ሪፖርት | 57 ጥፋቶች በተሰሩበት ጨዋታ ሀዋሳ እና ሀዲያ ነጥብ ተጋርተዋል

ሳቢ ያልነበረው የሀዋሳ ከተማ እና ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ ያነሱ ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራዎች ተደርገውበት 0ለ0 ተጠናቋል።

ባሳለፍነው ሳምንት በመቀመጫ ከተማው ተጫውቶ በሲዳማ ቡና አንድ ለምንም የተረታው ሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ ካጣበት ፍልሚያ አንድ ተጫዋቾ ብቻ ለውጧል። በዚህም ዳዊት ታደሠን ተክቶ ፀጋአብ ዮሐንስ ወደ ሜዳ ገብቷል። በተመሳሳይ የጨዋታ ሳምንት በፋሲል ከነማ የተሸነፈው ሀዲያ ሆሳዕና በበኩሉ ዳግም ንጉሴ፣ ግርማ በቀለ እና ባዬ ገዛኸኝን በስቴፈን ንያርኮ፣ ሪችሞንድ አዶንጎ እንዲሁም ፀጋዬ ብርሃኑ ተክቶ ጨዋታውን ቀርቧል።

\"\"

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እምብዛም ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራዎች ባይደረጉበትም በየቦታው የነበረው ፍልሚያ እና ፍትጊያ የጨዋታው የሀይል ሚዛን ወደ አንዱ ቡድን እንዳያደላ አድርጓል። 10ኛው ደቂቃ ላይ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ፈጣን የቀኝ መስመር ማጥቃት ሰንዝረው የመጀመሪያውን ጥቃት አስመልክተውናል። በዚህም ተመስገን ብርሃኑ ከብርሃኑ በቀለ የተቀበለውን ኳስ በጠባቡ አንግል መትቶት ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ መልሶታል። ፈጣን አጥቂዎች ያሏቸው ሀዋሳ ከተማዎች በበኩላቸው ከተከላካይ ጀርባ ኳሶችን እየላኩ የግብ ምንጭ ለማግኘት መጣርን መርጠዋል።


ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እያስመለከተ የሚገኘው ጨዋታው በአንፃራዊነት የኳስ ቁጥጥር ብልጫው ወደ ሀዲያ ሆሳዕና አምርቷል። ቡድኑ በእርጋታ ኳሶችን እየተቀባበለ በተለይ በመስመር ላይ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ቢጥርም የሰላ ዕድል አላገኘም። ሀዋሳም ሽግግሮችን እና ረጃጅም ኳሶችን ለመጠቀም ቢጥርም በአጋማሹ አንድ ብቻ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ አድርጎ ወጥቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃም አብዱልባሲጥ ከማል ከጥሩ ቦታ ግልፅ ዕድል አግኝቶ በወረደ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

እንደ ዐየር ሁኔታው ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ እያስተዋልንበት በሚገኘው ጨዋታ የሁለተኛው አጋማሽ በመጠነኛ ዝናብ ታጅቦ መከናወን ይዟል። ሀዋሳ ከተማዎች በሁለተኛው አጋምሽ ጅማሮ የተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ የተጫዋች ሽግሽግ አድርገው በጨዋታው የተሻለ ለመንቀሳቀስ ቢወጥኑም ብዙም እድገት ማሳየት አልቻሉም። የአጋማሹም በአንፃራዊነት ለግብ የቀረበ የመጀመሪያ ሙከራ በ71ኛው ደቂቃ ዳንኤል ደርቤን ተክቶ በገባው ዳዊት ታደሠ አማካኝነት ሰንዝረዋል።


ጨዋታው ሊገባደድ ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩት የኳስ ቁጥጥር ብልጫቸውን በግብ ማሳጀብ ያልቻሉት ሀዲያዎች ተመስገን ብርሃኑ የሀዋሳ ተከላካይ በረከት ያመለጠውን ኳስ አግኝቶ ጥብቅ ኳስ መትቶ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ቢሞክርም ሙንታሪ መልሶበታል። ጨዋታው ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ ሀዲያ በሰመረ አማካኝነት ሌላ እጅግ ወርቃማ ዕድል አግኝተው የነበረ ቢሆንም ኳስ እና መረብን ማገናኘት አልቻሉም። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ የሀዲያ ሆሳዕናው አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ ከባለፈው ጨዋታ ዛሬ የተሻሉ እንደነበረ ቢገልፁም በማጥቃቱ ረገድ ግን ጥሩ እንዳልነበር በመግለፅ ጎል ስላላስቆጠሩ አንዱ ነጥብ እንደሚገባቸው ተናግረዋል። የሀዋሳ ከተማው አሠልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ በበኩላቸው የተቃራኒ ቡድን አጨዋወት ከእቅዳቸው ውጪ እንዲጫወቱ እንዳደረጋቸውና እንዳስቸገራቸው በማንሳት በተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ባያስቆጥሩም የቡድኑ ችግር የአማካይ መስመሩ እንደሆነ አስረድተዋል።

\"\"