መረጃዎች | 95ኛ የጨዋታ ቀን

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት ማገባደጃ የሆኑ ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰናድተናል።

መቻል ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቀን 9 ሰዓት ላይ 29 ነጥቦችን በመያዝ 11ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን መቻሎች በ 51 ነጥቦች የሊጉ መሪ ከሆኑት ፈረሰኞቹ የሚያገናኘው ጨዋታ ሲደረግ መቻሎች ከወራጅ ቀጠናው በአስተማማኝ ሁኔታ ለመራቅ ጊዮርጊሶች ደግሞ ከተከታያቸው ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ከፍ ለማድረግ ብርቱ ፉክክር ያደርጉበታል ተብሎ ይጠበቃል።

የአዳማ ከተማ ቆይታቸውን ድሬዳዋ ከተማን 2ለ1 በመርታት ያጠናቀቁት መቻሎች አሰልጣኙ ከጨዋታው በኋላ እንደሰጡት አስተያየት ተጫዋቾቹ ውጤት በሚያጡበት አጋጣሚ የሚገቡበት የድብርት ስሜት በራስ መተማመናቸውን በማውረዱ ረገድ ከፍተኛ ጫና እያሳደረባቸው መሆኑ በግልጽ የሚታይ ቢሆንም ያላቸው የተጫዋች ስብስብ አሁንም ወደ ውጤት ለመመለስ የሚያስችል አቅም ያለው ነው። ሆኖም ካለፉት 10 ጨዋታዎች በ 9ኙ ግባቸው የተደፈረባቸው መቻሎች ድሎችን ለማሳካት የኋላ መስመራቸውን ማስተካከል እና የሚፈጥሯቸውን የግብ ዕድሎች ወደ ግብ መቀየር መቻል ይጠብቅባቸዋል። የመቻሉ ወጣት አማካይ በኃይሉ ኃይለማርያም ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ያሳየው ድንቅ ብቃት በነገው ዕለትም የሚጠበቅ ሲሆን በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ የሚሆናቸውን ተከታታይ ድል ለማስመዝገብም ከፈረሰኞቹ ፈታኝ እንቅስቃሴ ይጠብቃቸዋል ተብሎ ይገመታል።

\"\"

ካለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ስምንቱን የረቱት ጊዮርጊሶች ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ በፊት እና በኋላ ዕኩል አራት አራት ድሎችን ሲያሳኩ በውድድር ዓመቱ ተከታታይ አምስት ድል ካሳካው ብቸኛው ቡድን ባህርዳር ከተማ ጋር ሪከርድ ለመጋራት የነገው ድል ያስፈልጋቸዋል። ይቸገራሉ ተብለው በሚጠበቁበት ጨዋታ ሁሉ ድል ከማድረግ የሚያቆማቸው ያላገኙት ፈረሰኞቹ ካስቆጠሯቸው 43 ግቦች 21(48.83%) የሚሆኑትን ያስቆጠረው እስማኤል ኦሮ አጎሮ ባለበት ወቅታዊ ድንቅ ብቃት ታግዘው ወደ ዋንጫ የሚያደርጉትን ግስጋሴ አጠናክረው ሲቀጥሉ ከተከታያቸው ባህርዳር ያላቸውን የነጠብ ልዩነት ወደ ሰባት ለማሳደግም በነገው ዕለት ከመቻል የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል አይሆንም።

በመቻል በኩል በጉዳት ከሜዳ ከራቁት ፍጹም ዓለሙ እና ዳግም ተፈራ በተጨማሪ ዳዊት ማሞም በቅጣት ጨዋታው የሚያልፈው ይሆናል።

ሁለት ቡድኖች ከዚህ በፊት ለ32 ጊዜያት ተገናኝተው 18 ጊዜ ነጥብ በመጋራት ሲለያዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአሥራ ሁለት መቻል ደግሞ ለሁለት ጊዜያት ማሸነፍ ችለዋል።

