤ የግቧ መነሻም ፍሊፕ አጃህ ወደ መሀል ክፍል ተጠግተው ለመከላከል የሞከሩት የመድን ተካላካዮች ከኋላ የፈጠሩት ክፍተት ተጠቅሞ በማምለጥ ከግብ ጠባቂው አንድ ለአንድ ተገናኝቶ ግብ አስቆጥሯል። 

ፍሬው ሰለሞን በሂደቱ ላይ የመጨረሻ በማቀበል ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በአጋማሹ የተሻለ ብልጫ የነበራቸው ሲዳማዎች ከግቡ በኋላም በይገዙ አማካኝነት ከቅጣት ምት ሙከራ ቢያደርጉም ግብ ጠብቂው አድኖባቸዋል።

እስከ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ድረስ የተጋጣሚን ጫና ተቋቁመው ለመጫወት እና የግብ ዕድሎች መፍጠር የተቸገሩት መድኖች በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች ግብ ለማግኘት ተቃርበው ነበር ፤ በተለይ ባሲሩ አሻምቶት በግቡ ቅርብ ርቀት የነበረው ሀቢብ ያልተጠቀመበት ኳስ ቡድኑን አቻ ለማድረግ ተቃርቦ ነበር።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሲዳማ ቡናዎች ብልጫ የወሰዱበት ሁለተኛው አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የአቀራረብ ለውጥ ሳያደርጉ ነበር የተመለሱት።

እንዳለ ከበደ በተሰለፈበት የቀኝ መስመር ለማጥቃት ጥረት ይደርጉት ሲዳማዎች በሁለት አጋጣሚዎች በይገዙ ቦጋለ አማካኝነት ሙከራ አድርገዋል። በተለይም አጥቂው አጃህ ከቀኝ መስመር አሻምቶለት ወደ ግብነት ያልቀየረው ሙከራ ለግብ የቀረበ ነበር። ተቀይሮ የገባው አቤኔዜር በውሳኔ አሰጣጥ ስህተት ያመከነው ኳስም ሌላ የሚጠቀስ ዕድል ነበር።

በሀምሳ አምስተኛው ደቂቃ የሲዳማ ዋና አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥተዋል። ከደቂቃዎች በኋላም ተቀይሮ የገባው ኪቲካ ጅማ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ተሰናብቷል።

ከካርዶቹ በኋላ መድኖች በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲሞክሩ ሲዳማዎች በበኩላቸው ውጤቱን አስጠብቀው ለመውጣት በቁጥር በዝተው የተከላከሉበት ነበር። ከጨዋታው መጠናቀቅ አስቀድሞም ሁለቱም ቡድኖች ያለቀላቸው ሙከራዎች አድርገዋል። ሲዳማዎች የመድን ተከላካይ ስህተት ተጠቅመው በአጃህ አማካኝነት የፈጠሩት ግልፅ የማግባት ዕድል እና መድኖች በያሬድ ዳርዛ የግል ጥረት የሞከሩት ሙከራዎቹም የጨዋታው የመጨረሻ እንቅስቃሴዎች ነበሩ። በመጨረሻ ደቂቃዎች የቀይ ካርዱ ዕጣ ለሲዳማ ቡናም ደርሶ ሙሉቀን አዲሱ በሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከሜዳ እንዲወጣ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ገብረመድህን በጨዋታው ጅማሬ ግብ ማስተናገዳቸው ጫና ውስጥ እንደከተታቸው ከገለፁ በኋላ \”አስራ አራት ለአስር አንድ ነው የተጫወትነው ፤ ውጫዊ ጫና በዝቶብናል በማለት በዳኝነት ላይ ያላቸው ቅሬታ አሰተዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ቡድናችን ጥሩ ነው ያንን ሁሉ ጫና ተቋቁመው ለማሸነፍ ያደረጉት ጥረት ጥሩ ነበር ብለዋል።

\"\"

አሰልጣኝ ሥዩም በበኩላቸው አጀመራችን ጥሩ ነበር ፤ ከነበረብን ጫና አኳያ ውጤቱ ማግኘታችን ጥሩ ነው ካሉ በኋላ በተከታታይ ያገኘዋቸው ውጤቶች ወሳኝ እንደሆኑ ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም \”በዳኝነት ላይ የታየኝ ችግር ነገር የለም\” ብለዋል።