ሪፖርት | መቻል ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጣፋጭ ድል ተጎናጽፏል

መቻሎች በከነዓን ማርክነህ ብቸኛ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ ፈረሰኞቹን 1-0 መርታት ችለዋል።

9 ሰዓት ላይ የመቻል እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ሲደረግ መቻሎች በ 22ኛው ሳምንት ድሬዳዋ ከተማን 2ለ1 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በቅጣት ከጨዋታው ውጪ የሆነውን ዳዊት ማሞን እና ግርማ ዲሳሳን በአህመድ ረሺድ እና ግሩም ሃጎስ ሲተኩ ፈረሰኞቹ በበኩላቸው በተመሳሳይ ሳምንት ወልቂጤ ከተማን 2ለ1 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ግብ ጠባቂ ቻርልስ ሉክዋጎን አስወጥተው ባህሩ ነጋሽን ተክተው ቀርበዋል።

\"\"

ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ፈረሰኞቹ ብልጫ ቢወስዱም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ሁለቱም ደካማ ሆነው የታዩበት ነበር። ጊዮርጊሶች ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በርካታ ስኬታማ ቅብብል በማድረግ እና ዝግ ባለ የማጥቃት ሂደት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ውስጥ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ወደ ራሳቸው የሜዳ ከፍል ተጠግተው በሚያገኙት ኳስ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ የሞከሩት መቻሎችም በተመሳሳይ ተጠቃሽ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጨዋታው 40ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ ሲደረግበት የጊዮርጊሱ ዳዊት ተፈራ ከቅጣት ምት ያደረገው ሙከራ በግቡ አግዳሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ደግሞ የመቻሉ ሳሙኤል ሳሊሶ በግራ መስመር ከሳጥን አጠገብ በተገኘ የቅጣት ምት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ሲመልስበት ይህም በአጋማሹ ብቸኛው ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ከዕረፍስ መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተጋግሎ ሲቀጥል በአጋማሹ ተሻሽለው የቀረቡት መቻሎች በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በግራው የማጥቂያ መስመራቸው ተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ 51ኛው ደቂቃ ላይም ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉበት ንፁህ ዕድል ፈጥረው ነበር። እስራኤል እሸቱ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ጥቂት ዘግይቶ ወደ ውስጥ በመቀነስ ለ በኃይሉ ኃይለማርያም አመቻችቶ ሲያቀብል በኃይሉም ሄኖክ አዱኛ ያሳረፈበት ጫና ተጨምሮበት ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ በግቡ አግዳሚ በኩል ወጥቷል።

ጨዋታው 62ኛ ደቂቃ ላይ ሲደርስ መቻሎች ግብ አስቆጥረው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከነዓን ማርክነህ በግራው የሳጥኑ ከፍል ኳሱን እየገፋ በሚገባበት አጋጣሚ የመስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ ጥፋት ሠርቶበት ዋና ዳኛው ኢንተርናሽናል ዳኛ ዶክተር ኃይለየሱስ ባዘዘው የፍጹም ቅጣት ምት ሰጥተዋል። ፍጹም ቅጣት ምቱን የመታው ከነዓን ማርክነህም ኳሱ የግብ ጠባቂውን ባህሩ ነጋሽ እጅ ጥሶ መረቡ ላይ እንዲያርፍ አድርጎታል።


ፈረሰኞቹ ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በመነቃቃት የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ለማድረግ እስከ 90ኛው ደቂቃ መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ሄኖክ አዱኛ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው ተከላካዩ አማኑኤል ተርፉ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብ ጠባቂው ውብሸት ጭላሎ በቀላሉ ሲይዘው በሴኮንዶች ልዩነት ግን መቻሎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እጅግ ተቃርበው ነበር። በረከት ደስታ ሄኖክ አዱኛን አታልሎ በማለፍ በግራው የሳጥኑ ጠርዝ ይዞት የገባውን ኳስ ለምንይሉ ወንድሙ አመቻችቶ ሲያቀብል ምንይሉም ባልተረጋጋ አጨራረስ የግብ ዕድሉን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ሆኖም የጊዮርጊሱ ቸርነት ጉግሣ 94ኛው ደቂቃ ላይ የመቻል ተከላካዮች በሠሩት ስህተት ያገኘውን ኳስ ከማቀበል አማራጭ ጋር ወደ ግብ ሞክሮት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ዒላማውን ሳይጠብቅ ወጥቷል። ጨዋታውም በመቻል 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ጨዋታው ግለቱ የቀዘቀዘ እንደነበር እና በማጥቃት ሂደታቸው ላይ መቸገራቸውን ሲገልጹ \”ራሳችን በሠራነው ስህተት ተሸንፈናል። ሳጥን ውስጥ ስንደርስ ስኬታማ የሆነ እንቅስቃሴ አናደርግም ነበር።\” ብለዋል። አሰልጣኙ አክለውም ከፊት ያሉት ጨዋታዎች ላይ የተሻለ እንደሚሠሩ ተናግረዋል። የመቻሉ አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በበኩላቸው \”የምንፈልገውን ስላገኘን በቅድሚያ እግዚአብሔርን አመሠግናለሁ።\” ካሉ በኋላ \”በተቻለ መጠን የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን መቆጣጠር ችለን ያገኘነውን ግብ አግብተናል። በተለይ ከዕረፍት መልስ በነሱ የቀኝ መስመር ያገኘነውን ክፍተት ተጠቅመን ጠንካራውን ቡድን ማሸነፋችን ትልቅ የስነልቦና ጥንካሬ ይሰጠናል ብለን እናስባለን። ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስቱን መርታታችን ትልቅ ስኬት ነው። ትልቅ ቡድን እንደማሸነፋችን አያኩራራንም እንጂ ያጠነክረናል።\” ብለው የገለጹት አሰልጣኙ የከነዓን ማርክነህን ብቃት አድንቀው የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ እና ግብ በማስቆጠሩ በኩል ከዚህ የተሻለ እንደሚጠብቁበት ጠቁመዋል።