ሪፖርት | ነብሮቹ እና ሠራተኞቹ ነጥብ ተጋርተዋል

ከ75 ደቂቃዎች በላይ በጎዶሎ ተጫዋቾች የተጫወቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ከወልቂጤ ከተማ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይተዋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ የተለያየው ሀዲያ ሆሳዕና ከጨዋታው አራት ተጫዋቾችን ለውጧል። በለውጦቹም በብሩክ ማርቆስ፣ ስቴፈን ንያርኮ፣ ፀጋዬ ብርሃኑ እና ሪችሞንድ አዶንጎ ምትክ እያሱ ታምሩ፣ ግርማ በቀለ፣ መለሰ ሚሻሞ እና ዘካሪያስ ፍቅሬ ጨዋታውን እንዲጀምሩ ተደርጓል። ከመመራት ተነስተው ለገጣፎ ለገዳዲን 3ለ2 የረቱን ወልቂጤ ከተማዎችም በተመሳሳይ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ውሀብ አዳምስ፣ ተስፋዬ መላኩ፣ ተመስገን በጅሮንድ እና አቡበከር ሳኒን በፍፁም ግርማ፣ ቴዎድሮው ሀሙ፣ ኤፍሬም ዘካሪያስ እና የኋላሸት ሰለሞን ተተክተዋል።

\"\"

ጨዋታው ገና እንደተጀመረ የመዓዘን ምትን መነሻ ባደረገ አጋጣሚ የመጀመሪያ ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በአንፃራዊነት በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻለ ነበሩ። በተለይ ደግሞ ፈጣን ሽግግሮችን እያደረጉ ቀዳሚ ለመሆን ሲጥሩ ተስተውሏል። ከኳስ ጋር ጊዜ በማሳለፍ በእርጋታ ጨዋታውን ለመከወን ያሰቡት ወልቂጤ ከተማዎች በበኩላቸው በጨዋታው ሩብ ሰዓት የተጫዋች የቁጥር ብልጫ የሚያገኙበትን ዕድል ተፈጥሯል። በዚህም ፍሬዘር ካሣ የኋላሸት ሰለሞን ላይ በሰራው ጥፋት በዕለቱ ዳኛ ቢኒያም የቀይ ካርድ አይቷል።


እስካሁን የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ወልቂጤዎች በ30ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት ሙከራ ሰንዝረው ተመልሰዋል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በተመሳሳይ የቆመ ኳስ ሀዲያዎች በግርማ በቀለ አማካኝነት አፀፋዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ሀዲያዎች በጎዶሎ ተጫዋች ቢጫወቱም በ38ኛው ደቂቃ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በዚህም ግርማ በቀለ በቀላሉ ወደ ግብ የላከውን ኳስ የግብ ዘቡ ጀማል ጣሰው በሚገባ መቆጣጠር ሳይችል ቀርቶ ግብ ለማግኘት ተቃርበው የነበረ ቢሆንም ቴዎድሮስ ሀሙ ደርሶ የአጋሩን ስህተት አርሞታል። ቀዝቃዛ የነበረው አጋማሹም ያለ ግብ አቻ ተጠናቋል።

ገና በጊዜ የተጋጣሚ ተጫዋች በቀይ ካርድ ወጥቶላቸው የቁጥር ብልጫ ያገኙት ወልቂጤዎች እንደሚታሰበው ብልጫውን ተጠቅመው ጫና መፍጠር አልቻሉም። ሀዲያ ሆሳዕናዎችን ወሳኙን ተጫዋቻቸው ቢያጡም በጥሩ ሁኔታ ጨዋታውን ተቆጣጥረው ብልጫው አደጋ እንዳይፈጥርባቸው ጥረዋል።


ጨዋታው 70ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ የጨዋታው እጅግ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ተስተናግደውበታል። በዚህም በግራ መስመር ወደ ሀዲያ የግብ ክልል ያመሩት ወልቂጤዎች በጌታነህ ከበደ እና በአቤል ነጋሽ አማካኝነት ተከታታይ ሙከራ አድርገው ቢያንኳኩም የግብ ዘቡ ፔፔ ሰይዶ በሚገርም ቅልጥፍና ሁለቱንም ዕድሎች አምክኖባቸዋል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ የኋላሸት ከተከላካይ ጀርባ የደረሰውን ሌላ ወርቃማ ዕድል እጅግ በወረደ አጨራረስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በቀሪ ደቂቃዎች ተጨማሪ ዕድሎች ሳይፈጠሩ ፍልሚያው ያለጎል አቻ ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ የወልቂጤ ከተማው አሠልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በጨዋታው የቁጥር ብልጫ ቢያገኙም ተጫዋቾቻቸው ይቻኮሉ እንደነበር በመግለፅ ጨዋታውን ማሸነፍ እንደሚገባቸው አንስተው ክፍተቶችን በቀጣይ አስተካክለው እንደሚመጡ ተናግረዋል። የሀዲያ ሆሳዕናው አሠልጣኝ ያሬድ ገመቹ በበኩላቸው የፍሬዘር በቀይ መውጣት ጨዋታውን ከባድ እንዳደረገባቸው ጠቁመው ረጅም ደቂቃ በጎዶሎ ተጫዋች ተጫውተው ነጥብ አስጠብቀው በመውጣታቸው ተጫዋቾቻቸውን አድንቀዋል።