ወልቂጤ ከተማ ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

ምሽት 12 ሰዓት ላይ የሳምንቱ የመጨረሻ መርሐግብር 25 ነጥቦችን ይዘው 13ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡትን ወልቂጤ ከተማዎች በ 11 ነጥቦች የሊጉ ግርጌ ላይ ከተቀመጡት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ሲያገናኝ ሠራተኞቹ በአንድ ነጥብ ብቻ ከራቁበት የወራጅ ቀጠና ለመሸሽ ለገጣፎዎች ደግሞ በሊጉ ለመቆየት ያላቸውን ተስፋ ለማለምለም ጥሩ ፉክክር እንደሚያደርጉበት ይጠበቃል።

በሊጉ አምስተኛውን ከፍተኛ የግብ መጠን (32) ያስተናገዱት ሠራተኞቹ ባለፉት አራት ጨዋታዎች 7 ግቦችን ማስቆጠራቸው በእንቅስቃሴ ደረጃ ከሳምንታት በፊት ከነበራቸው አቋም እየተሻሻሉ መሆኑን ቢጠቁምም በአንጻሩ በነዚሁ ጨዋታዎች ላይ ደካማ በሆነው የመከላከል ሽግግራቸው 8 ግቦችን ማስተናገዳቸው ማግኘት ከሚገባቸው 12 ነጥብ 4 ነጥብ ብቻ እንዲያሳኩ ምክንያት ሆኖባቸዋል። በውድድር ዓመቱ ካስቆጠሯቸው 27 ግቦች 15 (55.55%) የሚሆኑትን በስሙ ያስመዘገበው ጌታነህ ከበደ ሳጥን ውስጥ ምህረት የለሽ ከመሆኑ በላይ 5 ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻትቶ ማቀበልም መቻሉ በቡድኑ ጎሎች ላይ ያለውን ተሳትፎ 74% ያደርሰዋል። ይህም ቡድኑ በአንድ ተጫዋች ትከሻ ላይ እንዳለ በመጠኑ ቢጠቁምም አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ እንዳሉት እግርኳስ የቡድን ሥራ ከመሆኑ አንጻር ረፍት የለሽ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት የቡድን አጋሮቹ በውጤት ደረጃ ቁጥሮች ባይደግፏቸውም በእንቅስቃሴ ደረጃ ያላቸው ተሳትፎ ግን ትልቅ ነው። በነገው ዕለትም ከወራጅ ቀጠናው በመጠኑ ለመራቅ የሚያስፈልጋቸውን ወሳኝ ድል ለማሳካት ከለገጣፎ ለገዳዲ የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል አይሆንም።

\"\"

ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ግብ ብቻ አስቆጥረው ሁለት የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገቡት ለገዳዲዎች ከወራጅ ቀጠናው ከፍ ብሎ ከሚገኘው ከነገው ተጋጣሚያቸው ወልቂጤ ከተማ በ 14 ነጥቦች ዝቅ ብለው መቀመጣቸው ወድድሩ ሊያልቅ የ ስምንት ጨዋታዎች ዕድሜ ከመቅረቱ አንጻር ለመትረፍ ያላቸውን ተስፋ እጅግ ያመነመነ ነው። ሆኖም በእንቅስቃሴ ደረጃ የማይታማው ቡድኑ በተለይም በአዲሱ አሰልጣኝ ሥር መነቃቃት ቢያሳይም በድጋሚ የውጤት ማጣት ቀውስ ውስጥ ተዘፍቋል። ቡድኑ በቀጣይ ከፋሲል ከነማ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር በተከታታይ ለሚያደርገው ፈታኝ ግጥሚያም በነገው ዕለት የሚያሳካው ውጤት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

በወልቂጤ ከተማ በኩል አፈወርቅ ኃይሉ እና አንዋር ዱላ በጉዳት ጨዋታው የሚያመልጣቸው ሲሆን ባለፈው ሳምንት  በህመም ምክንያት ቡድኑን ያልመሩት አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ከትናንት በስቲያ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ልምምድ እንዳሠሩ እና በነገው ዕለትም ቡድናቸውን እንደሚመሩ ታውቋል። በለገጣፎ ለገዳዲ በኩል ደግሞ ግብ ጠባቂው ኮፊ ሜንሳህ በቅጣት ጨዋታው የሚያልፈው ሲሆን የሱለማይን ትራኦሬ መሰለፍ አጠራጣሪ ነው።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የመጀመሪያ ግንኙነታቸው ወልቂጤ ከተማ 3-0 መርታቱ የሚታወስ ነው።