ጌታነህ ከበደ ደምቆ ባመሸበት ጨዋታ ወልቂጤዎች ከሁለት ለባዶ መመራት ተነስተው ለገጣፎን አሸንፈዋል።
ወልቂጤዎች ባለፈው ሳምንት ሽንፈት ከገጠመው ቋሚ 11 ፍፁም ግርማን ብቻ በአዲስዓለም ተስፋዬ ተክተው ሲጀምሩ ፤ ለገጣፎዎች በተመሳሳይ ሽንፈት ከገጠመው ስብስብ ሚክያስ ዶጂ ፣ ያሬድ ሀሰን ፣ ኤልያስ አታሮ ፣ ጋብሬል አሕመድ እና ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስን በበሽር ደሊል ፣ አስናቀ ተስፋዬ ፣ በረከት ተሰማ ፣ ተፈራ አንለይ እና ሱራፌል ዐወል ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።
ሁለት መልክ በነበረው የመጀመርያው አጋማሽ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ወልቂጤዎች የበላይ ሆነው ቢጀምሩም የኋላ ኋላ ግን በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሞከሩት ለገጣፎዎች የተሻለ የተንቀሳቀሱበት ነበር። በአስራ ስድስተኛው ደቂቃም ለገጣፎዎች ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶ ግብ አስቆጥረዋል። መሐመድ በራሱ ጥረት ይዞት ገብቶ ለሱራፌል ያቀበለው ኳስ አማካዩ አሻምቶት ኢብሳ በፍቃዱ በመቀስ ምት ከመታው በኋላ ቋሚውን ገጭቶ ግብ ጠባቂው በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሮታል።
ከመጀመርያው ግብ በኋላም መሐመድ በተሰለፈበት ቦታ በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሞከሩት ለገጣፎዎች በአማኑኤል አረቦ አማካኝነት ተጨማሪ ግብ አስቆጥረው መሪነታቸው ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል። አጥቂው በሳጥኑ ግራ ጠርዝ አካባቢ ሆኖ ከኢብሳ በግሩም መንገድ የተቀበለውን ኳስ ገፍቶ በማስቆጠር ነበር ቡድኑን ያረጋጋች ኳስ ከመረብ ያገናኘው።
ጥሩ አጀማመር ካደረጉ በኋላ የበላይነታቸው ማስጠበቅ ተስኗቸው ሁለት ግቦች ያስተናገዱት ወልቂጤዎች በአቤል አማካኝነት ወርቃማ ዕድል አምክነዋል። ተጫዋቹ ተመስገን በረጅሙ ያሻገረለትን ኳስ ከግቡ ቅርብ ርቀት ሆኖ ነበር የአጋማሹ ትልቁ ሙከራ ወደ ግብነት ያልቀየረው። አዲስአለም ከመአዝን የተሻማው ኳስ ፤ አስራት ደግሞ ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ ተጠቅመው በተመሳሳይ በግንባር ገጭተው ያደረጓቸው ሙከራዎችም ሌላ የሚጠቀሱ ሙከራዎች ናቸው።
በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃም የለገጣፎው ተጫዋች ታምራት አየለ በገጠመው ከበድ ያለ ጉዳት ተቀይሮ ወጥቷል።
ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ በኋላ በጥሩ ተነሳሽነት ጨዋታውን የጀመሩት ወልቂጤዎች በሀምሳ ሁለተኛው ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል። ብዙአየሁ ከሳጥን ውጭ ሆኖ መቶት ግብጠባቂው የተፋው ኳስ ጌታነህ አግኝቶ ወደ ሳጥን ካሻገረው በኋላ በግቡ ፊትለፊት የነበረው አስራት መገርሳ ወደ ግብነት ቀይሮ የግብ ልዩነቱን አጥቧል። ከግቡ በኋላም አቤል ነጋሽ በረዥሙ የተላከለትን ኳስ በጥሩ መንገድ አብርዶ መቶት የግቡ አግዳሚ ጨርፎ የወጣው ሙከራ እጅግ ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።
ከአጋማሹ ጅማሬ ጀምሮ ጫና ፈጥረው መጫወታቸው የቀጠሉት ወልቂጤዎች በጌታነህ አማካኝነት ከቅጣት ምት ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ከመአዘን ምት ከተሻማ ኳስ የኋላሸት በግንባር አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ጌታነህ ከበደም በጨዋታው ሁለተኛ ኳሱን ለግብ አመቻችቶ አቀብሏል።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች በርካታ ለግብ የቀረበ ሙከራዎች የታየበት ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተፈጥረዋል። በለገጣፎ በኩል መሐመድ ያሻማው ቅጣት ኢብሳ አመቻችቶት ካርሎስ ዕድሉን ሳይጠቀምበት የቀረው እጅግ አስቆጪ ሙከራ ፤ በወልቂጤ በኩልም በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ያደረገው አቤል ነጋሽ በሁለት አጋጣሚዎች ያደረጋቸው እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ይጠቀሳሉ።
በጨዋታው አስራ ሁለት የመዐዝን ምቶች ጨምሮ በርካታ የቆሙ ኳሶች ያገኙት ወልቂጤዎች በመጨረሻው ደቂቃ የአሸናፊነት ግብ አስቆጥረው መሪነቱን ጨብጠዋል። ጌታነህ ከበደ ከመአዝን ያሻማው ኳስ ኤፍሬም ዘካርያስ በግንባሩ ከጨረፈው በኋላ አዲስአለም ወደ ግብነት ቀይሮታል። የጨዋታው መጠናቀቅያ ፊሽካ ከተነፋ በኋላም ሱራፌል ዐወል ቀይ ካርድ ተመልክቷል።
ከጨዋታው በኋላ አሰልጣኝ ዘማርያም በፈለግነው መሰረት ተጫውተን ብልጫ ወስደን ግብም ማስቆጠር ችለናል ካሉ በኋላ በሁለተኛው አጋማሽ ያሳዩት እንቅስቃሴ እንዳላረካቸው ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም ተጫዋቾቻቸው ለማሸነፍ ያሳዩት ተነሳሽነት ካደነቁ በኋላ የዕለቱ ዳኛ ተደጋጋሚ ጊዜ የቡድናቸውን ጨዋታ እንዲዳኝ መደረጉ አግባብ እንዳልሆነ እና ጥያቄም እንዳላቸው ገልፀዋል።
አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በበኩላቸው የተቆጠሩባቸው ግቦች በራሳቸው ስህተት እንደነበሩ ገልፀው በሁለተኛው አጋማሽ ስህተቱን በማረማቸው ውጤቱን እንዲያገኙ እንዳገዛቸው ገልፀዋል። አሰልጣኙ ጨምረውም \”ይሄ የመጀመርያችን ነው። ተጫዋቾቼ በየጊዜው የተሻለ ነገር ነው የሚያደርጉት ፤ የሚከፍሉት ነገር ከፍተኛ ነው። በተጫዋቾቼ ኮርቻለው\” ብለዋል።