ሪፖርት | አዞዎቹ እና የጦና ንቦቹን ያገናኘው ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ደካማ እንቅስቃሴ እና ጥቂት የግብ ሙከራዎች የታየበት የአርባምንጭ ከተማ እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ ያለ ግብ ተፈፅሟል።

አዞዎቹ ባለፈው ሳምንት ከፋሲል ከነማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ወርቅይታደስ አበበ ፣ አበበ ጥላሁን እና ኤሪክ ካፓይቶን በአካሉ አትሞ ፣ ቡታቃ ሸመና እና አህመድ ሁሴን ለውጠው ጨዋታውን ጀምረዋል። የጦና ንቦች በበኩላቸው ከአዳማ ከተማ ጋር አቻ ከተለያየው ስብስብ ደጉ ደበበ እና ስንታየሁ መንግሥቱን በያሬድ ዳዊት እና ቢንያም ፍቅሩ ተክተው ጨዋታውን ጀምረዋል።

\"\"

ጠጣር እና በረዣዥም ኳሶች ለማጥቃት የሚሞክሩ ወላይታ ድቻ እና በተሻለ መንገድ ኳስ ለመቆጣጠር ጥረት ያደረገው አርባምንጭ ከነማ ያገናኘው ጨዋታ በቂ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። በመጀመርያው አጋማሽ አዞዎቹ በአንፃራዊነት የተሻለ ቢንቀሳቀሱም ጠንካራው የወላይታ ድቻ የመከላከል አደረጃጀት አልፈው የግብ ዕድል መፍጠር ግን አልተቻላቸውም። ሆኖም በአንድ አጋጣሚ ወደ ሙከራነት ያልተቀየረ ጥሩ የግብ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። ሙከራውም ሱራፌል ከመስመር አሻምቶት መልካሙ ቦጋለ በግንባር ያወጣው ኳስ ነበር።

በመጀመርያው አጋማሽ የተጋጣሚን የማጥቃት አጨዋወት ከማክሸፍ ውጪ በማጥቃቱ ላይ እምብዛም ያልነበሩት ወላይታ ድቻዎች በአንድ አጋጣሚ የአጋማሹ የተሻለው የጠራ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር። ያሬድ ከሳጥኑ ግራ ጠርዝ አከባቢ የተገኘው ቅጣት ምት አሻምቶት በግቡ ፊት የነበረው ቢንያም ያልተጠቀመበት ዕድል በወላይታ ድቻ በኩል ከተፈጠሩት ዕድሎ የተሻለ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ስንታየው መንግሥቱን ቀይረው በማስገባት በማጥቃቱ ላይ ጥሩ መነቃቃት ያሳዩት ወላይታ ድቻዎች የበላይነታቸውን ማስጠበቅ የቻሉት ግን ለጥቂት ደቂቃዎች ነበር። በጠንካራ ሙከራ ረገድም ሀብታሙ ከርቀት አክርሮ መቷት ወደ ውጭ ከወጣችው ሙከራ ውጭ ይህ ነው የሚባል ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

እንደ መጀመርያው አጋማሽ ባይሆንም ብልጫ የነበራቸው አዞዎቹም በእንዳልካቸው እና በአሸናፊ አማካኝነት ሙከራዎች ማድረግ ችለዋል። በተለይም አምበሉ ከርቀት ያደረጋት ሙከራ ዒላማዋን የጠበቀች ነበረች። በመጨረሻው ደቂቃ አሸናፊ በረዥም የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራም በጥሩነቱ የሚጠቀስ ነበር። የጎል ዕድሎች ያልተፈጠረበት ፤ ሙከራ ያልተደረገበት፤ በእንቅስቃሴ ደረጃም ደካማ የነበረው ጨዋታ ግን በአቻ ውጤት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ጠንካራ ከመሆናቸው አንፃር ቡድናቸው ተስፋ እንዳለው ያብራሩ ሲሆን ጎል ሳይቆጠርባቸው መውጣታቸውን በበጎው እንደሚያዩት እና የሚያገኙትን ዕድል መጨረስ ላይ ግን መሻሻል እንዳለባቸው ተናግረዋል። አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም በበኩላቸው ጥንቃቄ መርጠው መጫወታቸው እንዳዋጣቸው አንስተው ከተጋጣሚያቸው ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ታሳቢ አድርገው ጨዋታዎችን እንደሚቀርቡ አንስተው ፊት መስመር ላይ ልምድ ያላቸው አጥቂዎችን ለመጠቀም መሞከራቸውን ተናግረዋል።

\"\"